የአርታኢዎች መልእክት– ይህ ጽሁፍ በሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ዙርያ ለሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ የቀረበ ሙያዊ አስተያየት (Amicus Curiae) ሲሆን በጸሃፊዎቹ ፍላጎት በአማርኛ እንዲታተም የተወሰነ ነው።

 ፅሑፍ አዘጋጆች 

ሙሉ በየነምሕረተአብ ገ/መስቀልኣብራሃ መሰለ ገብረሂወት ሓዱሽ ገብረመስቀል ሃይሉ እና ገብረአበዝጊ ወ/ስላሴ [1]

መግብያ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2012 – የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ በቀን 03/09/2012 ዓ/ም ባሰራጨው የፕረስ መግለጫ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ለመመለስ ግብዓት ይሆነው ዘንድ የሙያ አስተያየት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህ ፅሑፍ ጥሪውን ተከትሎ የተዘጋጀ ሙያዊ ኣስተያየት ነው፡፡

ለጉባዔው የቀረበው ጥያቄ

የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ምላሽ አለመስጠቱ የገጠመንን ችግር በመፍታት ረገድ ክፍተት አለበት የሚያስብል ነው፡፡ በመሆኑም ከፍ ብለው የተጠቀሱትን የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች (አንቀፅ 54(1) አንቀፅ 58(3) አንቀፅ 93) ከሕገ መንግስቱ አላማና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማስተሳሰርና በማገናዘብ ትርጉም እንዲሰጣቸው የሚል እንደሆነ መግለጫው ላይ ተገልፀዋል፡፡

ጥሪው በተጨማሪም የሙያ አስተያየቱ የቀረበው የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ጭብጥ ጭምር የሚዳስስ መሆን ይኖርበታል በማለት ያክላል፡፡

ጉባዔው የቀረበለትን ጥያቄ በመመለስ ረገድ ከግምት ውስጥ ሊወስዳቸው ይገባል የምንላቸውን አንኳር ጉዳዮች በሶስት ዋና ዋና የክርክር ነጥቦች ሥር በመክፈል እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

ጥያቄው ምናባዊና ምክር ለመጠየቅ የቀረበ በመሆኑ ጉባዔው ጉዳዩን ማስተናገድ ስልጣን የለውም

የጥያቄው ምናባዊነት በተመለከተ

እላይ እንደተጠቆመው የቀረበው ጥያቄ በከፊል በቅድመና በምርጫ ግዜ “የአስቸኳያ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን….” ብሎ ይጀምራል። ይቀጥልና በእንደዚህ ሁኔታ የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው መንግስታዊ ተቋሞች ምን እንደሚሆን፣ ምርጫውስ የአስቸኳይ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነውን ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል? የሚሉ ጥያቄዎችን በመፍጠርና ለጥያቄዎቹ “ሕገ መንግስቱ ምላሽ አለመስጠቱ” በማንሳት ክፍተት እንዳለበትና በዚህ ምክንያትም ችግር እንደገጠመ ያትታል። ጥያቄው በባህርውና ባቀራረቡ ምናባዊ ከመሆኑም በላይ ብዙ አሳማኝ ያልሆኑ መላምቶች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለዚህም በማሳያነት የሚከተሉትን አስቀምጠናል።

መጀመርያ ጥያቄው የቀረበበት መንገድ ምናባዊ (hypothetical) መሆኑ ግልፅ ነው። ማለትም የተጠቀሱት ሁነቶች ወደፊት ብያጋጥሙ ሊኖር ስለሚገባ መፍትሔ የሚመለከት ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እታች እንደተብራራው እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች በትርጉም መልክ የሚስተናገዱበት መንገድ አላበጀም፡፡

ሲቀጥል መንግስት እራሱ ባመነበት እንኳን ቢኬድ በሕገ መንግስቱ አግባብ የተነሳውን ጥያቄ በመፍታት ረገድ ሊወሰዱ የሚችሉ እስከ ሶስት የሚያክሉ ሌሎች አማራጮች እንዳሉ ከዚህ በፊት አስቀምጧል። በመሆኑም  ሕገ መንግስቱ ለሁኔታው መፍትሔ አላስቀመጠም ተብሎ የቀረበና ለጥያቄ መሰረት የሆነው መላምት የሚያስኬድ አይደለም፡፡

በተጨማሪም የተፈጠረ ሕገ መንግስታዊ ክፍተት አለ እንኳን ቢባል በሕገ መንግስቱ እንዲህ ዓይነቱ ሁነት ለትርጓሜ ከሚያስቀርቡ መንገዶች አንዱ አይደለም። ከዚሁ በተያያዘ የተከበረው ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቅን አስመልክቶ ባደረገው ክርክር ላይ ጥያቄው ለመላክ እንደ መነሻ ተደርገው ሲነሱ ከነበሩት ሕጎች ዋነኛው አዋጅ ቁጥር 798/2005፣ አንቀፅ 3(2(ሐ)ን ይጠቀሳል። ድንጋጌውም በፍርድ ሊወሰን የማይችል በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ አንድ ሶስተኛ  ወይም ከዝያ በላይ በሆኑ በፌደራል ወይም በክልል ምክር ቤት አባላት ወይም በፌደራሉም ሆነ በክልል አስፈፃሚ አካላት ለአጣሪ ጉባዔ ሊቀርብ ይችላል የሚል ነው። ይሁንና እዚህ ላይ የንዑስ ኣንቀፅ 2 ሃሳብ ለመረዳት የንዑስ ቁጥር 1 ይዘትና አንድምታ ማየት የግድ ይለናል። ምክንያቱም አንቀፅ 3(2) “በዚህ አንቀጽ ንዑስ (1) መሰረት የሕገ መንግስት ትርጉም ጉዳይ ለአጣሪ ጉባዔ ሊቀርብ የሚችለው” ብሎ መጀመሩ ሁለቱንም ንዑሳን አንቀፆች አንድ ላይ መነበብ እንዳለባቸው ስለሚያስገድድ፡፡ አንቀፅ 3(1) ደግሞ እንዲህ ይላል አጣሪ ጉባዔው ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሰራር ወይም የመንግስት አካል ውሳኔ ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግስቱ ጋር ይቃረናል የሚል ጥያቄ በፅሑፍ ሲቀርብለት ያጣራል፡፡ እዚህ ላይ  ለሕገ መንግስት ትርጉም የሚጋብዙ ሶስት ፍሬ ነገሮች ተቀምጠዋል፡፡ እነሱም ሕግ፣ ባሕላዊ አሰራር እና የመንግስት አካል/ባለስልጣን ውሳኔ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሕገ መንግስት ጥያቄ እንዲቀርብ ከነዚህ አንዱ ከሕገ መንግስቱ ጋር መቃረንን አስመልክቶ የቀረበ ጥያቄ መኖርን ይፈልጋል፡፡ ይህንን አረዳድ በተለይም የሕገ መንግስቱ የበላይነት ከሚደነግገው አንቀፅ 9(1) አንድ ላይ ስናነበው ከሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት ውሳኔ ውጪ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሊነሳ እንደማይችል በበለጠ እንገነዘባለን።

ስለዚህ አንቀፅ 3(2) የአካሄድ ጉዳይ ማለትም የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በምን አኳኋን መቅረብ እንዳለበት የሚያትት ሲሆን፤ አንቀፅ 3(1) ደግሞ በመሰረቱ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ ሊቀርብባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም በአንቀፅ 3(2) የተቀመጡት የሕገ መንግስት ጥያቄ ማቅረብያ መንገዶች የግድ በአንቀፁ ንዑስ ቁጥር አንድ ከተቀመጡ የሕገ መንግስት ጥያቄዎች የሚነሱ መሆን እንዳለባቸው ግልፅ ይሆናል፡፡ ይሁንና አሁን በጭብጡ የተያዘ ጉዳይ በአዋጁ አንቀፅ 3(1) ከተቀመጡ ጥያቄዎች ውጪ ነው፡፡ ምክንያቱ ሕገ መንግሰታዊነቱ ክርክር ያስነሳ ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር ወይም የመንግስት ውሳኔ ስለሌለ፡፡ ይህንንም ከጥያቄው አቀራረብ ምናባዊነትና ካለው ተጨባጭ እውነታ መረዳት ይቻላል፡፡ ለጥያቄው መነሻ የሆነ ሕግም ይሁን የመንግስት ውሳኔ የለም፡፡ በመሆኑም ኣጣሪ ጉባዔው ጥያቄውን የማየት ሕጋዊ ስልጣን የለውም እንላለን፡፡

ከዚህም በተያያዘ የጉባዔውና የፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን አስመልክቶ ብዙ ክርክር ስያስነሳ የቆየና እዚሁ መጠቀስ ያለበት አንዱ ጉዳይ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 62(1) የተቀመጠው ሕገ መንግስቱን ‘የመተርጎም’ ስልጣንና በአንቀፅ 83 እና 84 የተቀመጡትን ሕገ መንግስታዊ ‘ጉዳዮች’/’ክርክሮች’ የማጣራትና የመወሰን ስልጣኖች የተለያዩ የስልጣን ስፋቶችን ያመላክታሉ ወይስ አይደለም የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ሕገ መንግስቱ ሲፀድቅ እነዚህ አገላለፆችን በተመለከተ የነበረ አረዳድ ምን እንደሆነ ክርክሩ በመፍታት ረገድ የተሻለ አማራጭ ነው ብለን እናምናለን። ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ጉዳዩን በማስመልከት ያደረጉት ጥናት እንደሚያሳየው በሕገ መንግስቱ የማርቀቅ ሒደት ላይ አገላለፆቹ አንዱ ሌላኛውን በሚተካ መልኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበርና፤ በተለይም በወቅቱ የነበረው የዳኝነት ጉዳዮች ኮሚቴ የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 83 አስመልክቶ ባቀረበው ሐተታና በሕገ መንግስቱ ጉባዔም በሙሉ ድምፅ የፀደቀው አስተሳሰብ ሕገ መንግስት መተርጎም ማለት ሁሉም የሕገ መንግስት ክርክሮችን (constitutional disputes) እልባት መስጠት ማለት እንደሆነ ይተነትናል።[2] ይህም የሚያሳየን ነገር ቢኖር በአገራችን የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ማስተናገድ የሚቻለው ሕገመንግስትን በሚመለከት ክርክር ሲነሳ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ክርክር ደግሞ በባህሪው ብያንስ ሁለት አካላት የሚያሳትፍና ተለይቶ በተቀመጠ ተጨባጭ ጉዳይ ላይ መሳሳብ መኖርን ይፈልጋል፡፡ እላይ እንደተገለፀው በተያዘው ጉዳይ የተነሳ ክርክር የለም። በተጨማሪም እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ክርክር አለ እንኳን ቢባል ክርክር መኖሩን ብቻ በቂ አለመሆኑን ነው፡፡ እላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ክርክሩ በሕገ መንግስቱ እና በአዋጁ አንቀፆች ተለይተው ከተቀመጡት ሶሰት ጉዳዮች የሚመለከትና ከሕገ መንግስቱ መቃረንን እንደ ጭብጥ የያዘ  መሆን የኖርበታል፡፡ 

በመሆኑም የቀረበው የሕገ መንግስት ትርጉም ይሰጠን ጥያቄ ክርክር የሌለበት፤ ባቀራረቡ ምናባዊ የሆነና ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟላ ስለሆነ የተከበረው ጉባዔ ጉዳዩን የማየት ስልጣን እንደሌለው በመገንዘብ ጥያቄው ውድቅ ማድረግ አለበት እንላለን። 

ጉባዔው ምክረ-ሐሳብ (advisory opinion) የመስጠት ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ  

በኛ ግንዛቤ ጥያቄው ወደ ጉባዔው ሲላክ በተወካዮች ምክርቤት ላይ የተስተዋለው አረዳድ እላይ እንደተጠቀሰው ሆኖ ጉባዔው የቀረበለትን ጥያቄ  ላይ የባለሞያ አስተያየት ለመጠየቅ ባሰራጨው ጥሪ እንደገለፀው ግን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለት ጥያቄ ‘የሞያ አስተያየት’ ለመጠየቅ እንደሆነ ይገልፃል። ይህም በአንዳንድ አገሮች እንደሚደረገው ምክረ ሐሳብ (advisory opinion) ሊባል የሚችል ነው ብለን እንወስዳለን። ጉባዔው ጥያቄው የተረዳበት መንገድ ይህ ከሆነ አጣሪ ጉባዔውም ይሁን የፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄው የማስተናገድ ስልጣን የላቸውም እንላለን። 

ለዚህም የመጀመርያ አስረጂ መሆን ያለበት እራሱ ሕገ መንግስቱ ነው። ፍርድ ቤቶች ወይም ሌሎች የዳኝነት ስልጣን ያላቸው አካላት ሁለት አይነት ጉዳዮች ላይ ስልጣን ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እነሱም የክርክር ስልጣን (contentious jurisdiction) እና ምክር የመስጠት ስልጣን (advisory jurisdiction) ናቸው። ነገር ግን ሁለተኛው ዓይነት ስልጣን ከፍርድ ቤቶች ማንነትና ባህርይ ስለማይነሳ ግልፅ የሕግ መሰረት ሊኖረው እንደሚገባ ብዙ ጥናቶች ያስረዳሉ። የብዙ አገሮች ተመኩሮዎችን የሚያሳዩንም ይህንኑ ነው። ለምሳሌ የህንድ ሕገ መንግስት አንቀጽ 143 ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በግልፅ ምክር የመስጠት ስልጣንን ይሰጠዋል። የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጀርመን የሕገ መንግስት ፍርድ ቤትም እንዲሁ በግልፅ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ሲሰሩበት ቆይቷል።[3] ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት፣ የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ እንዲሁም የአሜሪካ አገራት የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት በማቋቋያ ሕጎቻቸው በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት አስፈላጊ ምክር የመስጠት ስልጣን ጥቅም ላይ አውለዉታል።

በአንፃሩ የአሜሪካ ሕግ ለፍርድ ቤቶች የሰጠው ምክረ ሐሳብን የመስጠት ስልጣን ስለሌለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለረጅም ግዜ የሚቀርቡለት ምናባዊም ይሁኑ ምክረ ሐሳብን የሚሹ ጥያቄዎች ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።[4] ፍርድ ቤቱ መጀመርያ የምክረ ሐሳብ ጥያቄ ሲቀርብለት የመንግስት አካላት የስልጣን ክፍፍልን መሰረት በማድረግና የተዓቅቦ መርሆ ለዴሞክራሲያዊ አሰራር ያለው አስተዋፆን በመገንዘብ በሕግ አውጭውና ስራ አስፈፃሚው ሊወሰኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች ላይ ምክር ባለመስጠትም ጭምር እጁ ላለማስገባት ወስኗል።[5] በተመሳሳይ መልኩ የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመመስረቻ ስምምነት ፍርድ ቤቱ ምክር የመስጠት ስልጣን ስላልሰጠው ምክር ለመሰጠት ሌላ ሕግ እስኪወጣ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖበታል። 

 ከዚሁ መገንዘብ እምንችለው ምክር መስጠት በባህሪው የዳኝነት ስራ አለመሆኑን እና ያንን ስልጣን ከሚሰጥ ግልፅ ሕግ እንደሚመነጭ ነው። ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመለስ አጣሪ ጉባዔውንና ፈደሬሽን ምክር ቤት ያቋቋመው ሕገ መንግስት የማማከር ስልጣን  እንዳልሰጣቸው እንገነዘባለን። ይሁንና በአዋጅ 251/1993 አንቀጽ 4(2) የተቀመጠውና የፌደሬሽን ምክር ቤት ‘በሕገ መንግስት ትርጉም የምክር አገልግሎት ለመስጠት አይገደድም’ የሚለው አገላለፅ ተገልብጦ ሲነበብ ስልጣን አለው ሊያስብል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስልጣኑ በሕገ መንግስቱ በግልፅ ያልተሰጠ በመሆኑ ሕገ መንግስቱ ያልሰጠውን ስልጣን ደግሞ  በአዋጅ መጨመር የሕገ መንግስታዊነት ጥያቄ ስለያሚስነሳ[6] ስልጣን እንዳልተሰጠው መቆጠር አለበት ወደሚል  መደምድምያ ያደርሰናል። ጉባዔው ይህንን ዘሎ ምክር ወደ መስጠት ከሄደ ሊወጣው ወደማይችለው የምክር ጥያቄ ናዳ ሊያመራ እንደሚችልም ለመጠቆም እንፈልጋልን፡፡ በመሆኑም ጉባዔው በቀረበው ጉዳይ ላይ የማማከር ሕገ መንግስታዊ ስልጣን እንደሌለው በመገንዘብ ጥያቄው ውድቅ ሊያደርገው ይገባል፡፡

  • አጣሪ ጉባዔው ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለኝ ብሎ ቢወስንም እንኳ ስልጣኑ ባይጠቀምበት የተሻለ ስለመሆኑ

ጉባዔው ጥያቄውን የማየት ስልጣን እንደሌለው እላይ የተቀመጡት የመቃወምያ ክርክሮች በማለፍ ጥያቄው የማስተናገድ ስልጣን አለኝ የሚል ድምዳሜ ቢደርስ እንኳን ስልጣኑ ባይጠቀምበት የተሻለ ውጤት እንደሚኖረው በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት መግቢያ እና ዝርዝር ዓንቀፆች ላይ የተቀመጡትን የሕግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲ መርሆች፣ ምርጫና የዳኝነት ስርዓት መርሆች ጋር በማያያዝ ከታች በዝርዝር በተቀመጡት የክርክር ነጥቦች ለማንሳት እንወዳለን፡፡

  • ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ የህዝብ ስልጣን የበላይነት እና ምርጫ

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች የማይጣሱና የማይገደቡ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች እና በአገራት ሕገ መንግስታት ከፍተኛ ቦታ ያገኙ መርሆች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ የዓለም አቀፍ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን፣ የአፍሪካ ሰብአዊ መብቶች ቻርተር እና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮንፈረንስ የቭየና መግለጫ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይም የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን በአንቀፅ  1(3) ሁሉም አባል አገራት የህዝቦች የራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው እንዲያረጋግጡ፣ የማክበር እና የማገዝ ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የቃል ኪዳኑ አንቀፅ  1 ከቃል ኪዳኑ ሰብአዊ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለፅ፣ የመሰብሰብ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ነፃነቶች፣ ከአድልዎ ነፃ የመሆን እና የመምረጥና መመረጥ መብቶች ጋር አንድ ላይ ሁኖ የሚተገበር መብት መሆኑ ያሳያል፡፡ ይህ አተረጓጎም በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 12 ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ የአፍሪካ ቻርተርም በአንቀፅ  20(1) ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር የማይነካ መብት እንዳላቸው በመግለፅ በነፃ ፈቃዳቸው የፖለቲካ ሁኔታቸውን የመወሰን መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡

በ1993 ዓ/ም  የወጣዉ የአፍሪካ ሕብረት መቋቋምያ ሕግ (Constitutive Act of the African Union) አንቀፅ  3(ሸ) ላይም ዴሞክራሲ እንደ አንድ ወሳኝ መርህ ተቀምጧል። ይህም ዴሞክራሲያዊ መርሆች እና ተቋማት በመከተልና በማክበር፣ የህዝብ ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት አክብሮ እና መልካም አስተዳደር ተከትሎ መንግስታዊ ዉሳኔዎችና ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ይደነግጋል። እነዚህ መርሆች ደግሞ በ2004 ዓ/ም የፀደቀዉ የአፍሪካ ዴሞክራሲ ምርጫ እና አስተዳደር ቻርተር (African Charter on Democracy, Election and Governance) ላይ በመግቢያዉ በግልፅ በመጥቀስ ከፍተኛ አፅንዖት ሰጥቷቸዋል።

በአፍሪካ ዴሞክራሲ፣ ምርጫ እና አስተዳደር ቻርተር ዓላማ ተብለዉ በግልፅ ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ በአንቀፅ  2(3) ላይ ያለዉ ድንጋጌ ነዉ። ይህም አንድ መንግስት ያልተቋረጠ፣ ነፃ እና ፍትሓዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችሉ ተአማኒነት ያላቸዉ ተቋማት በመገንባት እና በዚሁ መሰረት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የመንግስትን ስልጣን በህዝብ ለተመረጠዉ ፓርቲ ማስተላለፍ እንዳለበት የሚደነግግ ነዉ። በተጨማሪም በቻርተሩ አንቀፅ 2(4) መሰረት ማንኛዉም ከሕገ መንግስት ዉጪ የሚደረግ የመንግስት ስልጣን ሽግግር የተከለከለ፣ ተቀባይነት የሌለዉ እንዲሁም መወቀስ ያለበት ጉዳይ መሆኑን ያስገነዝባል። ይህ ዓይነት የመንግስት ስልጣን ሽግግር መረጋጋት፣ ሰላም፣ ፀጥታ እና እድገት ጋር የሚጣረስ አካሄድ መሆኑን በግልፅ ተደንግጓል።

በዚሁ ቻርተር ምርጫ ማድረግ አንድ የዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ብቸኛ አማራጭ መሆኑና ምርጫን ማካሄድ ግዴታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምርጫን አላካሂድም ማለት እንደ ስልጣንን በሃይል መያዝ (unconstitutional change of government) የሚያስቆጥር መሆኑን ነዉ። በዚህ ሕግ አንቀፅ  23(5) መሰረት ስልጣን ለመያዝ ወይም ለማራዘም የሚደረግ ማንኛዉም የሕግ ማሻሻያ ወይም የሕገ መንግስት ክለሳ (amendment and revision) ወይም ማንኛዉም የሕግ ለዉጥ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስልጣን ሽግግር የሚጣረስ ተግባር መሆኑን እና በሕብረቱ ቅጣት የሚያስከትል ተግባር እንደሆነ ይደነግጋል። ይህንን በሕብረቱ የመቋቋምያ ሕግ አንቀፅ 30 እንደተቀመጠውም አባል አገራት ከአባልነታቸው እስከማገድ ድረስ ይሄዳል፡፡ በስልጣን ለመቆየት የሚደረገዉ የሕገ መንግስት ትርጉምም ይሁን ማሻሻያ ሕገ ወጥ እና በምርጫ የሚደረግ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር መርህ የሚጣረስ ተግባር በመሆኑ በሕብረቱ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል አካሄድ ነዉ።

ከላይ የተጠቀሱት የአፍሪካ ሕብረት ሕጎች ከኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንፃር ሲቃኙ የሚጣጣሙና የኢትዮጵያ መንግስት ሊያከብራቸው የሚገቡ ናቸው። ይህም በአንቀፅ  8(3) እና 39(3) የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት መሰረት ሕዝቦች ሕገ መንግስቱ ባስቀመጠዉ የመሳተፍ መብት ተጠቅመዉ ያሻቸዉን መንግስት የመምረጥ መብት ያልተገደ (በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን) መሆኑ በግልፅ ይደነግጋል።

መንግስት የተለያዩ መብቶች ሊገድብ ቢችልም የሚደረገው ገደብ የማይገደቡ ተብለው የተጠቀሱትን መብቶች የመገደብ ውጤት ካለው ግን መብቶች ላይ ገደብ ሊጥል አይችልም፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ  93 በግልፅ እንደተቀመጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (አንቀፅ 39 (1 እና 2) እና የፌደራል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት (አንቀፅ 1) በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ቢሆን የማይገደቡ ናቸው፡፡ ሊገደቡ ይችላሉ በሚባሉት አንቀፅ 54(1)እና 58(3) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ መገደብና የመንግስት ስልጣን ማራዘም ደግሞ የህዝቦች መንግስታቸውን የመምረጥ፣ የመቀየር እና የመተካት የማይነካ መብታቸው እንደመገደብ እና የስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ እንደመቀየር ይቆጠራል፡፡ የሚመጣው ውጤት ይህ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ሊሰጥ የሚችለውን የማራዘም ትርጉም ኢሕገ መንግስታዊ ያደርገዋል፡፡

አንቀፅ  9(3) ሕገ መንግስታዊ ከሆነ መንገድ ውጪ ስልጣን መያዝ (በስልጣን መቆየትን ጨምሮ) እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ ሕገ መንግስቱ በአንቀፅ 38 መሰረት ምርጫ እንደ ብቸኛ የመንግስት ስልጣን መያዣ መንገድ አድርጎ አስቀምጧል። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 58(3) መሰረትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት አመታት ብቻ መሆኑን ፤ የፌደሬሽን ምክር ቤትም እንዲሁ የአምስት ዓመት የስራ ዘመን እንዳለው (አንቀፅ  67(2)) እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ግዜ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እኩል እንደሚሆን (አንቀፅ  72(3)) እና የሚኒስትሮች ካውንስል የሚያቋቁሙ ሚኒስትሮች ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ (አንቀፅ 74(2) ይደነግጋል፡፡ ይህ የሚያሳየን ሕገ መንግስቱ በጥንቃቄና በማያሻማ መንገድ የግዜ ገደብ ማስቀመጡንና ያንን የሚቃረን ውሳኔ ሕገ መንግስቱን ውጤት አልባ የሚያደርግ ስለሚሆን የተከበረው አጣሪ ጉባዔ ጉዳዩን ላለማየት ቢወስን ለሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ መዳበር የተሻለ ውጤት ይኖረዋል እንላለን፡፡ 

  • የቀረበው ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያመዘነበት መሆኑ ጉባዔው በሕገ መንግስት ትርጉም አቋም መያዙ የተቋሙ ክብርና ተአማኒነት ሊጎዳ ስለመቻሉ

እላይ ካስቀመጥነው ነጥብ ጋር ተያያዥ የሆነውን ጉዳይ ስናነሳ የምርጫ ዝግጅት እና ምርጫ ማካሄድ ከሕገ መንግስት ክርክር በላይ ፖለቲካዊ ሽኩቻው የበለጠ ቦታ እንደነበረውና እንዳለው የሚያሳዩ እውነታዎች አሉ፡፡

አንደኛ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈው የ’ምርጫ ማድረግ አልችልም ውሳኔ’ እና ይህን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን ያፀደቀበት ሂደት ግልፅነት እና አሳታፊነትን በእጅጉ የጎደለው አካሄድ ነበር፡፡ የትኛው አካል በምን ሁኔታ እንዳራዘመው፣ የተደረጉት የጤና እና የህዝብ ደሕንነት ውይይቶች ምን እንደነበሩ ምንም ለህዝብ ይፋ የተደረገ ነገር የለም፡፡ በምርጫ ቦርድ የተወሰደው ምርጫ የማራዘም ውሳኔ መንግስት የጤና እክሉ በተመለከተ የተወሰዱ እርምጃዎችን መውሰድ ሳይጀምር የተደረገም ነበር፡፡ በዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ከቀረቡት አራት አማራጮች ለምን ይህ የሕገ መንግስት ትርጓሜ እንደወሰደም የተገለፀ ነገር የለም፡፡ የምርጫ ማራዘም ጉዳይ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አድርጎ ወደ መንግስት ከዛም ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሄደ ቀጥሎም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት የሚሄድ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውሳኔ እያስተላለፉ የመጡት በውሳኔው ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉትን አካላት ናቸው፡፡

ሁለተኛ መንግስት ምርጫውን ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ እያራዘመ ነበር፡፡ ምርጫው የሚካሄድበት ወር ከተለመደው ግንቦት ወደ ነሐሴ የተገፋበት ይህም ብዙ ተቃውሞ የተነሳበት እና በዛ ወቅትም ምርጫው መካሄድ መቻሉን በጥርጣሬ የታየበት ሁኔታ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ጊዜ ሲሰጥዋቸው የነበሩት የምርጫ አስፈላጊነትን የሚያሳንሱ ንግግሮች (ምርጫ ሳይደረግ 20 እና 30 ዓመታት መቆየት ይቻላል የሚለውን ጨምሮ) እና ዓለም አቀፋዊ የጤና ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ባለበት ሁኔታ ሆነው ምርጫ ያካሄዱ ሃብታምም ደሃም አገራት እንዳሉ እየታወቀ ያላካሄዱትን ብቻ በመጥቀስ እና ሊካሄድበት የሚችልበትን አማራጮች ላይ ውይይት ሳይካሄድ የተወሰነ እንደመሆኑ ይህንን ጥርጣሬ የሚያጎላ ነው፡፡ 

በዚህ የሕገ መንግስት ትርጓሜ ሊሰጥ የሚችለውን የስልጣን ማራዘም ውሳኔ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት ማጣት በማባባስ ወደ ተቃውሞ እና የፖለቲካ ችግር በማምራት፤ ይህንን ለመቆጣጠር ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየታወጀ አገሪቷ ወደማትወጣው ቀውስ ሊከታት ይችላል፡፡ አንዴ በምክንያት ምርጫ እንዲራዘም መፍቀድ የዴሞክራሲ ስርዓቱ እስከመጨራሻው መጉዳት የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ ስለዚህ ጉባዔው ከዚህ በጣም ፖለቲካዊ መልክ የያዘ ጉዳይ ራሱን አቅቦ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ሊያደርግ ይገባል፡፡

  • የጉባዔው ለጥያቄው ውሳኔ መስጠት ከዳኝነት መርሆች ጋር ሊኖረው ስለሚችል መቃረን

አንደኛ የዳኝነት ውሳኔ የሚሰጡ ተቋማት ከምንም ዓይነት ተፅዕኖ ወይ አድልዎ ነፃ ሆነው መስራት እንደሚኖርባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ይደነግጋሉ፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ፕሮቶኮል ይህ መርህ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ይህም በተቋም ደረጃ መረጋገጥ ያለበት ነፃነት ብቻ ሳይሆን በተለይም ተቋሞቹን የሚመሩ ሰዎች ለማሕበረሰቡ በሚታይ መልኩ በነፃነት የሚሰሩ መሆናቸውን ማሳየትም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ በቀን 06/09/2012 ዓ/ም በነበረው የፕረስ መግለጫ የጉባዔው ሰብሳቢ ያስተላለፉት መልእክት ጉባዔው ክርክሮችን በአግባቡ ሰምቶ ውሳኔ ይሰጣል ወይ የሚያስብል ነበር፡፡ በብዙ የሕገ መንግስት ምሁራን እንደ ትልቅ መከራከሪያ ነጥብ ተደርጎ ሲነሳ የነበረውና ጉባዔው የቀረበለትን ጥያቄ የመወሰን ስልጣንን አስመልክቶ የባለሞያ አስተያየት ተጠይቆበት ሲያበቃ ጉባዔው ውሳኔ እንደሰጠበት ለህዝብ መገለፁ እና ይህ ጥያቄም በጣም አስቸኳይ በሆነ ጊዜ እንደሚወሰን መገለፁ ለጉዳዩ አሳታፊነት የተሰጠውን ትኩረት አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡

ሁለተኛ የፌደሬሽን ምክር ቤት የራሱን የስልጣን ዘመን ሊያራዝምስ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ድርጊት አንድ ሰው/አካል በራሱ ጉዳይ ላይ ዳኛ ሊሆን አይችልም የሚለውን መሰረታዊ የዳኝነት መርህ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ እዚህ መታየት ያለበት ጉዳይ ይህ ጉባዔ ትርጉም ያስፈልጋል ባለበት ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ይሰጣል እንጂ ውሳኔው የሚወሰነው በፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

ሲጠቃለል ከላይ በተጠቀሱት መከራከሪያ ነጥቦች መሰረት በማድረግ የሚወሰነው ውሳኔ የሕገ መንግስቱ ምሰሶ የሆነውን የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የስልጣን ባለቤትነት የሚመለከት መሆኑ፣ ጥያቄው በጣም ፖለቲካዊ በመሆኑ፣ ጥያቄው ላይ መወሰን የጉባዔውና የፌደሬሽን ምክር ቤት ነፃነትና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ እና ከዳኝነት መርሆች አንፃር አጠራጣሪ ሁኔታዎችን የሚፈጥር በመሆኑ ይህ ጉባዔ በዚህ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ከመስጠት ታቅቦ የቀረበለትን ጉዳይ ውድቅ ሊያደርገው ይገባል እንላለን፡፡

  • ጉባኤው የቀረበለት ጥያቄ ተቀብሎ ቢያስተናግድም ትርጉም የተጠየቀባቸው አንቀፆች ትርጉም የሚሹ አይደሉም

የሕገ-መንግስት ኣጣሪ ጉባኤው ተጨባጭ ክርክር ሳይነሳ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ኣለኝ ብሎ ከላይ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦች የሚያልፋቸው ከሆነ፣ ትርጉም እንዲሰጥባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጉባኤው የቀረቡ ኣንቀፆች ማለትም አንቀፅ 54(1)፣ 58(3) እና 93 ትርጉም ኣያስፈልጋቸውም ብሎ ውድቅ ማድረግ ኣለበት እንላለን፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስችል የህግና የፍሬ ነገር ሃተታ ከታች በዝርዝር ቀርቧል፡፡

ከሁሉም በፊት መመለስ ያለበት ነጥብ ሕገ-መንግስት መተርጎም ያለበት መቼና በምን ሁኔታዎች ውስጥ ነው የሚል ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የዳበረ የሕገ-መንግስት ትምህርት የሚጠቁመን ነገር ቢኖር፣ ሕገ-መንግስት እንዲተረጎም አስፈላጊ የሚሆነው ሕገ-መንግስቱ ወይም የሕገ-መንግስቱ አንቀፆች ወይም ቃላት የግልፅነት ችግር ሲኖርባቸው፣ በቃላት ወይም በዓርፍተ ነገሮች ኣሻሚ የቃላት ትርጉም ወይም ኣረዳድ ሲፈጠር፣ ህገ-መንግስቱ የግድ ሊደነግገው ሲገባው ያልደነገገው ቁም ነገር ሲኖር፣ በሕገ-መንግስቱ ኣንቀፆች መካከል ወይም በሕገ-መንግስቱና ሌሎች ህግጋቶች ወይ ውሳኔዎች መካከል ያለመስማማት ወይም ግጭት ሲኖር፣ ህጉ ባለው ደረጃ ቢፈፀም ፍፁም ስሜት የማይሰጥ ወይም እጅግ የተዛባ ውጤት (absurdity) የሚያስከትል ሲሆን ነው፡፡ የህገ-መንግስት ትርጉም ዋና ዓላማም የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ለመጠበቅ ሆኖ ያንንም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የህገ-መንግስቱን የሽቅብና የጎንዮሽ የስልጣን ክፍፍል እንዲጠቅ፣ መንግስት ከተበጀለት የስልጣን ገደብ እንዳይወጣ ለመጠበቅና በጠቅላላ ህገ-መንግስታዊነትን ለማስፈን ነው፡፡

ከዚህ ኣንፃር አሁን ትርጉም እንዲሰጥባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ የቀረቡ የሕገ-መንግስት ኣንቀፆች ከላይ ከተጠቀሱ የሕገ-መንግስት ትርጉም እንዲሰጥ የሚያስገድዱ ምክንያቶች የትኛው ምክንያት ተሟልቷል ተብሎ መጠየቅ ኣለበት፡፡ ከላይ የተጠቀሱ ሦስቱ የህገ-መንግስት አንቀፆች በጥሞና ስናነባቸው በአንቀፆቹ ላይ ተጨባጭ የሆነ ግጭት ወይም ተቃርኖ ወይም የትርጉም አሻሚነት ወይም የአገላለፅ የግልፀኝነት ችግር የለም፡፡ በተመሳሳይ አረዳድ ሕገ-መንግስቱ የመንግስት ስልጣን ከኣምስት ዓመት በላይ የሚራዘምበት ሁኔታ ዝግ ማድረጉ በራሱ ስሜት የማይሰጥ ወይም እጅግ የተዛባ (absurd) ነው ሊባል ኣይችልም፡፡ ምክንያቱም የሕገ-መንግስት አንዱና ዋናው ዓላማ የመንግስትን ስልጣን መገደብ ነው፡፡ በዓለም ታሪክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ተመኩሮ አንፃር ስናየው፣ የመንግስታት ስልጣን በይዘትና በግዜ በአግባቡ ባለመገደቡ በህዝቦች ላይ ብዙ በደሎች መድረሳቸው፤ እነዚህም ለብዙ ህዝባዊ ትግሎች መነሻ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስታት ስልጣናቸውን ለማራዘም ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ለማሳካት ማንኛውንም የህግ ቀዳዳ የሚጠቀሙ በመሆኑ፣ ኣንድ ሕገ-መንግስት ያንን ቀዳዳ አስቀድሞ ለመድፈን ስልጣን ከምርጫ ውጪ ማራዘም የሚቻልበት መንገድ ዝግ ማድረጉ የሚጠበቅና እጅግ የሚደገፍ ስራ ነው፡፡ ስለሆነም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት በዚህ በኩል ጉድለት ኣለው ለማለት የሚያስችል ኣሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን በገጠመን ችግር ምክንያት ምርጫን በተለመደው ኣኳኋን ለማድረግ የሚያዳግት ሁኔታ ስለ ገጠመን በተለየ ዘዴና ኣሰራር መከወን አለብን የሚል አተያይ መምጣት አለበት እንጂ እንዲሁ ምርጫን ማራዘም የመጀመርያ መፍትሄ መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ ያሉ መፍትሄዎች አሟጥጦ በመጠቀም የህገ-መንግስቱን የስልጣን ገደብ ሳይጣስ ምርጫ ማድረግ የሚቻለበት ዕድል አለ፡፡ ህገ-መንግስቱም የስልጣን የግዜ ገደብ ላይ ልዩ ሁኔታ ለማስቀመጥ አለመፈለጉ ያንን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባቱ ሳይሆን፣ መንግስታት በትንሹም በትልቁም ክፍተቱን ተጠቅመው ስልጣናቸውን ለማራዘም እንደ ሰበብ እንዳይጠቀሙበት በመስጋት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ከዚህ የክርክር መንፈስ አንፃር ሲታይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት የአመስት ዓመት የግዜ ገደቡ በሚመለከት የማያሻማና ግልፅ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኣባላት በሚመለከት በኣንቀፅ 54(1) “. . . በየአመስት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ” በማለት ቁርጥ ያለ የግዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡ እዚህ ላይ የእነግሊዘኛው ቅጂ የተጠቀመበት ኣገላለፅ “shall” የሚል ኣስገዳጅ ሃይለ ቃል መሆኑ ሲታይ የተቃራኒ ትርጉም የማይቻል መሆኑ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚመለከት ሕገ-መንግስቱ አሁንም ግልፅ ነው፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ኣባላት ያስቀመጠውን የግዜ ገደብ በተመሳሳይ የአገላለፅ ስርዓት የምክር ቤቱ የግዜ ገደብም በአንቀፅ 58(3) በማያሻማ አኳኃን እንዲህ አመስት ዓመት መሆኑን ደግሞ ኣሰረግጧል፡፡ አንቀፁ ምክር ቤቱ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል ሲልም ያክላል፡፡ በዚህ ረገድ በሕገ-መንግስቱ ላይ ምንም ዓይነት የግልፅነትም ሆነ የዝምታ መንፈስ የለም፡፡ በመሆኑም ሕገ-መንግስቱ ያላየው ወይም ያልገመተው ሁኔታ ነበረ ለማለት ኣይቻልም፡፡ ይልቁንስ የመንግስት ስልጣን የሚጀምርበትና ሚያበቃበት ግዜ በቀናት ሳይቀር ሸንሽኖ ማስቀመጡ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር ምንም ዓይነት የሕግ ዝምታ የሌለ መሆኑን ብቻ ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከላይ የተጠቀሱ የሕገ-መንግስት ድንጋጌዎች በኣንቀፅ 93 መሰረት አሰቸኳይ አዋጅ ቢታወጅ በዚህ ምክንያት ምርጫ ማራዘም ይቻላልን? እነዚህ ድንጋጌዎች አንዱ በሌላው ላይ የሚኖራቸው ኣንድምታ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ኣደጋ ሲያጋጥም በህዝብ በተመረጠ ምክር ቤት የተሰየመ ሕጋዊ መንግሥት፣ አሰገዳጅ ሁኔታውን የሚያስከትለው ኣደጋ ለመቋቋም እንዲቻል፣ የተለየ ስልጣን ይሰጠዋል። ይሁንና እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ነጥብ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የማወጅ ስልጣን ተግባራዊ የሚሆነው፣ በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሰረት በዴሞክራሲያዊ ሂደት የተመረጠና የስልጣን ዘመኑ ባላለቀ ምክር ቤትና እሱን ባቋቋመው መንግስት መሆን ያለበት መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 9(3) ለዚህ አረዳድ ሁነኛ ኣሰረጂና ኣሳሪ አንቀፅ ነው፡፡ አንቀፅ 9(3) “በዚህ ሕገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው” ብሎ የደነግጋል፡፡ ይህንንም ከምርጫ ውጪ በማናቸውም አኳኋን ስልጣን መያዝ ሙሉ በሙሉ ዝግ ኣድርጎታል፡፡ በመሆኑም አንቀፅ 9(3) እያለ ያለው የስልጣን መያዣ ብቸኛው መንገድ ምርጫ መሆኑና ከዚህ ውጪ በሕገ መንግስት ትርጉም ስራም ቢሆን የአመስት ዓመቱ የስልጣን ገደብ ያለ ምርጫ ማለፍ የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ ከላይ የተቀመጠውን ትርጓሜና ኣረዳድ የሚሽረሸር የህገ-መንግስት ትርጉም ኣጠቃላይ የሕገ-መንግስቱ ዓላማና መንፈስ የሚያዛባ ነው የሚሆነው፡፡

በዚህ ረገድ ሊሰመርበት የሚገባው ቁምነገር ዴሞክራሲን እንደ ግብ የሚወስድ የሕገ መንግስቱ መግቢያ፤ ለብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉአላዊ ስልጣን የሚያጎናፅፍ የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 8፤ እንዲሁም በኣስቸኳይ የግዜ ኣዋጅም ቢሆን በመንግስት ሊገደቡ የማይችሉ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች የያዘውን ኣንቀፅ 39(1 እና 2) ስንመለከትና እነዚህ ስልጣኖችና መብቶች ያለ ምርጫ ትርጉም ኣልባ የሚሆኑ መሆናቸውን ስንገነዘብ፤ ስልጣንን ያለ ምርጫ ማራዘም ማለት በውጤት ኣጠቃላይ ሕገ-መንግስቱንና እንዲታነፅ የምንሻው ሕገ-መንግስታዊነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ተገቢ ያልሆነ ኣካሄድ መሆኑ ግልፅ ይሆንልናል፡፡

ስለሆነም የተከበረው የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ግምት ውስጥ በማስገባት የቀረበለትን ጥያቄ የማስትናገድ ስልጣን እንደሌለው በመገንዘብ፤ ይህ ከታለፈም ስልጣኑ አለመጠቀም ለሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ መጎልበት ይበልጥ ጠቃሚ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ፤ ይህንንም ሳይቀበለው ቢቀርና ወደ ፍሬ-ነገር ምርመራ ቢያመራ ለትርጉም የተመሩለትን የሕገ-መንግስቱ አንቀፆች ትርጉም የሚሹ ስላልሆኑ ጥያቄው ውድቅ ሊያደርጋቸው ይገባል በማለት የሙያ አስተያየታችንን እንቋጫለን፡፡ አስ


[1] ፅሑፉ ያዘጋጁት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት አስተማሪዎች ናቸው፡፡

[2] ጌታቸው  አሰፋ ‘All about Words: Discovering the Intention of the Makers of the Ethio­pian Constitution on the Scope and Meaning of Constitutional Interpretation’ የኢትዮጵያ የሕግ መፅሄት 24(2), (2011) (ገፅ 161-162)

[3] አሰፋ ፍስሃ፣ Constitutional Adjudication in Ethiopia: Exploring the Experience of the House of Federation (HoF) ሚዛን የሕግ መፅ ሄት 1(1) (2007) ገፅ 9

[4] ጆን ፍረዮን እና ላሪይ ክራመር “Independent Judges, Dependent Judiciary: Institutionalizing Judicial Self- Restraint,” N. Y. U. Law Review 77:4 (2002): ገፅ. 1003-1008.

[5] ዝኒ ከማሁ

[6] አሰፋ፣ እላይ ቁጥር ሶስት እንደተጠቀሰው

Previous post

Commentary: The 2015 Declaration of Principles is not a treaty and Ethiopia does not have obligations therefrom

Next post

AS Investigates: A decade ago Ethiopian diplomats siphoned $640,000 from maids in Lebanon to pay off a US based lobby firm. What happened next?