AfricaAnalysisConstituional debateEthiopiaEthiopia in transitionOppostion PartiesProsperity Partyself determinationTigray regional stateTPLF

አስተያየት: የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ፣ የትግራይ ክልላዊ ምርጫ እና ቀጣይ እውነታዎች

የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ከሪያ ኢብራሂም በትግራይ ክልል እና በማእከላዊው መንግስት መካከል ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠር አለምግባባትና ማእከላዊው መንግስት የወሰደውን ምርጫ የማራዝም ውሳኔ በመቃወም ነበር ከአፈ ጉባኤነታችው በፈቃዳቸው የለቀቁት። ዛሬ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው የክልል ምርጫ ተገኝተው መርጠዋል። ፎቶ፥ የትግራይ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ።

በማርሸት ሙሀመድ ሀምዛ

አዲስ አበባ፥ ጷግሜ 04/2012 – የትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለበት በዛሬው እለት እና እስካሁን ባሉት ወራቶች የክልሉ መንግስት እና የፌዴሬሽን ም/ቤት ፍጥጫ ቀጥሏል። አስቸኳይ ስብስባውን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ/ም ያካሄደው የፌዴሬሽን ም/ቤት የትግራይ ክልል መንግሥት ጳጉሜ 4 ቀን የሚያካሂደው ምርጫ ህጋዊ ውጤት የለውም የሚል ውሳኔ አሳልፏል። የፌዴሬሽን ም/ቤት ስብሰባ ዋዜማ ላይ የትግራይ ክልል ም/ቤት ባወጣው መግልጫ ከዚህ በፊት በክልሉ መንግሥት ተደጋግሞ እንደሚነገረው ሁሉ ክልላዊ ምርጫው በ”ማንኛውም ጣልቃ ገብነትና ጫና እንደማይቆም” በማረጋገጥ የፌዴሬሽን ም/ቤት ከማንኛውም “አደናቃፊ” ውሳኔ እንዲታቀብ አስጠንቅቆም ነበር።

የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚነገረው ያለፈ ትርጉም ያዘለ፣ ሊያስከትል የሚችለው ውጤትም በጣም የሰፋ ነው። ለዚህም እንደመነሻ ም/ቤቱ በውሳኔው መግለጫ የዘረዘራቸውን ሃሳቦች መመልከት በቂ ነው። ም/ቤቱ የትግራይ ከልል ምርጫ ‘ኢ ሕገመንግስታዊ’ መሆኑን፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሀገራዊውን ምርጫ ለማራዘም ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሁም ከዚህ በፊት በፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባዔ የተጻፈለትን ማሳሰቢያ የክልሉ ም/ቤት እና መንግስት አለመቀበሉ ኢ-ሕገመንግስታዊ መሆኑን፣ እና የክልሉ መንግስት ያወጣቸው ክልላዊ የምርጫ ማስፈጸሚያ ሕጎች ከፌዴራሉ ሕገመንግሥት የሚቃረኑ መሆናቸውን በመጥቀስ ባጠቃላይ ክልላዊ ምርጫው እና ሂደቶቹ በሙሉ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መሠረት “እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይጸኑ እና ተፈጻሚነት የሌላቸው ናቸው” ሲል ወስኗል። በመጀመሪያ የሚነሳው ጥያቄ ይህ ውሳኔ ምን ማለት ነው የሚለው ነው።

ሕገመንግሥታዊ ነው ማለት?

የውሳኔውን ዝርዝር አንድምታ ከማየታችን በፊት ግን አንድ አንባቢያን ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ቢኖር የትግራይ ክልል የሚያካሂደው ምርጫ “ኢ-ሕገመንግሥታዊ” የሚያስብለው የፌዴሬሽን ም/ቤት 6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማራዘም ያሳለፈውን ውሳኔ ባለማክበሩ አይደለም። የፌዴሬሽን ም/ቤት በውሳኔው ይሄንን እንደ ሕገመንግሥታዊ ጥሰት የጠቀሰው ቢሆንም፣ ነገር ግን በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ከተቀመጠው የሥልጣን ክፍፍል አንጻር ከተመለከትነው፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት የክልል ም/ቤቶችን የሥልጣን ዘመን የማራዘም ግልጽ ሥልጣን የለውም። የክልል ም/ቤቶች ምርጫ መራዘም ካለበት መራዘም የነበረበት በክልሎች ውሳኔ (በራሳቸው ክልላዊ የሕገመንግሥት ሥርዓት መሠረት) ነበር። በርግጥ በተቃራኒው የፌዴሬሽን ም/ቤትን ውሳኔ ደግፈው የሚከራከሩ ምሁራን አሉ። በኔ አስትያየት እነሱም ቢሆኑ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በክልል ም/ቤቶች ጉዳይ ላይ ምንም ግልጽ ውይይት ባልተደረገበት ያቀረበው ደካማ የውሳኔ ሀሳብ በፌዴሬሽን ም/ቤትም ምንም በቂ የሕግ ትንታኔ ሳይሰጥበት በግርድፉ በመጽደቁ የሚስማሙ አይመስለኝም።

የትግራይ ክልል ምርጫን ኢ-ሕገመንግሥታዊ የሚያረገው ክልሉ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ለፌዴራል መንግሥት የተሠጠውን ሥልጣን በመተላለፍ ክልላዊ የምርጫ ሕግ መደንገጉ እንዲሁም ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ መገኘቱ ነው። የፌዴሬሽን ም/ቤት በመግልጫው እንደጠቀሰው የክልሉ ድርጊት በርግጥም ከፌደራሉ ሕገመንግሥት አንቀጽ 55(1)፣ 55(2) እና 102 አንጻር ሲታይ የሕገመንግሥታዊነት ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል ነው። የትግራይ ክልል ሕገመንግሥትም ቢሆን የክልሉ ም/ቤት በምክር ቤቱ የተወካዮችን ቁጥር ከመወሰን አልፎ ምርጫን በተመለከት ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው አያመለክትም። ይህም የሆነው ሥልጣኑ የፌዴራል መንግሥት መሆኑ በፌዴራሉ ሕገመንግሥት በመደንግጉ ነው። በቀጥታ ሥልጣን የሚሰጠው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ አለመኖሩ የትግራይ ክልል መንግሥት ሌላ የሕግ ድጋፍ እንዲያፈላልግ አስገድዶታል።

የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ የምርጫ ሕጎች ከማጽደቁ በፊት የክልሉ መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክልሉ ምርጫ እንዲያስፈጽም ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ጥያቄው በምርጫ ቦርድ ውድቅ ሲደረግ ነው የክልሉ ም/ቤት ሕግ ወደ ማውጣት እና የምርጫ ኮሚሽን ወደ ማቋቋም የሄደው። ምንዓልባት ክልሉ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ያቀረበበት መሠረታዊ ምክንያት ከመነሻው ክልሉ በራሱ ምርጫ የማስፈጸም ሥልጣን እንደሌለው ተረድቶ ያደረገው እንደሆነ ግምት መውሰድ ይቻላል።

የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እንዲሁም የፌዴሬሽን ም/ቤት ሀገር አቅፍ ምርጫን ባጠቃላይ ማራዘሙን ተከትሎ የትግራይ ክልል ያመራው የክልሉን የምርጫ ሕጎች ወደ ማጽደቅ እና ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን ወደ ማቋቋም ነው። የክልሉ ም/ቤት ክልላዊ ሕጉን ለማጽደቅ እንደ ሕግ መሠረት የተጠቀመው ከጉዳዩ ጋር እምብዛም ቀጥተኛ ግኑኝነት የሌለውን ‘ራስን በራስ የማስተዳደር መብት’ ነው። ይህ መብት በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት በግልጽ ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠን ሥልጣን በመተላለፍ አንድ ክልል የራሱን የምርጫ ሕግ ለማውጣት ሥልጣን ይሰጠዋል ማለት ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይሆንም።እንደዛም ሆኖ የትግራይ ክልል መንግሥት መብቱን ለመከራከሪያነት ከመጠቀም ባለፈ በርግጥም  ዓላማው የክልሉን ሕዝቦች (ነዋሪዎች) ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማክበር ወይም ማስከበር አለመሆኑን ለመረዳት ምርጫው የሚደረገው ለክልሉ ም/ቤት ብቻ መሆኑን በማየት መገንዘብ ይቻላል። ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት አኳያ ጉልህ ሥፍራ ያላቸው የታችኛው አስተዳደር አካላትን (ማለትም የዞን እና ወረዳ ም/ቤቶችን) በተመለከት የሚደረግ ምርጫ የለም።

የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ ምን ሊያስከትል ይችላል?

የፌዴሬሽን ም/ቤት ያሁኑን ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ቀደም ሲል በአፈጉባዔው በኩል ለትግራይ ክልል ም/ቤት በጻፈው ማሳሰቢያ ክልሉ የጀመረውን የምርጫ እንቅስቃሴ ኢ-ሕገመንግስታዊነት ጠቅሶ ድርጊቱ እንዲቆም ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። ያም ብቻ ሳይሆን ማሳሰቢያው እንዲሁም የፌዴሬሽን ም/ቤት አገር አቀፍ ምርጫን ለማራዘም ያሳለፈው ውሳኔ በትግራይ ክልል የማይከበር ከሆነ የፌዴሬሽን ም/ቤቱ በሕገመንግሥቱ እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት በክልሎች ጣልቃ የመግባት ሥልጣኑን ተግባራዊ  እንደሚያደርግም አሳስቦ ነበር። የትግራይ ክልል ም/ቤት በበኩሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባዔ ሥልጣኑን አላግባብ እንደተጠቀመ ገልጾ በአጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ ጣልቃ የሚገባበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ምላሽ ሰቷል።

እንግዲህ ያሁኑ የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ ቀደም ሲል ለክልሉ ከተሰጠው ማሳሳቢያ አንጻር አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ውጤቱም በዛው ደረጃ ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ውጤቱም የሚታየው በትግራይ ክልል ምርጫ የሚመረጠው ‘አዲስ’ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ ይሆናል። የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ የመጀመሪያ ውጤትም ይህንን ‘አዲስ’ ክልላዊ መንግሥት ኢሕገመንግሥታዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ በክልሉ በሚደረገው ምርጫ የሚመሠረት ማንኛውም መንግሥት “ሕገወጥ” ነው የሚሆነው። ይኼ ምርጫው ሕጋዊ ካልሆነ በምርጫው የሚመሠረተው ቀጣይ መንግሥትም ሕጋዊ አይሆንም ወይም ህገወጥ ነው ከሚል አመክዮ የሚመነጭ ነው። በዚህ መሠረት በቀጣዩ ምርጫ አሸናፊው ህወሓት ራሱ ቢሆንም እንኳ የሚመሠረተው አዲስ ክልላዊ መንግሥት ኢ-ሕገመንግሥታዊ መሆኑን አያስቀርለትም። እዚህ ጋር ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድ በምርጫው የሚያሸንፈው ህወሓት ከሆነ ችግር የለውም ያሉት ነገር ሕገመንግሥታዊ መሠረት እንደሌለው ልብ ይሏል። ምናልባትም ጠቅላይ ሚንስትሩ በምጸት ሊናገሩ የፈለጉት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ትርጉም የለሽ ነው የሚለውን ይመስላል።

ምርጫው፣ ሂደቱ እና ውጤቱ ኢሕገመንግሥታዊ በመሆኑ “እንዳልተደረገ ይቆጠራል” የሚለውን ውሳኔ ተከትለን ከሕግ አንጻር ሊያስከትል ከሚችላቸው ውጤቶች መካከል የመጀመሪያው የፌዴሬሽን ም/ቤት በቀጣይ የክልሉን አሥተዳደር በተመለከት ሊያሳልፍ የሚችለው ውሳኔ ነው። የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት “ሕገመንገሥቱን ወይም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚድረግ ድርጊት ካለ” በሕጉ የተቀመጡትን ሥርዓት ተከትሎ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሊወስዳቸው ከሚችላቸው እርምጃዎች መካከል የክልሉን ም/ቤት እና የክልሉን የሕግ አስፈጣሚ አካል ማገድ ይገኝበታል። እገዳውን ተከትሎም ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ሊወስን ይችላል። በርግጥ ይህ የሕግ ሂደት በመርህ ደረጃ ታሳቢ የሚያደርገው ሕጋዊ የሆነን ክልላዊ መንግሥት በመሆኑ በትግራይ ክልል ‘አዲስ’ የሚመሠረተው መንግሥት በዚህ ሂደት ሊታገድ አይችልም የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። በሌላ በኩል ምርጫውም ሆነ ውጤቱ ሕጋዊ ውጤት የለውም ከተባለ ደግሞ በክልሉ ሕገመንግሥታዊ መሠረት ያለው ያሁኑ ክልላዊ መንግሥት በሥልጣን እንዳለ ስለሚገመት እገዳውም እሱን የተመለከት ሊሆን የችላል።  የከልሉን መንግሥት በማገድ ጊዚያዊ አሥተዳደር መመሥረት ካለውም ሆነ በቅርብ ይኖራል ተብሎ ከሚገመት ተጨባጭ እውነታ አንጻር አዳጋች፣ ሊፈጸምም የማይችል እንደሆነ መገመት ከባድ አይደለም።

ሌላው ምርጫውን ተከትሎ በክልሉ የሚቋቋመው ‘አዲስ’ መንግሥት ኢሕገመንግሥታዊ ነው ከተባለ በሌላ አነጋገር ክልሉ ሕጋዊ መንግሥት የለውም ማለት ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ ክልሉን በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥትም ይሁን ከሌሎች ክልላዊ መንግሥታት ጋር ህጋዊ ግንኙነት ሊኖረው የሚችል መንግሥት የለም ማለት ይሆናል። ይህም በመንግሥታት መካከል የሚኖረውን ግንኙነተ ከማቋረጥ አልፎ በክልሉ ‘አዲስ’ የሚዋቀረው መንግሥት ህጋዊ ሰውነት ስለማይኖረው ከማናቸውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር የክልሉ መንግሥት ሊያደርግ የሚችለውን ማንኛውንም ህጋዊ ግንኙነት በሙሉ ሊያቋርጥ ይችላል። ይኼ ሊያስተጓጉል ከሚችላቸው ግንኙነቶች ምካከል አንደኛው እና ዋነኛው ለክልሉ መንግሥት በፌዴራል መንግሥት የሚመደብ ቀጥተኛ እና ድጎማ በጀት ነው።

ሌላኛው ምርጫውን ተከትሎ ‘አዲስ’ ክልላዊ መንግሥት ሲቋቋም የፌዴሬሽን ም/ቤት ከሕግ አንጻር ሊወስድ ከሚችላቸው እርምጃዎች መካከል ክልሉ በፌዴሬሽን ም/ቤት ያለውን ተሳትፎ ሊያግድ መቻሉ ነው። ሕገመንግሥታዊ ክልላዊ ም/ቤት የለም ከተባለ እሰከ አሁን ባለው አሠራር መሠረት ክልሉን በፌዴሬሽን ም/ቤት የሚወክሉ አባላትን ሊመርጥ የሚችል ክልላዊ ም/ቤት አይኖርም ማለት ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ ክልሉን አሁን በፌዴሬሽን ም/ቤት የሚወክሉ ግለሰቦችን በአዲስ መተካት ግዴታ ባይሆንም ነገር ግን ‘አዲስ’ የሚመሠረተው የትግራይ ም/ቤት አዲስ የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላትን የሚመርጥ ከሆነ ወይም ወደፊት የአሁኑ የፌዴሬሽን ም/ቤት ጊዜውን ሲጨርስ እና አዲስ ም/ቤት ሲቋቋም ጉዳዩ መነሳቱ የማይቀር ይሆናል።

በመጨረሻም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተመራጭ መፍትሔ ያልሆነ ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት የማያስችል ቢሆንም በሕግ ደረጃ የፌዴሬሽን ም/ቤት ካሉት ሥልጣኖች አንደኛው በአዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ሲኖር የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚያዝበት ሥርዓት ነው። ጣልቃ የመግባት እርምጃ የፌዴሬሽን ም/ቤት ወይም ሌላ መንግሥታዊ አካል ጉዳዩን አጣርቶ በርግጥም “ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል” አደጋ መኖሩን ሲያረጋግጥ እና ችግሩ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት መንገድ የሌለ መሆኑ ሲርጋገጥ ብቻ የሚወሰድ ነው። በነገራችን ላይ ጣልቃ መግባት ማለት የግድ ከአንድ ክልል ጋር ጦርነት መግጠም ማለት ላይሆን ይችላል። የሕጉ ዓላማም ይኼ አይደለም። እንደ ሁኔታው የፌዴራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማሠማራትን ቢያካትትም ዓላማው ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል የተሣተፉ የመንግሥት አካላትን ለሕግ ማቅረብ እና ችግሩ በተከሰተበት ክልል መደበኛ የመንግሥት ሥራ እንዲጀመር ማድረግ ነው። ምንም እንኳን በሕጉ የተቀመጠው ሥርዓት ተሟልቶ ባይተገበርም ከዚህ ቀደም የፌደራል መንግስት በሶማሌ ክልል ጣልቃ የገባበትን ሁኔታ ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

ሳይቃጠል በቅጠል

ከላይ የዘረዘርኳቸው ሁኔታዎች የፌዴሬሽን ም/ቤትን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ከሕግ አንጻር ወደፊት በትግራይ ክልል መንግሥት ላይ የፌዴራል መንግሥት ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎችን ለማመልከት የቀረቡ እንጂ እነዚህ እርምጃዎች ቢወሰዱ በተጨባጭ ችግሩን ለመፍታት ያላቸው ፋይዳ እምብዛም እንደሆነ መገመት ይቻላል። በአቢይ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀጠለውን መካረር መነሻ አድርገን በተለይ ደግሞ ህወሓት የራሱን ከማዕከላዊ መንግሥት መገፋት የክልሉ ሕዝብ እንደተገፋ አድርጎ በማቅረብ በክልሉ ሕዝብ እና በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ የፈጠረው የመበደል እና የመገፋት ስሜት በቀጣይ በማዕከላዊ መንግሥት የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖረው ያደርጋል። ይህም ማለት በቀታይ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሊደርስ የሚችለው ውሳኔ ሕገመንግሥታዊነት ላይ ጥያቄ ባይነሳ እንኳ በተግባር ግን በትግራይ ክልል ሕዝብ ዘንድ ውሳኔው የሚፈጥረውን ሥሜት ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ከዚህም አንጻር ይመስላል የፌዴሬሽን ም/ቤት ለክልሉ ሕዝብ ክብር ያለው መሆኑን በመግለጽ “ህገወጥ አካላት በሚፈጽሙት ድርጊት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም” የሚል በመግልጫው ያካተተው። ነገር ግን ከመግለጫ ባለፈ ም/ቤቱም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ማናቸውም የሚወሰኑ ውሳኔዎች ዓላማቸው ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን መሠረታዊ ጥቅም ለማስከበር ያለመ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

ሌላኛው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ የክልሉ መሪ ፓርቲ ያለ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ያለ አውዱ በመለጠጥ ለፖለቲካ ዓላማ ሲባል ብቻ በክልሉ ሕዝብ ዘንድ እያሰረጸ የሚገኘው “የዲፋክቶ ስቴት” ጉዳይ ነው። ከታሪክ እና ከአለም አቀፍ ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ዲፋክቶ ስቴት የመሆን ፍላጎት መነሻው ፖለቲካዊም ይሁን ተጨባጭ የሕዝቦች መበደል ሁኔታው አንድን ሀገር የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል የሚባል አይደለም። ጥያቄው ግን ገፊ ምክንያት የሚያገኘው አና ከፍ ብሎ ለሃገር ፈተና ወደ መሆን የሚሸጋገረው መንግሥት ጥያቄ እንዳይነሳ በሚወስዳቸው አግባብነት የሌላቸው እርምጃዎችም ጭምር ነው። ይህንን ከወቅታዊው የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ችግር አንጻር ከመዘንነው ማዕከላዊው መንግሥት ላይ ትልቅ ሃላፊነትን የሚጥል ሆኖ እናገኘዋልን። ሕጋዊ እርምጃዎች የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚያገለግሉትን ያህል ባለማስተዋል እና ሴራ ተጠልፈው ሃገርን ከባድ መስዋዕትነት እንዳያስከፍላት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሁሉ በጥልቀት የታሰበባቸው፣ ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኙ እና ሀገርን ከጥፋት የሚያድኑ መሆን አለባቸው። AS

____________________________________________//________________________________


የአርታኤው መልእክት: ማርሸት ሙሀመድ ሀምዛ በInstitute of International and Development Studies, Geneva, የPhD ተመሪ ናቸው:: ፀሀፊውን ከታች በተጠቀሰው ኢሜል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡ marishetm@yahoo.com.

Show More

Related Articles

Back to top button