ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከሶማሊያዋ ግዛት ፑንትላንድ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. :- የሱማሊያ ግዛት ያሆነው የፑንትላንድ አስተዳደር ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በጋሮዌ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአስሸኳይ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

የጋሮዌ ከተማ ከንቲባ  አብዲቃዲር ሞሃመድ ሞሃሙድ ጌዲ የኢድ አል አድሃ በዓል በተከበረበት ቀን ባደረጉት ንግግር ነው ኢትዮጵያውያኑ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰቡት።

“ትዕዛዙን ተግባራዊ በማያደርጉ ኢትዮጵያውያን ላይ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል” ሲሉ ከንቲባው መግለጻቸውን የፑትላንዱ ጋሮዌ ኦንላይን የዜና አውታር ዘግቧል። 

ውሳኔው የተላለፈው “በህግ-ወጥ መንገድ በግዛቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መበራከቱና የስራ ዕድል እየተሻሙ በመሆኑ ነው” ሲል ዘገባው አስነብቧል።

አዲስ ስታንዳር ያነጋገራቸው የፑትላንድ ነዋሪዎች፤  የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የስደተኞች ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከጋሮዌ ከተማ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መተላለፉን አረጋግጠው በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በሶማሊ ላንድ መካከል የተፈረመውን የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያውያን ላይ ማስፈራሪያ፣ ጥቃት እንዲሁም በተለያዩ ታጣቂዎች ግድያ ሲፈፀም መቆየቱን ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ነዋሪ ገልፆ የአሁኑ ሁኔታም አስፈሪ ነው ብሏል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈፀም የቆየውን ጥቃት እንዲቀረፍላቸው ለሶማሊያ መንግስትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ያስታወሰው ነዋሪው አሁንም ችግሮች መቀጠላቸውን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማስፈራሪያ እና ጥቃጥ እየደረሰባቸው መሆንን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወቃል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ስታንዳርድ በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት ላቀረበው ጥያቄ ተቋሙ ጥቃቶች መፈፀማቸው መረጃው እንደደረሰዉ በመግለፅ የስደተኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከሶማሊያ መንግስት አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button