በይስሓቅ እንድሪስ @EndrisYish13226
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2/ 2016 ዓ/ም፦ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን የሚያስችል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነዳዴዎች ላይ እርመጃ እየወሰደ ቢሆንም በመዲናዋ የሚገኙ ሻጮች በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማደረጉን ቀጥለዋል።
ከሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የትግበራ ሂደት መጀመሯን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ አገሪቱ ከቋሚ የምንዛሬ ተመን ሥርዓት ወደ ገበያ-መር የምንዛሬ ተመን ሥርዓት መሸጋገሯን አስታውቋል።
ውሳኔውም ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ማግስት ጀምሮ የብር የመግዛት አቀም እየተዳከመ የዶላር፣ ፓውንድና የመሳሰሉት የመገበያያ ገንዘቦች የምንዛሬ ተመን እየጨመር መጥቷል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን መግዣ ዋጋ ከ54 ብር ወደ 100 ብር በላይ እንዲያሻቅብ ሆኗል።
ይህን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ መሆኑን አዲስ ስታንዳርድ በአዲስ አበባ በሚገኙ ተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ባደረገው ቅኝትና ካነጋገራቸው ሻጮችና ሸማቾች መረዳት ችሏል። የዋጋ ጭማሪው የተስተዋለባቸው ምርቶች ከውጭ በገቡ እንዲሁም በአገር ውስጥ በተመረቱ ላይ ሲሆን በዋናኝነት ዘይት፣ ስኳርና ሽንኩርት ምርቶች ላይ ጭማሪ ተደርጓል።
ይህ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ያለው መንግስት ምርት ባከማቹና የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እያስታወቀ ባለበት ወቅት ነው። ባሳለፍነው ሳምንት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር መመሪያን እንደ ምክንያት በመውሰድ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርትን ያለአግባብ ባከማቹ ከ700 በላይ የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውንና 33 ነጋዴዎች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለትም በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዲፈጠር ምርት ደብቀው በተገኙ ህገወጦች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርት በመደበቅ ተግባር ላይ የተገኙ ከ7 ሺ በላይ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ በመርካቶ ገበያ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ነጋዴ በጅምላ ርክክብ ዘጠኝ መቶ ብር የነበረው ባለ አምስት ሊትር ዘይት አሁን ላይ እስከ 1120 ብር እንደሚረከቡት እና እስከ 1200 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በኪሎ መቶ ብር የሚረከቡት ስኳር አሁን ላይ እስከ አንድ መቶ አስራ ስድስት ብር መድረሱን ገልጸዋል።
በመገናኛ ሾላ ገበያ ሲሸምቱ አዲስ ስታንዳርድ ያገኛቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ከዚህ በፊት 1000 ብር የነበረው ዘይት አሁን ላይ እስከ 1500 ብር እየተባለ መሆኑን ገልጸዋል።
“እኔ አሁን የ1800 ብር ደመወዝተኛ ነኝ። ልጅ አለኝ። በጽዳት ስራ ነው የምተዳደረው። የኑሮ ውድነቱ ከብዷል መኖር አልቻልኩም። ወደፊት የምንበላው ነገር የምናገኝ ሁላ አይመስለኝም። “ሲሉ በምሬት ነዋሪዋ ገልጸዋል።
አክለውም “ነጋዴ ነው የጎዳን። ይሄንንም ተመስገን ብላችሁ ኑሩ ከዚህ የባሰ ይመጣል ይሉናል። እርስ በእርሳችን ነው የምንበዳደለው።” ብለዋል።
በቡልቡላ የገበያ ስፍራ ሲሸምቱ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው ህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን ይገልጻሉ። “ህዝቡ ከዚህ በፊት ዶላር ላይ ጭማሪ ሲደረግ ወይም ሃገሪቷ ውስጥ የሆነ ኮሽታ ሲኖር ነጋዴው የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግ በመሆኑ የአሁኑ ሁኔታም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል” ሲሉ አስረድተዋል።
አክለውም “አሁን ላይ ሱቅ ስንገበያይ ዘይት እንደድሮው ከመደርደሪያ ላይ እያወረዱ ሳይሆን የሚሰጡን ከደበቁበት ሰወር ካለ ቦታ ነው የሚያወጡት። ለዕይታ ብቻ የሚሆን መደርደሪያው ላይ አንድ ሁለት ያስቀምጣሉ። እና ከሚረከቡበት ቦታ ነገ ጨምሮ ቢጠብቀኝስ በማለት አሁን እጃቸው ላይ ያለውን ምርት ይደብቃሉ።” ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በቡልቡላ አካባቢ በሚገኙ የገበያ ስፍራዎች ባደረገው ቅኝት በዘይት እና በስኳር ምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ለመረዳት ችሏል። ኦማር የተሰኘው የምግብ ዘይት ላይ 100 ብር ጭማሪ አሳይቶ በ1200 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ከዚህ በፊት በኪሎ 120 ብር የሚሸጠው ስኳር አሁን ላይ የአስር ብር ጭማሪ አሳይቶ130 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
አንደኛ የሚባለው ነጭ ጤፍ በኪሎ ሲሸጥበት ከነበረው 140 ብር የአምስት ብር ጭማሪ አሳይቶ 145 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ጥሬ ስንዴ በኪሎ እና የተፈጨ ዱቄት ላይ የዋጋ ጭማሪ አለመታየቱ ተገልጿል። አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ ምርቶቹን ከሚያመጡባቸው ስፍራዎች የታየው ጭማሪ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በመዲናዋ ሻጮች በርካቶች ሽቀጦችኝ በማከማት ላይ የሚገኙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በጉለሌ ክ/ከተማ ከ 800 ሺህ የምግብ ዘይት ምርት “ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች” ተወርሶ ለሸማቾች መህበር መከፋፈሉ ተገልጿል። ማሻሻያውን ተከትሎ “ጥቂት ነጋዴዎች” መሰረታዊ የፍጆቻ እቃዎች ላይ ሕግ ወጥ ተግባር እየፈፀሙ ነው ተብሏል።
የክፍለ ከተማው ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ክብረት፤ የምግብ ዘይቱ የተያዘው ሕገወጥ ነጋዴዎች ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርቱን በድብቅ አከማችተው በመገኘቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሻሸያውን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ እየታየ የሚገኘውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትሩ አቶ ካሳሁን ጎፌ 14 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተገዝቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊከፋፈል መዘጋጀቱን ያስታወቁ ሲሆን ይህ እርምጃ ገበያውን ለማረጋጋት እና ያለውን የምርት ፍላጎት ለማሟላት ያለመ መሆኑ ተናግረዋል።
የአትክልት ገበያው ውሎ
አዲስ ስታንዳርድ ቅኝት ባደረገባቸው አከባቢዎች የአትክልት ገበያው ላይ እምብዛም ያስተዋለው ለውጥ ባይኖርም ሽንኩርት ላይ ግን የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ለመታዘብ ችሏል። በጊዮርጊስ የገበያ ማዕከል አከባቢ አትክልትን የሚሸጡ ነጋዴዎች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ በበኩላቸው የሽንኩርት ዋጋ ማሻቀቡን አረጋግጠዋል። “ሽንኩርት ላይ በዚህ ሳምንት ጭማሪ አለ። በፊት ጥሩ የሚባለው ሽንኩርት ሃምሳ ወይም ሃምሳ አምስት ብር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዘጠና እና 100 በር ድረስ እየተጠራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን የዋጋ ጭማሪው ከዶላር ጋር የተያያዘ እንደማይሆን ምልከታቸውን ገልጸዋል።
“ብዙ ምርት እየገባ አይደለም። አብዘሃኛውን ጊዜ በክረምት ወቅት የሽንኩርት ምርት ይቀንሳል። በዚህ ወቅት የሚያረጋጉት ከውጭ የሚመጡት ከሱዳን እና ጅቡቲ የሚመጡ ምርቶች ነበሩ አሁን ላይ እነሱ ባለመኖራቸው ምርቶቹ ከውስን ቦታዎች ስለሚመጡ ገበያው ላይ ጭማሪ ያመጣሉ። ይሄ ከዶላር ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም። ምክንያቱም ከዶላር ጋር የተያያዘ ቢሆን ኖሮ ሌሎች እንደ ቲማቲም እና ድንች ያሉ ምርቶች ላይ ጭማሪ ይታይ ነበር።” ሲሉ አስተያየታቸውን አክለው ገልጸዋል።
በቀበና አከባቢ ነዋሪ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸው በወትሮው ቀበና መድሃኒዓለም አከባቢ ቅዳሜና እሁድ ድንኳን ጥለው ሲሸጡ የነበሩ ነጋዴዎች ባሳለፍነው ሳምንት ምርት አለማምጣታቸውን የገለጹ ሲሆን “ለዚህም ምክንያት ብለን ስንጠይቅ ዶላር ጨምሮ ነው ይሉናል።” ሲሉ አስረድተዋል።
መንግስት የቁጥጥር ትኩረቱን ለምግብነት በሚውሉ ሸቀጦች ላይ ያደረገ ቢሆንም በሌሎች ምርቶች ላይም ጭማሪ እየተደረገ ይገኛል።
ፒያሣ አከባቢ በኮንስትራክሽን ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ነጋዴ ግለሰብ፤ የእቃዎች እጥረት መኖሩን አረጋግጠው ነገር ግን በዶላር መጨመር ምክንያት የተጋነነ ጭማሪ እንዳላስተዋሉ ገልጸዋል።
“የዋጋ ጭማሪ ጄኔነተሮች ላይ ተደርጓል። ቢያንስ ከዚህ በፊት 80 ሺህ የነበረው ጄኔነተር አሁን ላይ 85 ሺህ እየተሸጠ ይገኛል። ነገር ግን ይህ የሆነው በዶላር ምክንያት አይመስለኝም። የእቃዎች እጥረት በመኖሩ የተፈጠረ እንደሆነ ነው የማምነው። አጠቃላይ ገበያው ተቀዛቅዟል። ሰው መሰረታዊ ነገር ላይ መሯሯጥ ጀምሯል መሰለኝ ገዥም የለም።” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ “ነገሮች እስኪረጋጉ” በሚል እቃዎችን የማስቀመጥ እና የመደበቅ ሁኔታዎች እንደሚታዩ አክለው ገልጸዋል።
ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ የነበራቸው አንድ ነዋሪ በበኩላቸው መንግሥት ፖሊሲውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ነበረበት ሲሉ ይገልጻሉ። “ማሻሻያው የተለያዩ በጎ ጎኖች ይኖሩታል፤ ነገር ግን ዶላር ጨመረ በሚል የግንዛቤ ማነስ በዕቃዎች ላይ የሚደረገው የተጋነነ ጭማሪ ህዝቡን እያማረረው ይገኛል።” ሲሉ የገለጹት ነዋሪ አክለውም መንግሥት የቁጥጥር ስርዓቱን እንዲያጠናክር እና ገበያ የማረጋጋት ስራውን እጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
“ንግድ የራሱ የሆነ ትስስር አለው።” በማለት የገለጹት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው “ዘይት ከጨመረ የሽንኩርት ነጋዴው ዘይት የሚገዛበት ገንዘብ ስለማይኖረው ሽንኩርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋል። ዞሮ ዞሮ ዕዳው ሁሉ ህዝቡ ላይ ይወድቅበታል።” ሲሉ የታዘቡትን ተናግረዋል። አክለውም መንግሥት ለኑሮ ውድነቱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል።
የሙህራን ማሳሰቢያ
በቅርቡ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደገለጹት የኢኮኖሚ ማሻሻያው በህጋዊው የምንዛሬ ተመን እና በጥቁር ገበያው መስመር መካከል ያለውን ልዩነት ሊያጠብ እንደሚችል ጠቅሰው ነገር ግን ከሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አንጻር ግን በኑሮ ውድነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር አሳስበዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ መርድ የብር ዋጋ ማሽቆልቆሉ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ ወጪን እንደሚያከትል ገልጸዋል። ”በተለይም አስፈላጊ የሆኑ እቃዎች ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ በሆኑበት ሀገር ለንግድ ድርጅቶች እና ሸማቾች ስጋት ሊፈጥር ይችላል” ብለዋል።
ባለሙያው አክለውም “አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቋሚ ገቢ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሰዎች በቁጥር ከፍተኛ በመሆናቸው ይህ የዋጋ ንረት በኑሮ ውድነት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ወደ ለሌሎች ማህበረ-ፖለቲካዊ ቀውሶች ሊያዳርግ ይችላል” ሲሉ አሳስበዋል::
በተጨማሪ ነጋዴዎችም ሸቀጦችን በመደበቅ በገበያው ላይ ሰው ሰራሽ የሆነ እጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል:: ይህም የዋጋ ንረትን በማባባስ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን አቅርቦት እንደሚያስተጓጉል እና በህዝቡ ላይ ግልጽ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ሸክም እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ባለሙያው አክለው ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ክቡር ገና ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ መንግሥት ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጨረሻ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ሲሉ ይገልጻሉ:: ሊኖሩ የሚችሉ ጥቅሞች ማለትም እንደ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መስፋፋት፣ ብድር፣ የገበያ ዕድገት እና የኢንዱስትሪ ድጋፍ ዕድገቶች በረጅም ጊዜ ውስጥ ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል::
አክለውም” እነዚህ ጥቅሞች ሊገኙ የሚችሉት ወሳኝ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ነው::” ሲሉ አበክረዋል::
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሬ ተመን ሥርዓት ከመተግበሩ በፊት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና አንዳንድ ፖሊሲዎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ::
አክለውም በ1970ዎቹ ውስጥ ቻይና ከተጠቀመችው ስትራቴጂ ጋር በንጽጽር ሲታይ ሀገሪቱ በወቅቱ ሆን ብላ ገንዘቧን ውድቅ በማድረግ በዓለም ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት አሳድጋ የነበረችው ባላት ጠንካራ የማምረት አቅም ተደግፋ ነበር ሲሉ አስረድተዋል::
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ባላት ደካማ የኢንዱስትሪ እድገት እና አነስተኛ የግብርና ምርት የተነሳ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ተግዳሮት ሊያጋጥማት ይችላል ሲሉ አብራርተዋል::
አክለውም “ኢትዮጵያ የማምረት አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ ካላሳደገች እና እየተከሰቱ ያሉ ማህበራዊ: ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ካልፈታች በስተቀር በቅርቡ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የመግዛት አቅምን ሊቀንስ እና ድህነትን ሊያባብስ ይችላል::” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አስ