ፖለቲካማህበራዊ ጉዳይርዕሰ አንቀፅ

ርዕሰ አንቀፅ፡ የምግብ እርዳታ ስርቆትን ለማውገዝ፣ እርዳታን ማቋረጥ ተጎጂዎችን ሁለት ጊዜ መቅጣት ነው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞት ተጋርጦባቸዋል፣ ሊታደጉ ይገባል!

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም፡- ብልጽግና መራሹ የለውጥ ሀይል ኢትዮጵያን ተረክቦ ማስተዳደር ከጀመረበት መጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በርካታ አሰቃቂ ሰብአዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል። ጦርነት ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ጥቃቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ የሀገሪቱ በሮች ለውጭ ሀይሎች ክፍት እንዲሆኑ በማድረጉ ቅጥረኞች የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ አስችሏል።

በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በከተማና በገጠር በሚኖረው ህዝብ ኖሮ ላይ ጫና ከማሳደር ባለፈ የረሃብ ስጋት እንዲያጠላ ምክንያት ሆኗል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ አለምን ስጋት ላይ ጥሎ በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ማግስት የተፈጠሩ ከመሆናቸው ባለፈ ጠ/ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ለሶስት አሰርት አመታት የተገነባውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሽባ ያደረጉ ክስተቶች ሆነዋል።

እነዚህ ችግሮች ጥሮ ግሮ የሚኖረውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከእርዳታ ጠባቂነት ውጪ ሌላ መትረፊያ መንገድ እንዳይኖራቸው አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ለተረጂነት የተጋለጡ ሆነዋል።

ለዚህም ነው በከፍተኛ ደረጃ በተደራጀ መልኩ ለተረጂዎች ታልሞ የቀረበ የምግብ እርዳታ መሰረቁ አለም አቀፍ ትኩረትን የሳበው እና ድንጋጤን የፈጠረው። ይህ አሰቃቂ ተግባር በርካታ ተዋንያኖች ያሉት ሲሆን ከመንግስት ባለስልጣናት እና እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ባሉ አካላት የተፈፀመ ነው። ይህም ከሰብአዊ ረድኤት ድርጅቶች አፋጣኝ ምላሽ ይሻል።

በዋና ዋናዎቹ የረድኤት ድርጅቶች ማለትም የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የአለም የምግብ ፕሮግራም በኩል የእርዳታ ስርጭቱ እንዲቋረጥ መወሰኑ ይህ ብልሹ ተግባር በፍጥነት እንዲታረም ለማድረግ ነው፡፡ ደካማ አስተዳደር፣ ተደጋጋሚ ጦርነት እና የላሸቀ ኢኮኖሚ በተላበሰች የአሁኗ ኢትዮጵያ ለተረጂዎች የሚቀርብ እርዳታ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ከተስፋ መቁረት የተነሳ ለስርቆጥ እንደሚጋለጡ የሚገመት ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን የቁጥጥር እና የተጠያቂነት ስርዓት ደካማ መሆን ነው። በሌላ አገላለጽ ብልሹ የእርዳታ ስርጭት አስተዳደር መኖር ማለት ነው።

እነዚህ ምክንያቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ አስተዳደር ስርዓት ተንካራ ተደርጎ እንዲቆጠር ካደረጉት ምክንያቶች ፍጹም ተቃራኒ ምክንያቶች ናቸው። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ለበርካታ አሰርት አመታት ተጠቂ ነች። ይህም መንግስት እና የረድኤት ድርጅቶች በእርዳታ ስርጭት ትግበራ በቂ ልምድ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። በእያንዳንዱ ድርቅ የሚያጋጥሙ ነገሮችን ለመወጣት የሚያስችል ስትራቴጂዎችን በማውጣት ልምድ ከማካበታቸውም ባለፈ በቂ ባለሞያዎችን ለማፍራትና በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቆጣጠር  አስችሏቸዋል።

በኢህአዴግ መራሽ መንግስት  ወቅት የምግብ ስጋትን በሀገር ደረጃ ለመመከት ጠንካራ ቁርጠኝነት አሳይታለች። የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በጠበቀ መልኩ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ በመስራት የምግብ አቅርቦት ችግርን፣ ስርጭቱን ለማሳለጥ እና ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ትብብርም ነው ሀገሪቱ ከአለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የተሳካ የሎጂስቲክ እና የእርዳታ አቅርቦት አስተዳደር እንድትመሰርት የረዳት። ይህም፣ ምንም እንኳን አንዳንድ ብልሹ ተግባራት የነበሩት ቢሆንም ተደጋጋሚ የእርዳታ ምግብ ስርቆት እንዳይፈጸም አስችሏል፤ በተመሳሳይም የምግብ አቅርቦቱ ለታለመለት አላማ መዋሉንም ለመከታተል አስችሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ምግብ የማግኘት መብት መሰረታዊ የሰው ልጅ መብት ከመሆኑ ባለፈ አለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ እና አለም አቀፍ መርህ በመሆኑ ነፃ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህንን በጣሰ መልኩ እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ያላቸው አካሄዶች በተለይም ለቅድመ ማስጠንቀቂያነት የሚያገለግሉ የምግብ አቅርቦት ችግር ትንበያ ማከናወን፣ ለተጎጂዎች የሚቀርብ የእርዳታ ምግብ ስርጭትን ከአከባቢው ማህበረሰብ ባህል ጋር የሚጣጣም ትግበራ መፈጸም፣ የምግብ ችግርን ለመከላከል ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶች የግብርና፣ መሰረተ ልማት ግንባታ እና ቀጣይነት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚሉት ተግባራት ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ከግጭት ጋር በተያያዘ መልካም ተሞክሮ ያላት ተደርጋ እንድትቆጠር አስችሏል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር ባደረገችው ጦርነት በተለይም በጥቅምት 2013 ዓ.ም በትግራይ ተካሂዶ በነበረው እና ወደ የአማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦነርነት እንዲሁም በኦሮምያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ይህ አካሄድ ተጨናግፏል።

የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ በጦርነቱ ሳቢያ ተጎጂ ለሆኑ እና የሰብአዊ የምግብ እርዳታ ለሚሹ ዜጎቹ እርዳታ እንዳይዳረስ ሲያደርግ ተጠያቂ አልተደረገም።

ለምሳሌ ያክል በትግራይ ክልል በመንግስት እና አጋሮቹ፣ የኤርትራ መንግስትን ጨምሮ ለሁለት አመታት  ወደ ትግራይ ምግብ እንዳይደርስ ሲዘጉ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ምንም አይነት ተጽእኖ አልደረሰባቸውም። ይህም በርካታ ንጹሃን በረሃብ እንዲሞቱ ከማድረጉም ባለፈ የእርዳታ ስርጭት ላይ የነበረውን ስርዓት እንዲበላሽ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ለኢትዮጵያ የአረዳታ መግብ በመለገስ ታላቁን ድርሻ የሚይዙት ምዕራባውያን፣ ሆን ተብሎ የተፈጸመውን የምግብ አቅርቦት እገዳን ለማስቀረት ወሳኝ እርምጃዎች መውሰድ እየተገባቸው ዝም ብለው መመልከታቸው ዋጋ እንዳስከፈለ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ከነመንስዔው የሚያውቁት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የአደባባይ ሚስጥር ሁኗል። በአንጻራዊነት በኢትዮጵያ በመልካም ሁኔታ ይተገበር የነበረውን የእርዳታ ስርጭት አካሄድን እንዲበላሽ እና በግልጽ እየታየ እንዲኮታኮት ሆኗል።

ሀገሪቱ እዚህ ደረጃ እንዴት አንደደረሰች መረጃው ያላቸው እና ለዚህ ህትመት ሚስጥሮችን ያካፈሉን ሰዎች እንደገለጹልን ዋና ዋናዎቹ ለጋሽ ድርጅቶች በተለይም መሬት ላይ አቅርቦታቸውን የሚያዳርሱ እንዲህ አይነት እንዝላልነት እና እብሪት በታችኛው የእርዳታ አቅራቢ ሰራተኞች ታይቶ በምይታወቅ ደረጃ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽአ አላቸው።

ጉዳዩን እኛን ጨምሮ በበርካታ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየተዘገበ ባለበት ወቅት፣ የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) እና የአለም የምግብ ፕሮግራም ተጨማሪ ምርመራ እስኪካሄድ ድረስ የምግብ እርዳታ ማቅረብ አቁመናል ሲሉ ገልፀዋል።

ይህ ውሳኔያቸው ተግባራዊ ከተደረገ ሶስት ወራት አልፈዋል። በዚህም ሳቢያ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከኦሮምያ እስከ ትግራይ ከአፋር እስከ አማራ ክልል ያሉ ተጎጂ ሰዎች ህጻናትንና ነብሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ አይደለም።

በትግራይ ክልል ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችም አስከፊ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቁ ሰዎች መበራከታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።

ማህበራዊ ቀውሶች፣ አዳዲስ ግጭቶች መከሰት እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተስተዋሉ መፈናቀሎች ከከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ጋር ጠንካራ ትስስር የመፍጠር እድል አላቸው። ቅድሚ የሚሰጠው እና አጣዳፊ ጉዳይ ተደርጎ የማይወሰድ ከሆነ በረሃብ እና ባለመረጋጋት ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ሀገራት በሚሰደዱ ሰዎች ሳቢያ ከባቢያዊ እና አለምአቀፋዊ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።   

የኢትዮጵያ መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቹን በረሃብ ሳቢያ ከሚፈጠር ሞት፣ ከረሃብና ከተመጣጠነ ምግብ እጦት ባይታደግም፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚደርሰውን የምግብ እርዳታ በአስቸኳይ ወደነበረበት ለመመለስ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አብሮ ለመስራት መራራ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት።

በተመሳሳይ የምግብ አቅርቦት ቀውሱ ከፊላዊ ምክንያት ሀገሪቱ የገባችበት ጦርነት ከሆነ መንግስት እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ተፋላሚ ሀይሎች ዋነኛ የግጭቶቻቸውን መንስኤ በንግግር እንዲፈቱ ተጽእኖ መፍጠር ያስፈልጋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የምግብ አቅርቦት ስርጭትን ለማሳካት ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝነት አለው።

በየግዜው የሚከሰተውን የምግብ ችግር ለመቅረፍ ዘላቂ ልማት እና ቀጣይነት ያለው መፍትሔም መስጠት እኩል ትኩረት ሊደረግበት ይገባል። በሀገሪቱ በተሻለ ደረጃ ለአስርት አመታት ሲያገለግል የነበረውን የእርዳት ምግብ ስርጭት መንገድ እንዲበላሽ ምክንያት የሆኑ ሰዎችም ተጠያቂ መደረግ አለባቸው፡፡ ነገር ግን የእርዳታ ስርቆትን ለማውገዝ በሚል እርዳታን ማቋረጥ፣ ተጎጂዎችን ሁለት ጊዜ እንደመቅጣት ነው። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button