ማህበራዊ ጉዳይርዕሰ አንቀፅ
በመታየት ላይ ያለ

ርዕስ አንቀጽ: በፈተና ውጤት ላይ ብቻ ማተኮር የኢትዮጵያን የትምህርት ስርአት ወደ ቀውስ የሚከት ነው፣ ተሻጋሪ ምልከታ ያሻል

አዲስ አበባ – ላለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል ይፋ የተደረገው መረጃ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በር የሚያንኳኳ እና ድንጋጤን የሚፈጥር ነው። መረጃው የሚያሳየው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሒወታቸውን በትምህርት አለም ማሰቀጠል የሚፈልጉ ተማሪዎች ህልማቸው እና ተስፋቸው መጨናገፉን የሚያትት መርዶ የያዘ ነው፤ ሁኔታው አብዘሃኛዎቹ ዳግም ወደ ትምህርት አለም እንዳይመለሱ በሚያደረግ መልኩ ቋጭቶታል።

እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለጸ ውጤቱ የመጣው የብሔራዊ ፈተናን ለማዘመን እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ እንዲሁም ኩረጃን ለማስቀረት በማለም አዲስ ያስተዋወቀው ጥብቅ ቁጥጥር የተሞላበት እርምጃ በመውሰዱ ነው።

በሁለቱም አመታት የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ ከመቶ በላይ በማመጣት ማለፍ የቻሉት ከስድስት በመቶ እምብዛም የማይበልጡት ናቸው፤ በቁጥር ሲሰላ ከጠቅላላ ተፈታኞቹ ፈተናውን በማለፍ ዩኒቨርስቲ የተቀላቀሉ 51ሺ 176 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

በግርድፉ ሲታይ አስደንጋጩ ውጤት የተመዘገበው ሚኒስቴሩ ኩረጃን ለማስቀረት በሚል በድፈረት የተገበረው ጥብቅ ቁጥጥር ያመጣው ይመስላል።

ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ የመጣውን የሀገሪቱን የትምህርት ስርአት ቀለል ባለ አገላለጽ በመቅረቡ ብዙዎች መታለላቸው አያስደንቅም፤ እንዲያውም ትምህርት ሚኒስቴር ኩረጃን ለማስቀረት ያወጀው ቅዱስ ጦርነት ተደርጎም ተወድሶበታል።   

በጉዳዩ ዙሪያ ቁልጭ ብሎ የሚሰማው ሙግት ሁለት መሰረታዊ የሆኑ አሳቤዎችን በማቻቻል ዙሪያ ነው፤ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የሚለው እና ትምህርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ብቻ መዳረስ አለበት የሚሉ።

ነገር ግን በተለየ ትኩረት ባለፉት አምስት አመታት በአሳሳቢ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የነበረውን የሀገሪቱን የትምህርት ስርአት በቅርበት ሲከታተል ለነበረ ሰው እውነታው ላያስገርመው ይችላል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በሀገሪቱ ሰላሳ ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ሂደት ውስጥ አልፈዋል፤ ከእነዚህ ውስጥም ከ130 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በየአመቱ የሀገሪቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይቀላቀላሉ። ኢትዮጵያ ለሁሉም ባይሆንም ለአብዘሃኛው ዜጎቿ ትምህርትን ተደራሽ በማድረጓ ስትወደስ ቆይታለች።  

ቁልጭ ብሎ የሚታየው ስጋት ሁለት መሰረታዊ የሆኑ በትምህርት ዘርፍ ያሉ እሳቤዎችን በማቻቻል ዙሪያ ነው፤ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የሚለው እና ትምህርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ብቻ መዳረስ አለበት የሚሉ።

መቀበል ያለብን፣ ኢትዮጵያ ከፈተኛ ቁጥር ያለው ያልተማረ ሰው ያለባት ሀገር ነች፣ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የነበረችው ኢትዮጵያ ብዙዎቹ ያላደጉ ሀገራት የሚያጋጥማቸው ፈተና እና ውጣ ውረድን ልታመልጥ አትችልም፤ በአለም ላይ እንዳጋጠመው ሀቅ ሁሉ በሀገሪቱ ትምህርት ተደራሽ የሆነው የጥራትን ጉዳይ በማቻቻል ነው።

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የነበሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብ እና መጻፍ አለመቻላቸው እጅግ እንዳስደነገጣቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል። ድንጋጤያቸው ቅቡል ነው፣ ነገር ግን ጉዳዩን አስመልክቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የተከተለው መንገድ እና ይበልጥ ያተኮረው ኩረጃን ማስቀረት ላይ መሆኑ ህዝቡ ዘርፈ ብዙ የሆነውን የትምህርት ችግር ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ እንዳይተኮር በማድረግ ማስቀየሱ ነው።

ባለፉት አመስት አመታት በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ የደረሰው የዘፈቀደ ውድመት፣ ለማሳየት ያክል በመላ ሀገሪቱ በጦርነት እና ወታደራዊ ግጭቶች ሳቢያ ዘጠኝ ሺ የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው በትምህርት ጥራት መጓደል ላይ ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ፖለቲከኞች በግልጽ ሊያነሱት አይፈልጉም። በእነዚህ ግዜያቶች የትምህርት ግብአቶች መጻህፍት እና የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ሆን ተብሎ እንዲወድሙ በከፍተኛ ሁኔታ ተደርገዋል።

በመላ ሀገሪቱ የተስፋፋው ጦርነት እና ግጭት በርካታ መምህራን እንዲሞቱ፣ አካላቸው እንዲጎድል ወይንም እንዲጠፉ ማድረጉ ትምህርት ቤቶችን ያለ መምህራን እንዲቀሩ አድርጓል። በሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ እውቀት ሊዘሩ የሚችሉ፣ እጅግ የሚፈለጉ፣ የሰለጠኑ እና ብቃት ያላቸው መምህራን ኢትዮጵያ በጦርነቶቹ አጥታለች።

የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የህዝቦች መፈናቀል እና የመደበኛ ትምህርት መቋረጥ በተማሪዎች ላይ በስነልቦና ይሁን በአካል ብቃት የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ግልጽ ነው። ይህም ቀጥተኛ በሆነ መልኩ በመላ ሀገሪቱ ለመጻኢው ትውልድ የመማር ማስተማር ሂደት የሚኖረው አስተዋጽኦ እና የሚያሳድረው ጠባሳ ከፍተኛ ነው።

ከሌሎች ችግሮች ባልተናነሰ ግምት ውስጥ ሊገባ እና መረሳት የለለበት ቀመር ሀገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግስት በትምህርት ዘርፉ የሚያፈሰው መዋዕለ ነዋይ በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱ የሚኖረው ወሳኝ ተጽእኖ ነው። ለመምህራን ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ለመፈጸም ዳተኛ መሆኑ እና አቅማቸውን ለማጎልበት የሚያስችል ወሳኝ ፖሊሲዎችን አለመከተሉ የመንግስትን አካሄድ አመላካች ናቸው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ የትምህርት ሂደት ላይ ተጽእኖ በሚፈጥሩ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉን የዳሰሰ ጥናት ማካሄዱ ወይንም አለማካሄዱ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያካሄደውን ጥናት ተንተርሰን ካየን 47ሺ የሚሆኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አራቱ ብቻ የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላሉ ብሏል። 86 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች የሆኑ ናቸው ሲል ገልጿል።

ሌላ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ አራተኛ የሚሆኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ብቻ ናቸው መመዘኛ ፈተና ያለፉት። የሀገሪቱ የትምህርት ስርአት በዚህ ደረጃ ከሆነ አግባብ የሚሆነው የትምህርት ስርአቱ ተበላሽቷል ማለት ሳይሆን ተንኮታኩቷል ነው።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በግልጽ የወቀሳው ተሸካሚ ተደርጎ የሚቀርበው የባለፈው መንግስት ይከተለው በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ማድረጉ ነው የሚል ነው።  ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ በቅርቡ ፓርላማ ላይ ቀርበው ገለጻ በሰጡበት እና ሁሉንም የተማሪ ቤተሰቦችን ጨምሮ በወቀሱበት ወቅት በምክንያትነት አቅርበውታል። ጉዳዩን በማሳነስ እና በማጥላላት የዚህ አይነት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ እና በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር በሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በምክረ ሃሳብ ደረጃ እንደተነገረው በቂ ምርመራ ማድረግ የችግሩን ስር መሰረት መለየት ያስፈልጋል።

በቅርቡ ዩኒሴፍ ያሳተመውን መረጃ በምሳሌነት እናቅርብ፣ ዩኒሴፍ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በግጭት እና ውድመት ሳቢያ ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው። በሀገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 8ሺ 552 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ወድመዋል። የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ኩረጃን ለማስቀረት ባካሄደው ቅዱስ ጦርነት እነዚህን አሳሳቢ ችግሮችንም ግምት ውስጥ ማስገባቱን ወይንም አለማስገባቱ ግልጽ አይደለም።

እነዚህ ችላ ልንላቸው የማንችላቸው እውነታዎች የሀገሪቱ የትምሀረት ስርአት በአጠቃላይ የተወሳሰበ መሆኑን ያሳያሉ እንጂ ሚኒስቴሩ በተሳሳተ መንገድ ትኩረት እንዳደረገበት የኩረጃ ቸግር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም።

ትምህርት ሚኒስቴር በቁንጽል ኩረጃ ላይ ብቻ ቅዱስ ጦርነት ማወጁ የሚፈጥረው የአዙሪት ተጽእኖ በርካታ ነው፤ ሀገሪቱ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ ስታደርገው የነበርውን ጥረት በመሸርሸር አውዳሚ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።

በዚህም ሳቢያ እንደ ቀደመው ግዜ ሳይሆን ሀገሪቱ ግራ በተጋባ ሁኔታና ሚዛኑን ባልጠበቀ መልኩ ወይ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ አላደረገች ወይንም ከነችግሮቿ ቢሆን ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት አላዋለችም።

ይልቁንስ የፈተና ውጤት ላይ በመጠመድ እና በርካታ ተማሪዎችን ማለፍ አለመቻልን እንደ መመዘኛ በመጠቀም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመጣር ላይ ይገኛል።

ትምህርት ሚኒስቴር በቁንጽል ኩረጃ ላይ ብቻ ቅዱስ ጦርነት ማወጁ የሚፈጥረው የአዙሪት ተጽእኖ በርካታ ነው፤ የጥራት ችግሩ ቢጣባውም ሀገሪቱ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ስታደርገው የነበርውን ጥረት በመሸርሸር አውዳሚ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።  

ለአንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ጥቅም ለሌለው ነገር 12 አመታትን በትምህርት ቤት ከሚያሳልፉ ይልቅ እቤት ቢያግዙን ይሻላል የሚል ተስፋ አስቆራጭ ውሳኔ እንዲደርሱ ሊገፋፋቸው ይችላል። ሀገሪቱ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የቆየውን የብዙዎች እምነተ እና ብዙ ዋጋ ከፍላ ለማስቀረት የሞኮረችውን ይህንን እሳቤና አመለካከት እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ነው።

ለሌሎቸ ደግሞ ምንም እንኳ ውስን የሆነ የትምህርት ስኬት ቢኖራቸውም ትምህርታቸውን በመቀጠል መጻኢ ግዜያቸውን የተሻለ ለማድረግ በትምህርቱ አለም ለመቀጠል ጥረት ለሚያደርጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሁኔታው ተስፋ እንዲቆርጡ ሊገፋፋቸው ይችላል።

አሳዛኝ በሆነ መልኩ በመሃይምነት ውስጥ በሚገኙ ዜጎቿ የተቆፈደደች ሀገር፣ መንግስት ለትምህርት ዘርፍ የሚያውለው መዋዕለ ነዋይ በእጅጉ ማሽቆልቆል ተጨምሮበት በሚሊየን ከሚቆጠረው ተማሪዎች ውስጥ ሶስት ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆኑት ጥቂት ተማሪዎቿ ብቻ በየአመቱ የዩኒቨርስቲ ትምህርት እድል ማግኘታቸው እንደ መደበኛ ነገር መቁጠር መዘዙ ብዙ ነው፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት በመላክ ገንዘባቸውን እና ግዜያቸውን እንዳያጠፉ ተስፋ ከማስቆረጥ ባለፈ በሰፊው ህዝብ ጫንቃ ጥቂቶች ብቻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲስተም ብቻ ያለባት ሀገር ሊፈጥር ይችላል።

ቢያንስ ሁሉንም ችግሮች ማዕከል ያደረገ የመፍትሔ መንገድ እስኪመጣ ሚኒስቴሩ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን ቀለል ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ግምት ውስጥ ሊያስገባው ያስፈልጋል።

ሌሎች ከፍተኛ ሚና ያለቸው ችግሮችን ወደ ጎን በማድረግ ኩረጃ ላይ ብቻ ላይ ማተኮር የትምህርት ጥራትን አያረጋግጥም፤ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማደረግ የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ይጥላል፣ ትምህርትን ለጥቂቶች በጥራት ተደራሽ በማድረግ ያልተማረ ትውልድ እንዲበራከት ያደርጋል። ተሻጋሪ ምልከታ ያሻል!!

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button