ቃለ መጠይቅ
በመታየት ላይ ያለ

ቃለ ምልልስ፡ ተስፋዬ ገብረአብ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አንስቶ ተነባቢ መጽሐፍ መፃፍ እንደሚቻል ያሳየ ደራሲ ነው- የተስፋዬ ህይወት ታሪክ መጽሓፍ ጸሓፊ ጉቺ ሽመለስ

በናትናዔል ፊጤ@NatieFit

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2016 ዓ/ም፡_  በሀገራችን ሰዎች ሊያወጉብት እንኳ የማይደፍሩትን የፖላቲካ እና ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ደፍርው በኪነ ጥበብ ሰራዎቻቸው በማንሳት በህይወት ዘመናቸው መነጋገሪያ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። 

ተስፋዬ በሙያው ጋዜጠኛ ነበር። በጋዜጠኝነት ሙያው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እስክ ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ የደረሰው ተስፋዬ ኢትዮጵያ እያል ከጋዜጠኝነት ሰራው ጎን ለጎን በርካታ መጽሓፍትን ለንባብ አብቀቷል። ተስፋዬ የጋዜጠኝነት ሰራውን ካቆመ በኋላ ህይወቱ እስከታልፍ ድረስ ሙሉ ጊዜውን መጽሓፍ በመጻፍ በማሳለፍ ስምንት የሚደርሱ መጽሓፍትን ከአንባቢዎች ዘንድ አድርሷል።

ከጻፋቸው መጽሓፍት መካከል በእጅጉ እንዲታወቅ ያደረገው እና ገበያ ላይ ከዋለበት ግዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አነጋጋሪ  የሆነው መጽሓፍ “የቡርቃ ዝምታ” የሚባለው መጽሓፍ ነው። በዚህ ልቦለድ መጽሓፍ ያደነቁት እንዳሉ ሁሉ የሚነቅፉትም በርካቶች ናቸው።  

ተወልዶ ለደጋባት ቢሾፍቱ ከተማ እና ለኦሮሞ ህዝብ ያለው ፍቅር የተለየ መሆኑን የሚናገረው ተስፋዬ ገብረአብ በኦሮሞ ባህል መሰረት በሞጋሳ ስነስርዓት “ገዳ” የሚል ስም ተሰጥታል። 

ተስፋዬ ከሀገር ከወጣ በኋላ ለወራት በህመም ላይ የቆየ ሲሆን በኬኒያ መዲና ናይሮቢ በህክምና ሲራዳ ቆይቶ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም በ53 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። 

ሰሞኑን በተስፋዬ የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት ያደረግው “የአደአው ጥቁር አፈር” መጽሓፍ ገበያ ላይ መዋሉን ተከትሎ የተስፋዬ ጉዳይ ዳግም አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል። የህይወት ታሪኩ በመጽሓፍ ተሰንዶ መቅረቡን የሚቀበሉት እንዳሉ ሁሉ “የዚህ ሰው የህይወት ታሪክ መጻፍ የለበትም” በማለት የተቃውሙም በርካቶች ናቸው። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“የአደአው ጥቁር አፈር” በሚል ርዕስ የሞክሼውን የተስፋዬ ገብረአብ የህይወት ታሪክ  የጻፈው ተስፋዬ ሽመልስ (ጉቺ) የአንድ አባት ልጅ ሲሆን እድሜ በ20ዎቹ መጨረሻ ላይ ይገኛል። ጸሃፊው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጋሰራ ወረዳ ጪፋሮ ቀበሌ ተውልዶ ግኒር ውስጥ ያደገ ሲሆን ተስፋዬ ከሚለው መጠሪያ ይልቅ “ጉቺ” በማለት አያቱ ባወጡለት ስም መጠራትን እንደሚምርጥ ይናገራል።  

ከሀገር ውስጥ ደራሲዎች የባህሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁ፣ አዳም ረታ እና ተስፋዬ ገብረአብ፤ ከሀገር ውጭ ደገሞ የቼኮቭ፣ ማርክ ትዌን፣ የሀርመን ሄስን እንድናቂ መሆኑን የሚናገረው ጉቺ፤ ከዚህ ቀደም እራሱን እና ጀማሪ እና አንጋፋ ጻሓፊዎችን ያሳተፈ “አቦል” የተሰኘ መጽሓፍ ማዘጋጀቱን ገልጿል። ለዚህ ስራ ያነሳሳው ተስፋዬ በአምስት ቅጾች ያዘጋጀው ”እፍታ” የተባለው በጋራ የተዘጋጀ ስራ ነው።

ጉቺ ሽመልስ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ ትውልዱ ከተስፋዬ ህይወት ታሪክ የሚማረው ነገር እንዳለ በመመን መጽሃፉን ማዘጋጀቱን ገልጿል። ጸሓፊው፤ መጽሓፉ የተዘጋጀው ኤርትራን ጨምሮ ተስፋዬ በስራዎቹ ውስጥ ወዳነሳቸው አካባቢዎች በመሄድ ሰፊ ጥናት በማደረግ መሆኑን አስረድቷል። 

የተስፋዬ ስራዎች ለኦሮሞ ህዝብ እና ለአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ያለው አስተዋጽኦ፣ የሚደርስበትን ነቀፌታ እንዲሁም ለቢሾፍቱ ያለው ፍቅር ጨምሮ መጽሃፉ የተጻፈበትን ሁኔታዎች በተመለከተ ከጉቺ ጋር ያደረግንው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል። 

አዲስ ስታንዳርድ፡ ተስፋዬ ገብረአብ ለቢሾፍቱ ያለውን ፍቅር፣ ለስነ-ጽሑፍ ያለውን ችሎታ እንዲሁም ሰራዎቹን እንዴት እንደተረዳሃቸው ንገርን ? 

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ የተስፋዬ ገብረአብን ስራዎች ቀደም ብዬ አንብቤ የነበር ቢሆንም አጥርቼ በማስታውሰው  አንድ አጋጣሚ ግን በይበልጥ በስነጽሑፉ የመማረክ ዝንባሌ እንዳደረብኝ አስታውሳለሁ። ”የደራሲው ማስታወሻ” ላይ ”ያልተፃፈ መጽሐፍ” የሚል ትረካውን ሳነብ እንግዳ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ስራዎቹን በተደጋጋሚ አንብቤአለሁ። ተስፋዬ የአከራካሪነቱን ያህል በቃላት የሚራቀቅ ደራሲ ነው። በብዕሩ ምትሃታዊ ውበት መፍጠር ይችላል። ስራዎቹን ማንበብ ጀምሮ ማቆም አይቻልም። 

ለቢሾፍቱ ልዩ ፍቅር ነበረው። በስራዎቹ ውስጥ ቢሾፍቱ ጉልህ ናት። የብዕሩ አልፋና ኦሜጋ፣ የልብ ዜማው፣ ሁሉ ነገሩ ናት ቢሾፍቱ። ካህሊል ጂብራን ሊባኖስን አንስቶ እንደማይጠግበው ሁሉ ተስፋዬም ለቢሾፍቱ ዘምሯል። 

ስራዎቹ የቱም ስነጽሑፍ አድናቂ  የሚወዳቸው አይነት እንደሆኑ ይሰማኛል። አንዳንዶቹ ስራዎቹ  በይዘታቸው የሚያጨቃጭቁ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በኪናዊ ለዛቸው እንዲነበቡ የሚያስገድዱ ናቸው።

አዲስ ስታንዳርድ፡ የተስፋዬን የህይወት ታሪክ ለመጻፍ ምን አነሳሳህ?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ”የአደአው ጥቁር አፈር …” መጽሐፍን እንዳዘጋጅ ገፊ ምክኒያት የሆነኝን አንድ ክስተት የመጽሐፉ መግቢያ ላይ አስፍሬዋለሁ። ባጭሩ ተስፋዬ ገብረአብ ካለፈ ከሁለት ወር በኋላ ወንድሙ ጋር ሄጄ የነገረኝ አንድ አስደንጋጭ ሁኔታ መነሻ ሆኖኛል።  ይህ ሁኔታ በመጻፉ ላይ ተካቷል።

አዲስ ስታንዳርድ፡ “የአደአው ጥቁር አፈር …” የሚለውን መጠሪያ እንዴት እና ለምን መረጥክ?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ መጽሐፉን ”የአደአው ጥቁር አፈር” ያልኩት አንድም ተስፋዬ ራሱን እንደዛ ብሎ መግለፅ ስለሚመርጥ ነው። ተስፋዬ በመጽሐፉ በተደጋጋሚ ቢገልፀውም ለመጀመሪያ ጊዜ ”እኔ የአደአ ጥቁር አፈር ነኝ” ያለው ከያሬድ ጥበቡ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ነው። ወዲህ ደግሞ ሰዎች ባደጉበት አከባቢ ተፅዕኖ ስር በመሆናቸው (በዚህ ረገድ ተስፋዬ በብዙ ሊጠቀስ የሚችል ከአከባቢው የወረሰው ባህሪ አለው።) ነው።

አዲስ ስታንዳርድ፡ የመጸሓፉ ይዘት ምንድነው?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ”የአደአው ጥቁር አፈር” መጽሐፍ ምንም እንኳ የተስፋዬ ገብረአብን ግለ ታሪክ የያዘ ቢሆንም፤ ስነጽሑፍ፣ ታሪክ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችና ፖለቲካ መባያ ሆነው ቀርበዋል። መጽሐፉ በ18 ምእራፎችና በ12 ንዑስ ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን 360 ገፆች አሉት። በኢትዮጵያ የሩብ ክፍለ ዘመን ውሰጥ ሲያነጋግር ስለነበረው ተስፋዬ ገብረአብ ሙሉ ምስል ለመስጠት የሚሞክር መጽሐፍ ነው።

 እንደሚታወቀው ተስፋዬ ገብረአብ እጅጉን አወዛጋቢ የሆኑ ታሪካዊና ማህበረ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያነሳ ፀሀፊ ነው። እኚህን ጉዳዮች እሱ ሲያነሳቸው ተቃርኖአዊ የንባብን ውጤት ክሱት አድርገዋል።  በዚህ መጽሐፍ እኚህና መሰል  እንቆቅልሾች ተፈተዋል።

አዲስ ስታንዳርድ፡ በመጽሓፉ ላይ የተጠቀምካቸው ምንጮች እነማን ናቸው? 

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ መጽሐፉ ኤርትራን ጨምሮ ተስፋዬ በስራዎቹ ወዳነሳቸው አከባቢዎች በመጓዝና አያሌ ጥናት በማድረግ የተሰናዳ ነው። በርካታ ዋቢ መጽሐፍትና ሰነዶችን ከማገላበጤም በላይ የአነጋጋሪውን ደራሲ ቤተሰቦች፣ የቀድሞ ጋዜጠኞችና ባለስልጣናትን በማነጋገር አመት ከሰባት ወር ገደማ ፈጅቶ ያዘጋጀሁት መጽሐፍ ነው። 

ከውልደት ቦታው ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት ግርታ መጽሐፉን ባላነበቡ ሰዎች የመጣ ነው። መጽሐፌ ላይ ፎቶዎችን ጨምሮ ተስፋዬ ቢሾፍቱ ስለመወለዱ የሚያስረግጡ መረጃዎችን አካትቻለሁ። በዚያ ዘመን ፎቶሾፕ ነበር ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። (ሳቅ) ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋዬ ኤርትራ ተወለደ ቢባል እንኳን የሚቀይረው ነገር ያለ አይመስለኝም። 

አዲስ ስታንዳርድ፡ እንደሚታወቀው ተስፋዬ አነጋጋሪ ሰው ነው። በርካታ ወዳጅ አድናቂ እንዳለው ሁሉ የሚጠሉት እና የሚነቅፉትም ቀላል አይደሉም። ይህን ነገር እንዴት ታየዋለህ?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ልክ ነው መቼም ተስፋዬ በስራዎቹ የሚያደንቁት የመኖራቸውን ያህል የሚጠሉትና የሚተቹት መኖራቸው አልቀረም። በተለይ ”የቡርቃ ዝምታ” የተሰኘ መጽሐፉ በብዙዎች ዘንድ ከማነጋገሩም ባለፈ በአንድ በኩል የታሪካቸውን ጠባሳ  እንደፃፈ ባለውለታ፤  በሌላ በኩል ደግሞ ሁለቱን ትልልቅ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች እርስ በእርስ ለማጋጨት እንደፃፈ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ። 

ለዚህ መጽሐፍ ዝግጅት ባደረግኩት ግምገማ ግን  ”የቡርቃ ዝምታ” መጽሐፍ በዚህ ደረጃ ያወዛገበው ተነቦ ሳይሆን እንዲያው በሰሚ በሰሚ እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ። በእኔ እምነት መጽሐፉን ልናነበው፣ በግልፅ  ልንነጋገርበት፣ ልንወያይበትና ልንተቸው ይገባል። በመጽሐፌ ይሄን አድርጌአለሁ። በእርሱ አከራካሪ ስራዎች ላይ ለመነጋገር ምቹ መደላድልን ፈጥሬአለሁ። በአመክንዮ ላይ በተመሰረተ መልኩ እንደ ልብ መተቸትም ሆነ ማወደስ ይቻላል። ተስፋዬ በስነጽሑፉ የዳሰሳቸውን ይዘቶች ምንም ይሁኑ ምን፤ በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ መሻርም ሆነ ማጽናት ከእኛ የሚጠበቅ የቤት ስራ እንደሆነ አምናለሁ። እኔ መንገዱን ጀምሬአለሁ። 

አዲስ ስታንዳርድ፡ ተስፋዬ ለኦሮሞ ህዝብ የዋለው ውለታ ምንድነው?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ተስፋዬ በኦሮሞ ህዝብ መካከል ተወልዶ እንደማደጉ መጠን የማህበረሰቡን እሴት፣ እምነት፣ ወግ፣ ባህል ስርዓትና የአኗኗር ይትባህል የማየት በዛም ውስጥ የማደግ እድልና የመቃኘት አጋጣሚ ነበረው። በጽሑፎቹ ውስጥም እኚህ ከላይ የጠቅስናቸውን የማህበረሰብ አይነተኛ መለያዎችን ሲያወሳ፣ ሲዘክር አንዳንዴም ሲተች እናገኘዋለን። ተስፋዬ የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ጭቆና እና ድል የያዙ በርካታ ፅሁፎችን ፅፏል። በዚህም በኦሮሞ ህዝብ ባህል መሰረት በሞጋሳ ”ገዳ” ተብሎ ኦሮሞ ሆኗል። በእርግጥ እሱ ከመነሻውም ኦሮሞ ነበርኩ ይላል።

አዲስ ስታንዳርድ፡ ከሁለት አመት በፊት ተስፋዬ ሲያርፍ በርካታ ሰዎች ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር። ተስፋዬ ይህን ያህል ጥላቻ ይገባዋል ብለህ ታስባለህ?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ህልፈቱን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከኢትዮጵያዊ ባህልና ስርዓት ባፈነገጠ መልኩ ”እንኳን ሞተ” ሲሉ ተሰምቷል። በግሌ ”ሙት አይወቀስም” እየተባለ የሞቱ ሰዎች ጥፋት መነሳት የለበትም በሚለው እምብዛም አልስማማም። ማንም በሰራው ልክ አበጀህ ሊባል እንደ ጥፋቱ መጠንም መወቀስ እንዳለበት አስባለሁ። በዚህ መሰረት ተስፋዬ ”እንኳን ሞተ” እስኪባል ድረስ አጥፍቷል ወይ የሚለው መታየት አለበት። ከላይ ያነሳሁት መጽሐፉን ለማዘጋጀት የገፋኝ ምክኒያትም ከዚህ ጋር የሚናበብ ነው።

አዲስ ስታንዳርድ፡  ለአማርኛ ስነ ጽሑፍ ያደረገውን አስተዋጽኦ እንዴት ትገልጸዋለህ? 

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ተስፋዬ በበዙ መልኩ ሊጠቀሱ የሚችሉ አስተዋፅዖዎችን ለአማርኛ ስነፅሁፍ አበርክቷል። በአምስት ቅፆች የተዘጋጀውን ”እፍታ” በግንባር ቀደምነት መጥቀስ ይቻላል።  እፍታ ከ300 በላይ ትረካዎችና 100 ታላላቅ እና ጀማሪ ደራሲያንን ስራ አካቶ የያዘ ስራ ነው። የዚህ ስራ ሃሳብ ባለቤትም ሆነ ፅሁፎቹን አሰባስቦ ሲያሳትም የነበረው ተስፋዬ ነው። እሱ ያዘጋጃቸው የ ”ተራሮችን ያንበጠቀጠ ትውልድ” ከቅጽ አንድ እስከ ሶስትም የዘመኑን መንፈስና ማህበራዊ ስነልቦና በማሳየት ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። 

እንደዚሁም ወጥ የፈጠራ፣ የስነጽሑፍና ታሪክ ቀመስ ልብወለዶቹ በቀለማቸው፣ በውበታቸው የአማርኛውን ስነጽሑፍ ሌላ ገጽታ አላብሰውታል። ለብዙ ጀማሪ ደራሲያን አርዕያ መሆንና ተነሳሽነት መፍጠሩ፣ ለአማርኛ ስነጽሑፍ ማንሰራራትና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አንስቶ ተነባቢ መጽሐፍ መፃፍ እንደሚቻልም እንዳሳየ ማየት ይቻላል። ይሄ የስነጽሑፍ ፍኖቱ ነው ”ስነጽሑፍንና ፖለቲካን ድል ባለ ሰርግ ያጋባ” የሚል ስም ያሰጠው። በብዙ አንባብያን ዘንድ ተመራጭ የሆነውንና በተለይም ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንና በዓሉ ግርማ የሚታወቁበትን የአጫጭር አረፍተ ነገር መጠቀም ዘዬ፤ ይበልጥ በማጎልበትቱም  ከአማርኛ ስነጽሑፍ ባለውለታዎች እንደ አንዱ እንዲቆጠር ሆኗል።

አዲስ ስታንዳርድ፡  ስዎች ይህን መጽሓፍ ካነበቡ በኋላ ምን ይማሩበታል ?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ”የአደአው ጥቁር አፈር” መጽሐፍ በማንበብ ከተስፋዬ ገብረአብ ሕይወት ሰዎች ላመኑበት ጉዳይ የሚሄዱበትን መጠን አልባ ርቀት፣ የአላማ ፅናት፣ ለወደዱት መሰጠትን፣ ከምንም በላይ በውጣ ውረድ ከተሞላው የተስፋዬ ህይወት ሊማሩት የሚችሉት ነገር እንደሚኖር ገምታለሁ። 

እንግዲህ አንድ ሰው ህይወቱ በአዎንታዊ ጉዳዮች ብቻ የተሞላ አይደለም። የእንደዚህ አይነት መጽሐፎች አንዱ ፋይዳ ሰዎች ከግለሰብ ስህተትም ትምህርት ማግኘት መቻላቸው ነው። መጽሐፉ በዘመኑ የተከሰቱ ጉዳዮችን ጭምር በማንሳቱም አንባቢያን በተስፋዬ ህይወት ሽንቁር ውስጥ የሚመለከቱት የጊዜና የዘመን መልክ ይኖራል። ከላይ እንደጠቀስኩት የመጽሐፉ ማእከላዊ ጭብጥ ተስፋዬ ቢሆንም፤ ታሪክ፣ ሰሰነልቡና፣ ማህበራዊ ጉዳይና ፖለቲካንም ይንተራሳል። 

አዲስ ስታንዳርድ፡ በመጨረሻም ስለ ተስፋዬ ገብረአብ መጨመር የምትፈለገው ነገር ካል?

ተስፋዬ (ጉቺ)፡ ተስፋዬ ያመነበትን ነገር ፅፎ አልፏል። እያጠለልን ማንበብ የእኛ ፈንታ ነው። ተስፋዬ እንደማናችንም አይነት ሰው ነበር። ”የአደአው ጥቁር አፈር” መጽሐፍ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ሆኖ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው። ተስፋዬ መጽሐፎቹን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንደፃፈ፣ ለመፃፍ ያነሳሱትን ምክኒያቶች፣ ከዘመኑ መንፈስ ጋር አገናኝቼ  ነው ያዘጋጀሁት። ተደራሲ ስለ ተስፋዬ በቂና ዝርዝር መረጃዎችን ያገኛል።  በመጨረሻም አንብቡት። ተቹት። ተወያዩበት። ማለት እፈልጋለሁ። አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button