አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6/2016 ዓ.ም፡- የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲያቸው የሰጠውን በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሳኔ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ህወሓት እንደአዲስ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ ይመዝገብ ማለት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትን ማፍረስ ማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ነሃሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የህወሐት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ከመንግሥት በኩል ሊደረግ የሚችለው ሁሉ ተደርጓል” ሲል በመግለጽ ህወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንዲያከብር አሳስቧል።
እየተካረረ የመጣው የትግራይ ፖለቲካ ውዝግብ “የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥል” በሚል በክልሉ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ሰልፎች መከልከላቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የሰላምና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስታወቁ።
“በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ይፈታል” ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
“የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ላልተወሰነ ግዜ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ሰልፎች ማካሄድ የተከለከለ ነው” ሲሉ የተደመጡት ሌተናል ጀነራል ታደሰ “የፖለቲካ አለመግባባቶች ወደ ማንኛውም የጸጥታ አደጋ እንዲሸጋገር የጸጥታ ሀይሉ እንደማይፈቅድ” አመላክተዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ነዋሪ ደህንነት ላይ ችግር እንዳይፈጠር በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ማለታቸውን ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክተው ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲያቸው የሰጠውን በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሳኔ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። “ህወሓት እንደአዲስ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ ይመዝገብ ማለት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትን ማፍረስ ማለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“በምርጫ ቦርድ ፓርቲው እንውቅና እንዲያገኝ ሲባል የክልሉ ህዝብ ያካሄደውን የህልውና ትግል አይጨናገፍም” ሲሉ ሊቀመንበሩ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናግረዋል።
የፓርቲው ህጋዊ ሰውነት አስመልክቶ ተከታታይ ውይይቶች ከፌደራል መንግስቱ ጋር መደረጉን የጠቆሙት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል “ህጋዊ ሰውነቶ እንደሚመለስ ነበር መግባባት ላይ የተደረሰው ቢሆንም አዋጅ በማሻሻል ከነሃሴ 3 ቀን 2016 ጀምሮ እንደ አዲስ እንዲመዘገብ ነው የተደረገው” ሲሉ ገልጸዋል፤ “የ50 ዓመታት ታሪክ ያለው ፓርቲ ነው እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የተፈለገው፣ አይሆንም” ብለዋል።
እንደ አዲስ ፓርቲ ለመመዝገብ” አንፈልግም፣ አልጠየቅንም” ያሉት ሊቀመንበሩ በምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ “አመጽ አስነስታችኋል ነው የተባልነው፤ ይህም ህዝቡ ያካሄደውን የህልውና ትግል ለማሳጣት እየተሰራ ያለን ስራ የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ህወሓት እንደ ፓርቲ እውቅና እንዲያገኝ ተብሎ “ትግሉ ሊጨናገፍ አይችልም፣ በአጠቃላይ በዚህ አካሄድ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እየፈረሰ ነው ማለት ነው፣ ምክንያቱም ደግሞ ከፌደራል መንግስቱ ጋር የተፈራረመው ህወሓት እንደ አዲስ እንዲመዘገብ እየተደረገ ስለሆነ” ብለዋል። የፐሪቶርያው የሰላም ስምምነት ባለቤት አልባ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስቱ ህወሓት ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ፍላጎት ማሳየቱን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ይህንን በእኛ በኩል ያደነቅነው ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“በፓርቲው አመራር መካከል መሰንጠቅ መፈጠሩ የጉባኤውን አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ላይ ሁኖ መታገል የማይችል ሀይል ስላለ ይህንን ለማስተካከል ጉባኤ ያስፈልጋልና” ብለዋል።
ፓርቲው እየፈረሰ ያለው “ከውጭ በመጣበት ሳይሆን ከውስጥ በመሆኑ ሊድን የሚችለው በጉባኤተኛው ነው” ብለዋል። ጉባኤው “የፓርቲው የድህነት መንገድ ስለሆነ ይካሄዳል” ያሉት ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል በዚህም ሳቢያ የሚመጣ አደጋ የለም ሲሉ አስታውቀዋል። “በፓርቲው አመራር መካከል የተፈጠረው መሰነጣጠቅ ሊስተካከል የሚችለው በጉባኤው በመሆኑ መካሄድ አለበት” ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ነሃሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የህወሐት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ከመንግሥት በኩል ሊደረግ የሚችለው ሁሉ ተደርጓል” ሲል በመግለጽ ህወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንዲያከብር አሳስቧል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት መነሻና መድረሻው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ማክበር ነው በሚል ርዕስ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ “የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ የገባው ግዴታ የህወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሣ ሂደቱን የማሣለጥ ኃላፊነት እንጂ የወሰድኩት የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አልነበረም” ብሏል።
ስለሆነም፣ “ከፕሪቶሪያ ስምምነት አኳያም ሲታይ የሕወሐት የሕግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ሕግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲል ገልጿል።
ስለሆነም የምዝገባ እና የህግ ሰውነትን ጉዳይ በዚህ በመቋጨት በልማት አጀንዳ ላይ ልናተኩር ይገባል ሲል አሳስቧል።
በሌላ ዜና አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ፓርቲው በቀጣይ በሚያካሂደው ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ በደብዳቤ አስታወቁ። ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው 14ቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ “ህወሓትን ለማፍረስ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ እንደማንሳተፍ በግልጽ እናስታውቃለን” ብለዋል።
በፓርቲው ከፍተኛ ስልጣን ያለው የማዕከላዊ ኮሚቴው ያልተረዳዳበት፣ የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን ያልተቀበለው፣ ከህወሓት አሰራር ባፈነገጠ መልኩ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴውን በማፍረስ ራሱን አዘጋጅ ኮሚቴ በማድረግ ጉባኤ ለማካሄድ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ቡድን አለ ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ አመላክተዋል።
በዚህ ቡድን ሊካሄድ የታሰበው ጉባኤ በበርካታ የክልሉ አከባቢዎች በተለይም በደቡብ እና ደቡባዊ ትግራይ ዞኖች ተቀባይነት ያላገኘ፣ በምዕራብ እና በተወሰኑ የምስራቅ የክልሉ ዞኖች የሚገኙትንም በአግባቡ ያላሳተፈ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር መግባባት ላይ ያልተደረሰበት ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው ተችተዋል።
ጉባኤውን ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን ፓርቲውን እና የክልሉን ህዝብ ከባድ አደጋ ውስጥ በመክተት የቡድኑን ጠባብ ፍላጎት ለማሟላት መሆኑን ግልጽ ነው ያሉት አባላቱ በደብዳቢያቸው ፓርቲውን እና ህዝቡን ለከፋ አደጋ በሚያስገባው ጉባኤ ላለመሳተፍ ወስነናል ብለዋል።
ፓርቲውን ለማዳን የምናደርገውን ትግል የበለጠ አጠናክረን እንደምንቀጥል እንገልጻለን ብለዋል። ከአቶ ጌታቸው ረዳ በተጨማሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሒወት፣ አቶ ረዳኢ ሃለፎም እና ሃፍቱ ኪሮስ ይገኙበታል። አስ