ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ፣ የአከባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎች “የፋኖ ታጣቂዎችን” ተጠያቂ አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም፡-ባሳለፍነው ሳምንት በኦሮምያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ። የአከባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ጥቃት አድራሾቹ የፋና ሃይሎች ናቸው ብለዋል።

ስማቸው ለደህንነታቸው ሲሉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በደራ ወረዳ በሚገኙ ጂሩ ደዳ እና ወሬን ገብሮ በተባሉ መንደሮች ነው።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጂሩ ደዳ መንደር ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት በጥቃቱ የተገደሉት ነዋሪዎቹ ታደሰ ጆቢር (የ46 አመት እድሜ)፣  ተስፋየ ደምሴ (48 አመት እድሜ)፣ ታሜ አበራ (32 አመት እድሜ)፣ ተሾመ ክብረት (የ60 አመት እድሜ) ናቸው።

በወረዳዋ የምትገኘው ጨካ ከተማ እና በዙሪያዋ የሚገኙ መንደሮች በተፈጠረው ጥቃት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ስጋት የመንግስት ጽ/ቤቶች መዘጋታቸውንም ተናግረዋል፤ “የጤና፣ ትምህርት እና ማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ዝግ ናቸው” ብለዋል።

ስለጥቃቱ አዲስ ስታንዳርድ የጠየቃቸው የጨካ ከተማ ከንቲባ ሁኔታውን ሲያስረዱ ግጭቱ የተፈጠረው “በጽንፈኛው የፋኖ ሀይሎች” እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል መሆኑን ጠቁመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ሀይሎች የፋኖ ሀይሎችን ከከተማዋ በማስወጣት ተቆጣጥረዋታል ብለዋል። እንደ ከንቲባው ገለጻ ከሆነ የፋኖ ሀይሎች በተደጋጋሚ ይህንን ለመበቀል ወደ ከተማዋ በመዝለቅ በንጹሃን ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ ብለዋል።

“ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ታጣቂዎች በከተማዋ የገበያ ቦታ ላይ በቅርቡ በፈጸሙት ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውንም” ገልጸዋል። በአከባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። በዚህም ሳቢያ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች አከባቢውን ለማረጋጋት መግባታቸውን አስታውቀዋል። አከባቢው በጣም ሰፊ በመሆኑ እና በረሃማ አየር ጸባይ ስላለው የጸጥታ ቁጥጥሩን አስቸጋሪ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋ።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን (ሸኔን) እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ የፋና ሀይሎች በሌላ አቅጣጫ ጥቃት እንደሚከፍት ጠቁመዋል። ይህም በወረዳዋ የጸጥታ እና መረጋጋት ስራውን እንዳወሳሰበት አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአከባቢው የፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው ጉዳት አደረሱ የሚሉ በርካታ ክሶች በቡድኑ ላይ በመቅረብ ላይ ይገኛሉ። በቡድኑ ላይ ከሚቀርቡ ውንጀላዎች መካከል ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ዞን በኪረሙ ወረዳ አሮ መንደር በፈጸመው ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የተመለከተው ይገኝበታል።

በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አንዱ የሆነው የ35 አመቱ የበሪሳ አያና ወንድም የሆነው ሀብታሙ አያና ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የፋኖ ታጣቂዎች ጠዋት ሶስት ሰአት አከባቢ ጥቃት ማድረስ መጀመራቸውን ገልጿል።

ሁኔታውንም ሲያብራራ ወንድሙ እና ሁለት ሌሎች ሰዎች ወደ አሮ መንደር በመጓዝ ላይ እያሉ የፋኖ ታጣቂዎች እንዳስቆሟቸው እና ታጣቂዎቹ ወንድሙን በሞባይል ባንኪንግ 31ሺ 400 ብር እንዲያስተላልፍላቸው ጠይቀውታል፣ ብሩን ካላስተላለፍክልን አንተንም ሁለቱንም ሰዎች እንገላችኋለን ሲሉ እንዳስፈራሩት አስታውቋል።

ሀብታሙ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጸው ከሆነ ከወንድሙ ጋር የነበሩት ሰዎች እንደሚያውቃቸው ጠቁሞ አንደኛው የ45 አመቱ ግዛቸው ፈይሳ የሚባል እና የኪራሙ ወረዳ መንግስት ሰራተኛ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ጃልዱ ገለታ የተባለ የ26 አመት ወጣት የሞተር ሳይክል ሹፌር ነው።

በተመሳሳይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ሀይሎች በፈጸሙት ጥቃት አንዲት እናት ከሁለት ልጆቿ ጋር በዚሁ በኪራሙ ወረዳ መገደሏን የአከባቢው ሰዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ያደረሱት መረጃ ያሳያል። ጥቃቱ የተፈጸመው በወረዳው በምትገኘው አይሾ ኩሻየ መንደር ሲሆን የሟች ባለቤት እና የልጆቹ አባት መሆኑን የገለጸልን ማንጎ ጎፋ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ታጣቂዎች ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በመንደሯ ባደረሱት ጥቃት ባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ሲገደሉ አንዱ ልጁ መትረፉን አስታውቋል፤ ከጥቃቱ የተረፈው ልጁ በነቀምት ሆስፒታል በመታከም ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button