በሞላ ምትኩ @MollaAyenew
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18/ 2016 ዓ/ም፦ የትግራይ ህዝብ ለሁለት አመታት በዘለቀው ጦርነት የከፋ መከራን አሳልፏል። ምንም እንኳ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ግጭትን ቢቋጭም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቃይ ሆነው ቆይተዋል። እንደ ምግብና ህክምና ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘትም እየታገሉ ይገኛሉ።
የጦርነቱ ቀጠና የነበረውና የከፋ ውድመት የደረሰበት የትግራይ ክልል አሁን ደግሞ ተባብሶ ከቀጠለው እገታ እና ጥቃት ጋር እየታገለ ይገኛል። በክልሉ እየተፈፀሙ የሚገኙት እነዚህ ወንጀሎች ከሁለት ዓመቱ ጦርነት ወዲህ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በማደፍረስ ማህበረሰቡ እንዲሸበርና የክልሉን የማገገም ሂደት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል።
በመጋቢት ወር ታግታ ሰኔ 2016 ዓ.ም. የተገደለችው ማህሌት ተኽላይ፤ ለዚህ እየተባባሰ ለመጣው ቀውስ አሳዛኝ ምሳሌ ናት። የ16 ዓመቷ ማህሌት ተኽላይ በባጃጅ ተሳፍራ ቋንቋ ወደ ምትማርበት ት/ቤት ስትሄድ ከታገተች በኋላ የማስለቀቂያ ብር ተጠይቆባት ነበር።
“አጋቾቹ ልጃችንን ለማስለቀቂያ የሚውል 3ሚሊዮን ብር እንድናዘጋጅ ጠይቀው አስፈራርተውን ነበር። በወቅቱ ለመደራደር ያደረግነው ጥረት ቢኖርም ያልጠበቅነውና በጣም አስከፊው ነገር ተፈጠረ።” ሲሉ የሟች ወላጅ አባት አቶ ተኽላይ ግርማይ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
የአድዋ ከተማ ፓሊስ ኃላፊው አቶ ተስፋዬ አማረ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት የማህሌት አጋቾችን ለፍርድ ማቅረብ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ምርመራው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልፀው በቀጣይ በምርመራ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ግኝቶችን እና የሚኖሩ ሁኔታዎችን ለህብረተሰቡ እንደሚያሳውቁ ቃል ገብተዋል።
በሚያሳዝን ሁኔታ የማህሌት ታሪክ በክልሉ ብቸኛው ክስተት አይደለም። በህፃናት እና በጎልማሶች ላይ ሳይቀር ያነጣጠሩት የእገታ ተግባራት በክልሉ እየተበራከቱ መጥተዋል። ቀደም ሲል በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቢኖሩም አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ ነው። ይህም ክስተት ነዋሪውን ኑሮውን በፍርሃት እንዲገፋ አድርጎታል።
ሌላኛው አሳዛኙ ክስተት በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም. የተፈጸመ ሲሆን፤ አቶ መሃሪ ከበደ የተባሉ ግለሰብ ልጅ የሆነ ህፃን ታግቶ ተወስዶ ለማስለቀቂያ የሚውል አራት ሚሊየን ብር እስኪከፍል ድረስ ለአንድ ሳምንት ተይዞ ቆይቷል።
በትግራይ ዋና ዋና ከተሞች የዘረፋ እና ስርቆት ተግባራት መበራከታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።
በቅርቡ 27 የሚደርሱ የትግራይ ሲቪክ ማህበራትም በክልሉ እየተስፋፉ ለመጡ ቀውሶች ማለትም በሥርዓተ ጾታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችን እንዲሁም ግድያ እና አፈናዎችን ለማስቆም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። ቡድኖቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ከመቀሌ ከተማ ፖሊስ የተገኘውን አስደንጋጭ አሃዝ ማለትም በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 12 ሴቶች መገደላቸውን፣ 80 መደፈራቸውን፣ 10 መታገታቸውን፣ 178 የሚሆኑት የግድያ ሙከራ ሰለባ መሆናቸውን በመጥቀስ በክልሉ እየደረሰ ያለውን ግፍ አውግዘዋል።
የሲቪክ ማህበራቱ እነዚህን ወንጀሎች ለማስቆም ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለመኖሩ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል ሲሉ ገልፀዋል። አክለውም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታና የፍትሕ ተቋማት ወንጀለኞችን መከላከልና ለህግ ማቅረብ አለመቻላቸውን ገልፀው ይህም ድርጊት የዓለምአቀፍ ህግን መጣስ ነው ሲሉ ከሰዋል።
በሰኔ ወር በአዲግራት የተደረገው ሰልፍ በክልሉ መዲና መቀለም ተካሄዷል። ሰልፉ በሴቶች የተደረገ ሲሆን በክልሉ እየተፈጸሙ ያሉ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል። በተጨማሪም የጾታ ጥቃት፣ እገታና ሌሎች ጥቃቶች የደረሰባቸው ሴቶች ፍትህ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጦርነት ወደ ቀውስ
ተመራማሪ እና የዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ተስፋዬ ገብረመድህን፤ በክልሉ ያጋጠመውን እገታ መስፋፋት ከጦርነቱ በኋላ ከደረሰው አጠቃላይ የህግ እና ስርዓት ውድቀት ጋራ ያያይዙታል። የትግራይ ነዋሪዎችን በተለይም ሴቶችን እና ህፃናትን ድህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊነትንም አጽንኦት ሰጥተውታል። “ጦርነቱ ቢቆምም፤ የአለመረጋጋት ስሜት እና የአፈና ፍርሃት እንደቀጠለ ነው” ሱሉም መምህሩ አክለዋል።
ምሁሩ በበኩላቸው በክልሉ የጸጥታ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ወደ ቦታው ባለመመለሱ የሃይል ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸው ይህም ለታጣቂ ቡድኖች ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው አብራርተዋል። የጦርነቱ ዳፋም የጦር መሳርያ መስፋፋትን እና የወንጀል ድርጊቶች መበራከትን ጨምሮ ክልሉ እንዳይረጋጋ መንስኤ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ በህወሓት ውስጥ ያለው የውስጥ መከፋፈል ሁኔታውን አባብሶት በክልሉ ውስጥ ያለውን ሁከት እንዲጨምር አድርጓል። “ፍርሃት ለትግራይ ተወላጆች ቋሚ የኑሯቸው መገለጫ ሆኗል።” ያሉት መምህሩ አክለውም ሲቪሎች፣ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ሰራተኞች እና ጋዜጠኞች የጥቃቱ ኢላማዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። የጥቃት ፈፃሚዎችም ማንነት እስከአሁን ድረስ ግልጽ ያልሆነ ሲሆን ከግለሰቦች አንስቶ እስከ ተደራጁ ወንጀለኞች እና የታጠቁ ወታደራዊ አንጃዎች ድረስ የወንጀል ድርጊቶቹ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።
ከእነዚህ አፈናዎች በስተጀርባ ያሉት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም በዋነኛነት ግን ለገንዘብ፣ የአከባቢ ፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ወይም በቀላሉ ሽብርን ለማስፋፋት ነው ሲሉ አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል::
አክለውም በየጊዜው የሚስተዋለው የፀጥታ ስጋት የክልሉን መንፈስ እየረበሸው እንዳለ፤ ከጦርነቱ በኋላ መልሶ ለመቋቋም እና ለማገገም የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፈ እንደሚገኝ እና ህብረተሰቡ ከጦርነቱ ወዲህ የዕለት ተዕለት ኑሮውን በድጋሚ እንዳይመሰርት እያደረገው ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የተቃዋሚው ውድብ ናፅናት ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን መዝገበ፤ የጸጥታው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ሲሉ ይገልፃሉ። “ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ተቋማት መላክ ይፈራል” ያሉት ሊቀመንበሩ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህግና ስርዓትን ማስከበር አልቻለም ሲል ወቅሰዋል። አክለውም “የህወሓት አባላት በወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሳታፊ ናቸው” ሲሉ ከሰዋል።
“ከጦርነቱ ወዲህ የተኩስ አቁም በክልሉ ቢደረግም ሁከት፣ እገታ እና ግድያ አሁንም ቀጥሏል” ሲሉ ዶ/ር ደጀን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ገብረመድህን አያሌው በበኩላቸው ክልሉ ታይቶ በማይታወቅ የጸጥታ ችግር ውስጥ መውደቁን ይስማማሉ። ትግራይ በድህረ ጦርነት ወቅት ላይ ከሚገኙ ሌሎች ክልሎች በላይ የከፋውን እያሳለፈ እንሚገኝ ይናገራሉ።
የሥነ ልቦና ባለሙያው አክለውም “ነዋሪዎች በቋሚ ፍርሃት ውስጥ ሆነው መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይታገላሉ” ያሉ ሲሆን፤ “የማህበራዊ ሥርዓት መበስበስን እየታዘብን እንገኛለን።” ሲሉ ሁኔታውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል።
ዶ/ር ደጀን ለችግሮቹ መባባስ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ለዚህም በፓርቲና በመንግሥት ተግባራት መካከል ይህ ነው የሚባል ልዩነት አለመኖሩን እንደ መንሰኤ ያስቀምጡታል። አክለውም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የቀድሞውን የፖሊስ ሃይል አፍርሶ ያልሰለጠኑ አዳዲስ ተተኪዎችን ሾሟል ሲሉ ይከሳሉ።
“በክልሉ በጠራራ ፀሃይ የሚፈፀሙ አፈናዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። በተለይ ህፃናት እና ሴቶች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። የቀድሞው የፖሊስ ሃይል መፍረስ እና ያልሰለጠኑ ተተኪዎች መሾማቸው እንዲሁም በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ተሳትፎ ማድረጋቸው በክልሉ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንዲበራከቱ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።” ሲሉ ዶ/ር ደጀን አክለው ገልጸዋል።
በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ቀውስ ገልጸዋል። ባለስልጣናት ሳይቀሩ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው አክለውም የማይታወቁ እስር ቤቶች መኖራቸውን አጋልጠዋል::
ሆኖም ከወራት በኋላ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ተንሰራፍተው በሚገኙ የወንጀል ተግባራት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ችግሮቹን ለመፍታት ከተለምዷዊ የጸጥታ ወይም የፖሊስ አሠራሮች ባለፈ ሁሉን አቀፍ አካሄድ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
አስተዳደሩ የመንግሥት ባለስልጣናትን እና ባለሃብቶችን ጨምሮ በወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በምንም ሁኔታ እንደማይታገስ አስታውቋል።
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ የተካሄዱ ምርመራዎችን ተከትሎ በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ተጠርጣሪዎች መታሰራቸው የተገለጸ ሲሆን የብረት ማዕድንን በኮንትሮባንድ ማዘዋወርን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለማስወገድ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ሕግ እና ስርዓትን ወደ ነበረበት መመለስ
የዩኒቨርስቲ መምህሩ እና ተመራማሪው አቶ ተስፋዬ በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ረጅም እና አድካሚ ሂደትን ማሳለፍ ይጠይቃል ብለው ያምናሉ። በፌደራሉ መንግሥት፣ በህውሓት እና በክልሉ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ተጨማሪ ጥረት ያስፈልገዋል ሲሉ ያስረዳሉ። ተለዋዋጭ በሆነው በዚህ ሁኔታ እና አከባቢ የፕሪቶሪያው ስምምነት ቁልፍ አካል የሆነው የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ህበረተሰቡ መልሶ ማዋሃድና መልሶ ማደራጀት ሂደት በጥንቃቄ መያዝ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።
ለወደፊት ሁከት እና ብጥብጥን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ፍትሕን ማስፈን እንዲቻል ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል።
የፀጥታ ስርአቱን ማጠናከር እና የሕዝብ ተሳትፎን ማረጋገጥ በክልሉ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም ባለሙያው ጠቁመዋል። ችግሮቹንም ከስር መሰረታቸው ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በፌደራልና በክልል ባለሥልጣናት መካከል ግልጽ የሆነ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የትግራይን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ፈታኝ ይሆናል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ነገር ግን የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት፣ ውይይትን በማጎልበት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ ቁስሎችን ማከም እና ለወደፊት ከፍርሃት የፀዳ ህይወት መገንባት ያስችላል ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ በክልሉ የሚታየውን የአፈና መስፋፋት የሁለት ዓመቱ ጦርነት ካስከተለው የህግና ሥርዓት ውድቀት ጋራ በቀጥታ ይገናኛል ሲሉ ይሞግታሉ። የነዋሪዎችን በተለይም የህፃናትን ደህንነት በማስቀደም የትግራይን ጸጥታ ወደ ነበረበት መመለስ አስፈላጊ ነው ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል። ወደፊትም የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ተስፋዬ አክለውም “የጦርነት ጥላ ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የማገገም እና ከፍርሃት የፀዳ የወደፊት ህይወት የመገንባት እድል አለ።” ሲሉ ተናግረዋል::
ዶ/ር ደጀን የክልሉ መንግሥት ሁሉንም የትግራይ ተወላጆች በማካተት እንዲጠናከር አሳስበዋል። አስተዳደሩ የአካታችነትን መርህ በመከተል እና ሁሉንም የክልሉን ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በማረጋገጥ ጠንካራ የክልል ምክር ቤት እንዲያቋቋም እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲጠናከር ጠይቀዋል። ይህም ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን በተቀናጀ ሁኔታ ጥረት ማድረግ የሚችል አስተዳደርን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ የማህበረሰቡ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸው በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው ወጣቱ ለማህበረሰቡ ዘብ ከመቆም ወደ ሁከት ፈጣሪነት መቀየሩን ጠቁመዋል። ጠንካራ የሞራል መሰረትን እንደገና መገንባት እና የሥነምግባር እሴቶችን ማደስ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
አክለውም ችግሩን ለመፍታት በወላጆች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በጸጥታ አካላት መካከል ትብብርን የሚያካትት አጠቃላይ አካሄድ ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ብልሹ አሰራርን እና ሁከት ፈጣሪነትንም ለመዋጋት በት/ቤቶች ውስጥ የስነምግባር ትምህርት እንዲሰጥ አሳስበዋል። የሃይማኖት ተቋማት ሥነምግባር እና ግብረገብነትን በማስተዋወቅ ረገድ የሚጫወቱት ሚናም ከፍተኛ እንደሆነ አንስተዋል።ሷ
የስነልቦና ባለሙያው አቶ ተስፋዬ እየታዩ የሚገኙ የማህበረሰብ እሴቶች መሸርሸርን ለማረም የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታትም በመንግሥት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በትምህርት ተቋማት እና በህብረተሰቡ መካከል አንድነት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::
በትግራይ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ፈታኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይገለፃሉ። መተማመንን እንደገና መገንባት፣ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ለተፈፀሙ የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ እርምጃዎች ናቸው። በተጨማሪም፤ በአመራሮች እና በስራ ሃላፊዎች መካከል ግልጽ የሆኑ ግንኙነቶችን መፍጠር እንዲሁም የግጭቱን መንስኤ በእውነተኛ እና ቅን በሆነ የውይይት መንፈስ መፍታት አስፈላጊ ከሆኑ እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ዞሮ ዞሮ ትግራይ ማገገም የምትችለው ያለፉትን ቅሬታዎች በመጋፈጥ እና ከፍርሃት የፀዳ የወደፊት ጊዜን በመገንባት ብቻ ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።አስ