አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19/ 2016 ዓ/ም፦ በትግራይ ክልል አስከፊ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ እና የረሀብ አደጋ እየተባባሰ መምጣቱን ቢቢሲ ከሳተላይት ምስሎች ማረጋገጡን ዘግቧል።
በክልሉ ከተከሰተው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በድርቅ እና ሰብል ባለመሰብሰቡ ምክንያት የከፋ የሰብአዊ ቀውስ እየተከሰተ መሆኑ ተገልጿል።
ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቆሪር በተሰኘው ስፍራ አነስተኛ ሃይቅ የሚገኝ ሲሆን ሰው ሰራሽ ግድብም ተሰርቶለት ከግድቡ ጀርባ በታቆረው ውሃ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁንና ቢቢሲ ከሳተላይት ምስሎች አረጋገጥኩ ብሎ እንደገለጸው በሰኔ 2016 ዓ.ም. ውሃ ማቆሪያው ደርቆ፤ የእርሻ ቦታውም ተራቁቶ ይታያል።
የመስኖ ልማትን ተጠቅመው ቲማቲም፣ ሽንኩርት እና ማሽላ ያመርቱ የነበሩት የአከባቢው አርሶአደር ድምፁ ገብረመድኅን ከቢቢስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “አሁንም በቂ ዝናብ ካልዘነበ የመስኖ ሥራ ማካሄድ የማይታሰብ ነው” ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
ጦርነቱን ተከትሎም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ እና ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ በርካታ ካምፖች የተጠለሉ ሲሆን አርሶ አደሮች በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት የእርሻ ስራ ማከናወን ባለመቻሉ በርካቶች አሁንም በመጠለያ ካምፖች መቆየትን መርጠዋል ተብሏል።
በክልሉ ካጋጠመው የምግብ እጥረት ጋራ ተያይዞ በርካት ህፃናት ለመቀንጨር ችግር መጋለጣቸውም ተነግሯል።
እንዳባጉና ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል እያገለገሉ የሚገኙት ዶ/ር ገብረክርስቶስ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ህፃናት ከመጠለያ ጣቢያዎች እና ከአጎራባች ከተሞች እንደሚመጡ ጠቅሰው “እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ የምንደርስበት አቅም የለንም::” ሲሉ አስረድተዋል።
የትግራይ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኃላፊ ዶ/ር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው “2.1 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። 2.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አስተማማኝ የማይባል የምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ዎርልድ ፒስ ፋውንዴሽን የተሰኘው ተቋም ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክስ ደዋል በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በ1984 (እአአ) ከተሰተው እና አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ረሃብ ጋር ያመሳስሉታል:: “በወቅቱ የነበረው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠም ነበር::” የሚሉት ሃላፊው አክለውም ረሃብ ሰው ሰራሽ መሆኑን እና የችግሩ ፈጣሪዎችም ሃላፊነታቸውን እንደማይወስዱ ይጠቁማሉ።
የፌዴራሉ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች አሉ የሚባሉ የምግብ አቅርቦት እጥረቶችን በተለመከተ የሚወጡ ሪፖርቶችን እንደማይቀበል ማሳወቁ ይታወሳል:: ይሁንና ባለፈው የካቲት ወር የአገሪቱ እምባ ጠባቂ ተቋም የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በረሃብ ምክንያት 400 ሰዎች ሞተዋል ሲል መግለጫ የሰጠ ሲሆን ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ በረሃብ እየሞቱ ያሉ ሰዎች የሉም” ብለው ነበር።አስ