ርዕሰ አንቀፅ
በመታየት ላይ ያለ

ርዕስ አንቀጽ: በአዲስ አበባ ግዜውን ያልጠበቀና ያለበቂ ዕቅድ እየተተገበረ የሚገኘው ከተማዋን የማነጽ ስራ አቅመ ዳካሞች ላይ ጫና ፈጥሯል፣ ቢያንስ ሂደቱ ሰብአዊነትን ሊላበስ ይገባዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም፡- የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ባለስለጣናት አዲስ አበባ በከንቲባዋ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በታሪኳ አይታው በማታውቀው ሁኔታ እየተለወጠች ትገኛለች በሚል በኩራት ሲናገሩ ይደመጣል። ባለስልጣናቱ ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል በቅርቡ በከተማዋ በተለዩ አምስት የመንገድ ኮሪደሮች ከ40 ኪሎሜትር በላይ በመገንባት ላይ ያለውን ከተማዋን የማሰዋብ ስራ ይጠቅሳሉ፤ መዲናዋን ዘመናዊ በማድረግ እንደ ስሟ አዲስ አበባ እንድትሆን እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ስራ ነው ሲሉ ይደመጣል። 

ከተማዋን የተመቸች ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ግን በማፍረስ ላይ የተመሰረተ ሁኗል፤ የከተማዋን ነዋሪዎች በሚያሳምም ሁኔታ በብርሃን ፍጥነት እየተተገበረ ነው፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት እና የአምልኮ ስፍራዎችን በማፈራረስ ላይ ይገኛል።

ብዙም ትኩረት ካልተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የከተማው ድሆች የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡበት ትክክለኛ ሰነዶች አለመኖር ሲሆን ይህም እነዚህን የማህበረሰቡ ክፍሎችን ለዘላቂ የቤት እጦት አደጋ የሚጥል ነው

የከተማዋ በድህነት ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚኖርባቸው ከሁለት ሺ በላይ ንብረትነታቸው የመንግስት የሆኑ ቤቶች፣ መንግስት ሲያከራያቸው የነበሩ ተጨማሪ 400 ቤቶች፣ 300 ንብረትነታቸው የግል የሆኑ መኖሪያና የንግድ ቤቶች፣ ለሀይማኖት ተቋማት የገቢ ምንጭ የሆኑ መደብሮች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግዜያዊ መጠለያዎች፣ የኮንቴነር ሱቆች በአንድ ሳምንት ግዜ ውስጥ ማፍረስ ያለጥርጥር ለዘመናት የተመሰረተውን የህብረተሰቡን የእርስ በርስ ግንኙነት ላይ ተጽእኖው ከባድ ነው።

በከንቲባዋ አዳነች አቤቤ አፍ እንደተገለጸው በፒያሳ አከባቢ ብቻ በተከናወነው ፈረሳ ከ11 ሺ በላይ ሰዎች ተነስተዋል። በመካሄድ ላይ ያለው ፈረሳ ተጽእኖው በደረሰባቸው ማህበረሰብ ክፍሎች የፈጠረውን ቀውስ ለመረዳት ማሳያ የሚሆን ነው።

ምንም እንኳ የከተማ አስተዳደሩ ቤታቸው የፈረሰባቸውን ሰዎች ወደተሻለ መኖሪያ ስፍራ እንዲዘዋወሩ እና ተለዋጭ መኖሪያ ቤቶችን በመስጠት ስራው ላይ ውጤታማ እንደሆነ ቢገልጽም የአዲስ ስታንዳርድ ቡድን ዘገባን ጨምሮ በርካታ ሪፖርቶች አስተዳደሩ በይፋ የሰጠው መግለጫ እና መሬት ላይ ባለው እውነታ መካከል ወሳኝ ልዩነቶች መኖራቸውን የሚያመለክቱ ፍንጮች አሉ።

በተለይም ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በተሰጠው የካሳ ክፍያ እና በልጆች ትምህርት ቤቶች ድንገተኛ ለውጦች እንዲሁም እንደ ጤና አገልግሎቶች ባሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ የተደረገበት ግዜ ተጠቃሽ ናቸው።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ብዙም ትኩረት ካልተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የከተማው ድሆች የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ትክክለኛ ሰነዶች አለመኖር ሲሆን ይህም እነዚህን የማህበረሰቡ ክፍሎችን ለዘላቂ የቤት እጦት አደጋ የሚጥል ነው።

በፒያሳ የሚገኙት እንደ ዶሮ ማነቂያ ያሉ ሰፈሮች ጎስቋላ እና ለሰው ልጅ መኖሪያነት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች፣ እንደ መጸዳጃ እና ንጹህ ውሃ የሌሉበት ለኑሮ የማይመቹ መሆናቸው እሙን ነው።  ነገር ግን መረሳት የሌለበት በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘው የማህበረሰብ ክፍል እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት የሚቋቋሙበት ቦታ ነው። እነዚህ አከባቢዎች በዘመናት ሂደት በተፈጠረ መልካም ጉርብትና በተሞላበት አኗኗር ችግረኞች በመተጋገዝ ኑሮን የሚገፋበትም ነው።

ምንም እንኳ ከዚህ አከባቢ እንዲነሱ የተደረጉ ሰዎች የተሻለ ቤት ቢሰጣቸውም (ብዙዎች ደግሞ ቃል የተገባላቸውን መኖሪያ በመጠባበቅ ላይ ናቸው) ለዘመናት የመሰረቱትን እና የተላመዱትን አኗኗር በማጣት አስቸጋሪ ከሆነው እውነታ ጋር መጋፈጣቸው አይቀሬ ነው፤ እንዲሁም በሚዛወሩበት አከባቢ ከሚሮረውን የኑሮ ውድነት ጋር ግብግብ መግጠማቸው የማይቀር እውነታ ይሆናል።

የመንገድ ኮሪደር ልማቱ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን በአራት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ሲኤምሲ እና መሰል ቦታዎች የሚገኙ አነስተኛ ንግድ ስራዎችን ማስተጓጎሉ አይቀሬ ነው።

የዚህ ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ከንግድ ባለቤቶች በላይ የሚዘልቅ ሲሆን ከከተማው ርቀው የሚገኙትን ቤተሰቦቻቸውንም በር ማንኳኳቱ የማይቀር ነው።

በጣም ጥሩ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ቢሆን ከአዳዲስ ቦታዎች እና ገበያዎች ጋር መላመድ አዳጋች መሆኑ አይቀርም፤ ለነጋዴዎቹም ሆነ ለደንበኞቻቸው ሊተመን የማይችል ዋጋ በመክፈል የሚያገኙት ነው የሚሆነው።

ይህ ሁሉ ደግሞ በአንድ ሳምንት ሲተገበር የሚያመጣው ጣጣ ብዙ ነው፤ በየጊዜው የሚስተጓጎሉ አቅርቦቶችን ጨምሮ በአስደንጋጭ የዋጋ ግሽበት በመታመስ ላይ ላለችው አዲስ አበባ ተጽእኖው ለቀጣይ አመታት የሚንከባለል ይሆናል።

የሚዲያ ተቋሙ ርዕስ አንቀጽ በከተማዋ የሚካሄደውን ልማት በመጻረር አለመሆኑን ልብ ሊባል ይገባል። ደረጃውን የጠበቀ እና የተሻሻለ የመንገድ አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቦታ፣ የህዝብ ትራንስፖርት፣ ፍጆታዎች እና አረንጓዴ ስፍራዎች እጅግ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ መሆናቸውን እንረዳለን።

ነገር ግን እንቆቅልሽ የሚሆነው መንግስት ይህንን ግዙፍ የማፍረስ ተግባር የሚከናውነው ለምንድ ነው የሚለው ሲነሳ ነው፤ እንደመንግስት ገለጻ ፈረሳው በመካሄድ ላይ የሚገኘው የከተማዋን ገጽታ ለማሻሻል፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መስመሮችን ለመፍጠር ነው የሚል ነው። 

ይህ ግብ በራሱ ጠቃሚ ቢመስልም በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የህይወት መስመር በማወክ ሊሆን ግን አይገባም።

ይህ ውግንናው በተለይ መንግስት በቅርቡ የውጭ ዜጋ ባለሀብቶች መሬትን ጨምሮ ንብረት እንዲኖራቸው ለማድረግ አዋጅ እንደሚያወጣ ከማስታወቁ በግልጽ ይታያል። በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን እውነታ ሊነቁበት አልቻሉም።

60 በመቶ የሚሆነው ህዝቡ በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚኖርበት መንግስት፣ ከተማ ማስዋብ ቀዳሚ ተግባሩ መሆን አልነበረበትም። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ እጥረት ገጥሟታል።

ለቤት ፈረሳ፣ ለካሳ ክፍያ እና ለመንገድ ኮሪደሮች ግንባታ የተመደበው በጀት በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት ጥቅም ላይ ሊውል በቻለ ነበር።

እርግጥ ነው አስፍተን ካየነው የመዲናዋን እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመከናወን ላይ ያሉ መሰል ፕሮጀክቶች የሚያመላክቱት ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከቀደመው የኢህአዴግ፣ ለድሃው ከነበረው ውግንና ከሚያሳዩ የፖሊሲ ስልቶች በመውጣት በተቃራኒው ለባለጸጎች መወገኑን የሚያመላክት ነው።

ይህ ውግንናው በተለይ መንግስት በቅርቡ የውጭ ዜጋ ባለሀብቶች መሬትን ጨምሮ ንብረት እንዲኖራቸው ለማድረግ አዋጅ እንደሚያወጣ ከማስታወቁ በግልጽ ይታያል። አለመታደል ሁኖ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን እውነታ ሊነቁበት አልቻሉም።

ወቅቱ የሚያዘው እንደዚህ አይነት ሰፊ የከተማ ለውጦች ሲከናወኑ በዋነኛነት ድሃውን እና ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ክፍል በመጉደትም ቢሆንም መተግበር እንዳለባቸው ከሆነ እንኳ በትንሹ ባለስልጣናቱ ህዝቡን በስርአቱ በማወያየት ሊሆን ይገባው ነበር። በማስከተልም ሂደቱ ለከተማው ድሃ እና ጭቁን ማህበረሰብ ሸክም በማይሆን መልኩ ዝፍጅቶች መከናወን ነበረባቸው።

የቀረበው የመከራከሪያ ሀሳብ የዘገየ እና ውሳኔውን ማስቀልበስ የማይችል ክርክር ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ይህ መከራከሪያ ሀሳብ መቅረቡ ቢያንስ፣ የአስተዳደሩ ባለስልጣናት ቀጣይ ባሉ ሂደቶች ጨዋነት የተላበሰ፣ ሰብአዊነት የተሞላበት አካሄድ እንዲከተሉ ለማድረግ ተጽእኖ ማሳደር ይቻላል።

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button