ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል “ከ1967 ዓ/ም ወዲህ ትልቅ” የተባለ የቀበሌ አደረጃጀት ስራ ላይ ዋለ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 28/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል “ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እና ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ” በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ አዲስ የአስተዳደር አደረጃጀት ከትላንት ነሀሴ 27፣ 2016 ዓ/ም ጀምሮ በስራ ላይ መዋሉ ተገለጸ።

የክልሉ መንግስት በስራ ላይ ያዋላው አዲስ አደረጃጀት፤ “ወደ ሰፊው ማህበረሰብ የመቅረብ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል፣ ሰላምን የማስፈን፣ የወል ፍትህ እና መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ እንዲሁም ጠንካራ መንግስት የመገንባት” ቀጠሜታ እንዳለው ተጠቁሟል።

ይህ አዲስ አደረጃጀት በሁሉም የገጠርና ከተማ ቀበሌዎች በስራ ላይ መዋሉን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስረጃጀቱን በማስመልከት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ማብራሪያ፤ የክልሉ መንግስት፤  የቀበሌ አደረጃጀቱ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠት ያሚያስችል ይሆናል በሚል ከዚህ በፊት የነበረውን አደረጃጀት በድጋሜ እንዲዋቀር ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ይህም “ለመጀመሪያ ጊዜ 1967 ዓ/ም የቀበሌ አደረጃጀት ከተዋቀረ ወዲህ፤ መንግስት ወደ ህዝቡ ለመቅረብ የተደረገ ትልቁ ውሳኔ ነው” ብለዋል። 

በቀበሌዎች ሰፊ የልማት ፍላጎቶች እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት መኖሩን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ በዚህ መሰረት የክልሉ መንግስት ከቀበሌዎች ጀምሮ የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ አደረጃጀቶች እንዲዋቀር ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። “ይህ ተግባር መንግስት እስከ ቀበሌ ድረስ ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ነው” ብለዋል።

“ከ1967 ዓ/ም በኋላ አሁን እየተካሄደ ያለውን ታሪካዊ የቀበሌ አደረጃጀት ውሳኔ  ለማስተላለፍ፤ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ መግባባት ላይ መድረስ ግዴታ ነበር” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ አዲሱ አደረጃጀት ውስጥ ከተመደቡ አመራሮ እና ሠራተኞች ጋር መግባባት ላይ መደረሱንና የህዝብ ውይይት መቀጠሉን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዚሁ ሁኔታ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ወረዳ እና የቀበሌዎች ውስጥ በየደረጃው የአደረጃጀት ድልድል መካሄዱን እና አዲሱ አደረጃጀት ስራ ላይ እየዋለ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። 

የክልሉ መንግስት የአደረጃጀት ለውጥ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያ አይደለም። በጥር ወር “የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ለመመለስ እንዲሁም ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር  ድንበር ላይ  የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት” የከተሞች እና የቀበሌ አደረጃጀቶችን በአዲስ መልክ ማዋቀሩን አስታወቆ ነበር።

በዚህም አደረጃጀት ምስራቅ ቦረና ዞን 12ኛ ዞን ሆኖ እንዲደራጅና መቀመጫውም ነጌሌ ቦረና እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ የጎሮ ዶላ እና ሌሎች በምስራቅ ቦረና ስር የተደራጁ ቀበሌዎች አደረጃጀቱን በመቃወም ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button