አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19/ 2016 ዓ/ም፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በተከሰተ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የሰዎች ህይወት ማለፉና በርካቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን በዴቻ ወረዳ ሞዲዮ ጎምበራ ቀበሌ ትላንት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ 3 የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በአንድ ሰው ላይ የአካል ጉዳት ድርሷል። በአደጋው 24 የአከባቢው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውም ተገልጿል።
የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት አደጋው መከሰቱን ገልጸው በአከባቢው ላይ ከባድ የሆነ የናዳ አደጋ ስጋት በመኖሩና በርካታ ቤቶች ለአደጋው ተጋላጭ በመሆናቸው ተፈናቃዮቹ በቀበሌው በተለያዩ የመንግስት ተቋማት እንድጠለሉ ተደርጓል ብለዋል።
በዞኑ አደጋ ልከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።
በዴቻ ወረዳ ሞዲዮ ጎምበራ ቀበሌ በተከሰተው ድንገተኛ ናዳ ምከንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ የቤተሰብ አባላት የተለያየ የሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
የዝናቡ ሁኔታው ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በተሰጠባቸው የዞኑ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጥሪ ተላልፏል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ቀበሌ በጣለው ከባድ ዝናብ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት ናዳ አደጋ መከሰቱ ገልጿል።
የመሬት መንሽራተት አደጋው በቃዳ ማዬ፣ ፉንጡሌ፣ በሻሻና ባርሶማ ውስጥ መከሰቱን ያስታወቀው የጎማ ዞን ኮሚዩኒኬሽን፤ በአደጋው የሞተ ሰው አለመኖሩን ገልጿል።
እነዚህ የመሬት ናዳ አደጋዎች የተከሰቱት በርካታ ሰዎች ህይወት ያለፈበት አስደንጋጭ የመሬት ናዳ አደጋ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን መከሰቱን ተከትሎ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 በተከሰተው ከፍተኛ የመሬት ናዳ አደጋ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባቢያ ጽ/ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።
በጎፋ የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቁጥር 500 ሊደርስ ይችላል ያለው ድርጅቱ ከ15 ሺ በላይ የሚሆኑ የአከባቢው ነዋሪዎች አሁንም ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ናቸው ብሏል።
በደረሰው አደጋ ከ500 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገልጸዋል። ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል። አስ