ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በደራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ፣ በሰላሌ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ 400 ተማሪዎች ወደ ቤታችን መመለስ አልቻልንም ብለዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም፡- በኦሮምያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎቸ በፈጸሙት አዲስ ጥቃት ሶስት ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ አንድ ነዋሪ መቁሰሉ ተገለጸ። ጥቃቱን የፈጸሙት የፋኖ ታጣቂዎቸ ናቸው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው የደራ ወረዳን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስነው ኢሉ ጎዳ ጨፌ ቀበሌ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑን የጠቀሙት ነዋሪዎቹ በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌዎች በአንጻራዊነት ብዙም ጥቃት የማይስተዋልበት እና የተረጋጋ ነበር ብለዋል።

ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀው በአከባቢው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በነበረው ግጭት ታጣቂዎቹ ኡዌ ግርማ፣ አብዱ ኢብራሂም፣ አብዱልዋሂድ ጀማል የተባሉ ነዋሪዎች ገድለዋቸዋል፤ አብዱ ሰይድ የተባለ ነዋሪን አቁስለዋል ብሏል። በተጨማሪም አንድ የፖሊስ አባል መቁሰሉን አስታውቋል።

በአከባቢው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጡ እና በፍቼ ከተማ በሚገኘው የሰላሌ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ከሁለት ሳምንት በፊት የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ 400 የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ መጡበት አከባቢ መመለስ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል። በአከባቢዎቻቸው በመካሄድ ላይ ያሉት የታጣቂዎች ግጭት ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል።

ቦንቱ ግርማ የተባለች የሶሻል ሳይንስ ተማሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀችው በሰላሌ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ከሁለት ሳምንት በፊት ፈተናዋን ተፈትና ብታጠናቅቅም ወደ መጣችበት መመለስ አለመቻሏን ተናግራለች። መቸ እንደምመለስ አላውቅም ስትል ገልጻለች።

ፍስሃ አባተ የተባለ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ በበኩሉ ከሳምንት በፊት በዩኒቨርስቲው በመገኘት የ12 ፈተና ወስዶ ቢያጠናቅቅም ወደ መጣበት አከባቢ መመለስ ባለመቻሉ በዩኒቨርስቲው ከጓደኞቹ ጋር እንደሚገኝ አስታውቋል። ወደ ቤታችሁ በዚህ ሳምንት ትሔዳላችሁ ተዘጋጁ ተብለው እንደነበር የገለጸልን ተማሪ ፍስሃ ነገር ግን የአከባቢው ባለስልጣናት እንደገና ቆዩ ብለውናል ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የነገሩን ልጃቸው ለፈተና ወጥቶ አለመመለሱን የነገሩን ወላጅ በበኩላቸው የተማሪ ወላጆች የደራ ወረዳ ባለስልጣናትን እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎችንን ማነጋገራቸውን አስታውቀው ነገር ግን እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጡንም ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም ከደራ ወደ ፍቼ በሚወስደው መንገድ የፋኖ ታጣቂዎቸ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና የመከላከያ ሀይሎች እርስ በርሳቸው በተደጋጋሚ የሚዋጉበት በመሆኑ አስቸጋሪ ነው ብለዋል፤  በጸጥታ ችግር መንገዱ ጥገና ተደርጎለት ስለማያውቅ ለመጓጓዝ እንደማያመችም ጠቁመዋል።

በአከባቢው እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ ችግር ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ የአከባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል፤ አብዘሃኛዎቹ ገበሬዎች ሲሆኑ መሬታቸውን ማረስ ባለመቻላቸው ጥለው ተሰደዋል።

በወረዳዋ ከሚገኙ መንደሮች አንዷ በሆነችው ደንዩ ውቤንሶ ነዋሪ የሆነው እና በእርሻ ተግባር እንደሚተዳደር የገለጸልን ሰለሞን ውቤ ቀያቸውን እና የሚታረስ መሬታቸውን ጥለው ወደ አጎራባቻቸው የአማራ ክልል ከተሰደዱ መካከል አንዱ ነው።

የአምስት ልጆች አባት የሆነው ሰለሞን ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀው ወደ ቀየው መመለስ ማለት ቤተሰቦቼን ለአደጋ ማጋለጥ ነው የሚሆነው፣ ምክንያቱም ደግሞ የፋኖ ሀይሎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና የመከላከያ ሰራዊቱ በአከባቢው እርስ በርስ ውጊያ ያካሂዳሉና ብሏል።

“እርዳታ እየለመን እንገኛለን፤ መንደራችንን፣ ከብቶቻችንን እና መሬታችንን ለቀን ተሰደናል። አምና ባካሄድኩት እርሻ 60 ኩንታል ምርት እጠብቅ ነበር፣ ግን መና ቀርቷል። መንግስት የተደራጀ የጸጥታ ሁኔታ ያስከብርልን እና ወደ ቀያችን እንመለስ የሚል ጥያቄ ብናቀርብም ሁለተኛ እንዳትጠይቁ የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን” ሲል ገልጿል።

የወረዳው የግብርና ሃላፊ አባተ አለሙ በፋኖ ታጣቂዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በተቆጣጠሯቸው  የወረዳው በርካታ መንደሮች የሚገኘው የእርሻ መሬት አለመታረሱን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። በአካባቢው በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ሳቢያ ማረስ አልተቻለም ብለዋል።

ለእርሻ ተግባር የሚውሉ እንደ ምርጥ ዘር፣ ጸረ ተባይ እና መሰል ግብአቶችን በጸጥታ ችግር ወደ አካባቢው ማጓጓዝ አለመቻሉንም ጠቁመዋል።

ተፈናቃይ ገበሬዎቹን ወደ እርሻ መሬታቸው ተመልሰው የግብርና ስራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማድረግ የደራ ወረዳ የጸጥታ ምክር ቤት ሁኔታዎችን እያጤነ ይገኛል ሲሉ የግብርና ሃላፊው ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button