ባህል እና ጥበብዋና ትረካ
በመታየት ላይ ያለ

ትረካ፡ “በስዕል ሥራዎቼ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በማስተዋወቅ ላይ ነኝ” – ስዕሉን የአይርላንዳ ባንድ የአልበሙ ሽፋን ያደረገለት ወጣት ሰዓሊ ሲሳይ ተሸመ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24/ 2015 ዓ.ም፡- ስዕል የሰዎችን ቀልብ የመሳብ አቅም ያለው፣ የማህበረሰብ ብሎም የሀገር ውክልና የሆኑ እሴቶችን፣ ባህልን፣ መገለጫዎችን እንዲሁም የተለያዩ መልዕክቶችን በውብ ቀለማት ስብጥር መግለፅ የሚቻልበት፣ በብዙኃኑም የሚወደድ አንዱ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡  ቀለማት ተደባልቀው፣ ብሩሽና ሸራ ሲገናኙ የሚፈጠረው “ስዕል” እንደ ሰዓሊው እይታና የመሳል ችሎታ ልዩ ልዩ መልዕክቶችን የማስተላለፍና ውበትን የማጉላት ተግባር ሲያከናውኑ ለዘመታት ቆይተዋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በዚህ የጥበብ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለየት ያሉ የአሳሳስል ዘዴን በመጠቀም ስዕሎችን በመሳል ላይ ከሚገኙ ስኬታማው ወጣት ሰዓሊያን መካከል ሲሳይ ተሾመ አንዱ ነው፡፡

ሰዓሊና ፀራፂ ሲሳይ ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል ደብረ ሲና ከተማ ሲሆን ከአንደኛ አስከ አስረኛ ክፍት ያለውን ትምህርቱን በዚያው ተከታትሏል፡፡ ኪዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በ2006 ዓ.ም. ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቅርፅ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው ሲሳይ ወደ ስዕል የገባበትን አጋጣሚ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ ሲያስረዳ ከልጅነት ጀመሮ ስዕል መሳል እንደሚያዘወትር፣ በተለይም ለዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ በዓል ስዕሎችን በመሳል እንደሚያሳልፍ አስረድቷል፡፡ በልጅነቱ ያደረበት የስዕል ፍቅር እያደገ በመምጣቱ አሁን ላለበት የሰዓሊነት እና ቀራፂነት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡

“ስዕል መሳል የጀመርኩት የአስር አመት ልጅ ሳለሁ ነው” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለፀው ሲሳይ “ስዕል ማለት ለእኔ የኣዕምሮ እረፍት ነው፣ ሲከፋኝ ከዛ ስሜት የምላቀቅበት፣ ሌላ አለም የማይበት፣ ችግሮቼን የምረሳበት፣ ሰላምን የማገኝበት ነው” ሲል ሰዓሊነት ለእሱ ያለውን ትርጉም ገልጿል፡፡ ሲሳይ ስዕል ለአዕምሮ ህሙማን እንኳ የሚመከር፤ እንደ ህክምናም የሚያገለግል የኪነ ጥበብ ዘርፍ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲሳይ የሚስላቸው ስዕሎች ፖርትሪየት ከሚባ የአሳሳል ዘውጅ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን ቀለም እና ሸራን አንድ ላይ ሲያገናኛቸው የሚገኘው ውጤት የኢትዮጵያውያንን እና በአጠቃላይ የአፍሪካን ውበት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ስራዎች ናቸው ለማለት የሚያስደፍሩ ናቸው፡፡ በበርካታ ስዕሎቹ ላይ ጎልቶ የሚታየው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ መልክ ያለቸው ሴቶች የውጭ ሀገራ ዜጎችን ሳይቀር የበርካታ ሰዎችን ቀልብ የሳበ መሆኑን ባለታሪኩ በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ስዕሎቼ ፖርትሪየት አርት ከሚባሉት የአሳሳል መደብ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የምታውቀው የራሴን ስልት በመጠቀም ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ውስጥ ያሉ ባህልን ለማሳየት ለየት ያሉ ስዕሎችን በመሳል ነው” ሲል ሲሳይ አስረድቷል፡፡

ሰዓሊው ይበልጥ እውቅናን ያስገኙለት ስዕሎቹ የሴቶች ፊት ገፅን በመሳል በእሱ ላይ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ያሉ ባህሎችን፣ ጌጣጌጦችን፣ አልባሳትን ለማሳየት የሚስላቸው ስዕሎቹ መሆናቸውንም ይናገራል፡፡

ይህን ለየት ያለ የአሳሳል አይነት ይዞ እንዲመጣ የረዳው የተለያዩ የሀገራችንን ባህልና ልዩ መገለጫዎችን ማወቁ መሆኑን የሚናገረው ሲሳይ የኢትዮጵያ እንዲሁም የአፍሪካ አልባሳት፣ ቀለም እንዲሁም የሴቶቹ ውበት ከሌላው አለም የተለየ መሆኑን ለማስተዋወቅ ስዕሎቹን እንደሚጠቀምባቸውና ይህንንም ልዩ መገለጫችንን ለሌላው አለም ለማስተዋወቅ እየሰራ እንሚገኝ ገልጿል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙት ስካይ ላይት፣ ቤስት ዌስተርን ፐላስ እና ኢሊሊ ሆቴልን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ድርጅቶች ውስጥ ስዕሎቹ በክብር ተሰቅሎ ድምቀት ሆነዋል፡፡

ይህ ወጣት ኢትዮጵያን እና አፍሪካን የሚወክሉ ሴቶችን በመጠቀም የራሱ በሆኑ የአሳሳል መንገድ የሚስለው ስዕል ከኢትዮጵያ አልፎ በሀገረ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ አይርላንድና በሌሌች የውጭ ሀገራት  በብዛት እንደሚሸጥና ተመራጭ እንደሆኑለት ይናገራል፡፡ በተለይ ፈረንሳይ የሚገኙ በርካታ ካፌዎች የኢትዮጵያን ባህል በሚያሳዩ ስዕሎቹ እናዳሸበረቁ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አይርላንድ የሚገኝ “ላዛረስ ሶው” የሚባል የሚዚቃ ባንድ የአልበሙን ሽፋን የተጠቀመው የዚህን ወጣት ሰዓሊ ስራን ነው፡፡  ስዕሉ የአልበሙ ሽፋን ከመሆኑ በተጨማሪ በክሊፖቹ፣ በሚያከናውኑት ኮንሰርቶችም ጭምር እንደመለያቸው እንሚጠቀሙበት ሲሳይ ገልፆልናል፡፡

“ስራዎቼን በብዛት የሚገዙት ነጮች ናቸው፣ በስዕሎቼ በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ሁሌም ይነግሩኛል፡፡ እነዚህ ስዕሎች የሀገሬ መገለጫዎች ናቸው” የሚለው ሰዓሊው በውጭ ሀገራት ካፌዎች፣ ሆቴሎች መኖሪያ ቤት ውስጥ ተሰቅለው ሳይ ሀገሬን አፍሪካዊነትን እያስተዋወቅኩ እንደሆነ ስለሚሰማኝ በጣም ደስተኛ ያደረገኛል ይላል፡፡

ይህ ወጣት ሰዓሊ በአንድ አይነት የአሳሳል ብቻ የተገደበም አይደለም፣ ይልቁንም ፖላሪ የሚባል ጋዜጣ ወይም መፅሔቶችን በመቆራረጥ የሚሳል ስዕሎችንም ይሠራል፡፡ ከሰዎች ጋር በሰፊው ያስተዋወቁት ግን ፖርትሪየት ስራዎቹ ናቸው፡፡  በዋናነት ፖርትሪየት አሳሳልን እንደሚያዘወትር የሚናገረው ሰዓሊው የስዕሉ ይዘቶች ከሌሎች የተለዩ መሆኑንና ሰዎች ስዕሎቹን ሲያዩ ይህ የሲሳይ ስዕል ነው ብለው በቀላሉ እንዲለዩት ማስቻሉን ያምናል፡፡

ስዕሎቹ በውጭ ሀገራት ዜጎች ተመራጭ እንዲሆኑ ያደረገው ምንድነው?

ሲሳይ ስዕሎቹን ለመሳል የሚጠቀምበት አቃዎች ሌሎች ሰዓሊያን ከሚጠቀሙበት የተለየ አለመሆኑን ነገር ግን የሚያስተላልፉት ሃሳብ እንደሚለይና በዚህም ምክንያት ሰዎች እንደሚወዱት ይገልፃል፡፡ “ስዕሎቼ የሚያቀነቅኑት ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ስዕሎች የሚያሳዩት የአፍሪካን ሴት አለባበስ፣ ጌጣጌጥ፣ ባህል  በመሆኑ የየትኛውም አለም ሰው ስዕሎቹን ሲያይ የሚያስበው አፍሪካን ነው” ብሏል፡፡

በርካታ ስዕሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ነጮቹ የሚያውቁትን ሀሳብ ስለሚያካትቱ ብዙም አያስደንቃቸውም የሚል እምነት ያለው ሲሳይ እሱ ከዚ ለመለየት ሲል አሁን በስፋት የሚስላቸውን ስዕሎች እንደሚሰራ ይናገራል፡፡

“ውበት በሴት ይገለፃል” የሚለው ሲሳይ ስዕሎቹ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች የስዕል አፍቃሪያንን ቀልብ ለመሳብ ካስቻሉ ዋና ምክንያቶች አንዱ አፍሪካዊ መልክ ያላቸውን ሴቶች ከነመገለጫቸው አጉልቶ ለማሳየም መሞከሩ እንደሆነ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡

የስዕል ገበያ በኢትዮጵያ

የስዕል ስራ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚለው ሲሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስገኘው ገቢ ከሌላው አለም ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡   “በእኛ ሀገር ሰዎች ለስዕል ያለቸው ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑ የስዕል ገበያው አስደሳች አልነበረም፤ አሁን ላይ ግን ሰዎች ላይ ስዕል የመግዛት አዝማሚያ እየተስተዋለ በመሞኑ እየተሸሻለ ይገኛል”፡፡

ሰዓሊው ህይወቱን የሚመራው በዚሁ ስራ ብቻ ሲሆን በተለይ ለውጭ ዜጎች ከሚሸጠው ስዕል ጥሩ ገቢ ያገኛል፡፡ በአንድ ስዕል እስከ 60 ሺ ብር እና ከዛ በላይ እንደሚያገኝ የነገረን ሲሳይ አሁን ላይ የሀገሪቱ ሰላም መደፍረስ ስዕሎችን ለቱሪስቶች በመሸጥና ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘውን ገቢ ቀንሶታል ብሏል፡፡

የቤተሰብ ድጋፍ

ተምሬ ትልቅ ቦታ እንድደርስ እንጂ ሰዓሊ እንድሆን ቤተሰቦቼ ፍላጎት አልነበራቸውም የሚለው ወጣቱ በዚህም የተነሳ የሚገጥሙትን ፈተናዎች በራሱ ጥረት እንደተወጣቸው ይገልፃል፡፡ “ ተማሪ እያለሁ ትልቅ ፈተናዎች ነበሩብኝ ሲል የገለፀው ሲሳይ፣ ቤተሰቦቹ ትምህርቱን ጨርሶ ተቀጥሮ እንዲሰራ ይፈልጉ የነበር በመሆኑ ይህን ባለማድረጉና ሰዓሊነቱን በመምረጡ ቤተሰቦቹ በሚያስፈልገው ነገሮች ድጋፍ አያደርጉለትም ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዓሊ የመሆን ህልሙን በራሱ ጥረት እውን አድርጎ የቤተሰቦቹን ሀሳብ ማስቀየር ችሏል፡፡ በሰዓሊነቱ ጠንክሮ የገፋው ሲሳይ ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረስ የቤተሰቦቹ ሀሳብ በማስቀየር በስራው ደስተኛ እንዲሆኑ መድረግ ችሏል፡፡

ሰዓሊ ለመሆን ተሰጥኦ ውይት ትምህርት

የትኛውም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት መጀመሪያ ተስጥኦ እንደሚያስፈልግ የሚያምነው ሲሳይ ትምህርት ተሰጥኦን ለማሳደግ ይረዳል ባይ ነው፡፡ “ የሚያምር ድምፅ ከሌለህ ዘፋኝ መሆን አትችልም፤ ሰዓሊ ለመሆንም ውስጥህ ምንም ነገር ሳይኖርህ ብትማር ትርጉም ያለው ነገር መስራት አትችልም፤ ስለዚህ ተሰጥኦ አስፈላጊ ነው” ብሏል፡፡

የስዕል ስራ ትእግስት የሚያስፈልገው የጥበብ ዘርፍ ነው ሲል የሚናገረው ሰዓሊው ከላይ ካልተሰጠህ ሳትሰለች ለረጅም ሰዓታት ሰቱዲዮ ውስጥ ቁጭ ብለህ መሳል አትችልም፤ ወጣቶች ወደዚህ ስራ ለመግባት ፍላጎት፣ አለመሰልቸት፣ ጥረት፣ ብርታት ሊኖራቸው ይገባል ሲልም መክሯል፡፡

የሚገጥሙህን ፈተናዎች ሁሉ የምታለፈው ስራውን ስትወደው ነው፣ ህልምህን ለማሳካት ፍላጎቱ ካለህ ሳትበላም ብታድር ምንም መስሎ አይታይህም ይላል፡፡

ለወጣቶች ያለውን ምክርም ሲያጋራ “ፈተናዎች ሲገጥሙን ለምክንያት ነው ብሎ በማመን ተስፋ አለመቁረጥ ይገባል፡፡ ፈተናዎች ውስጥ ስትሆን ብዙ ትምህርቶችን ትማራለህ፤ እንዚህ ትምህርቶች ደግሞ ህይወትህን ሊለውጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ በየትኛውም ፈተና ተስፋ ካልቆረጥክና እጅ ካልሰጠህ ስኬታማ የማትሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም” ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሙያውን ወዶ መስራት፣ መጣር፣ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር መሞከር ውጤት እንዲገኝ የሚያስችሉ ቁልፎች ናቸው ብሏል፡፡

የወደፊት እቅድ

ሲሳይ አሁን አየረሰራበት ያለውን የአሳሳል ዘዴን በመጠቀም በአለም አቀፍ ደረጃ አሁን ያገኘው ተቀባይነት የበለጠ ለማሳደግ አቅዷል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋዋር የስዕል አውደ-ርዕይ በማዘጋጀት ከአድናቂዎቹ ጋር መገናኘት እና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ማቀዱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button