ዜናፖለቲካትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ትንታኔ: በግድያ እና ሰብአዊ መብት ጥሰት ታጅቦ የተራዘመው የአማራ ክልል አስቸኳይ ግዜ አዋጅ

በዘላለም ታከለ @ZelalemTakelee

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16/2016 ዓ.ም፡- ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር በ30 ኪሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው የመራዊ ከተማ በጥር ወር መገባደጃ ላይ የተሰማው መረጃ እጅግ አሳዛኝ እና የሚረብሽ ነበር።

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኝ የወታደሮች ካምፕ ላይ ታጣቂዎች የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎ በከተማዋ ቤት ለቤት እየዞሩ በአከባቢው ስለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ነዋሪዎችን መጠየቅ እና ማሰስ መጀመራቸውን ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ፤ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ የዘፈቀደ ጅምላ ግድያ ሲፈጸሙ አደሩ ሲሉ ይገልጻሉ።

በቀጣዩ ቀን ከ14 አመት ታዳጊ እስከ የ94 አመት አዛውንት ባካተተ ግድያ ከመቶ በላይ የመራዊ ከተማ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ስለተጨፈጨፉባት መርአዊ ከተማ ወሬው በሁሉም ቦታ መዛመት ጀመረ።

ሁኔታው ከተፈጸመ ከቀናት በኋላ በከተማዋ መንገዶ የሞቱ ሰዎች አስከሪን በየቦታው ወድቆ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨት ጀመረ። እንደነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ የሟቾቹ አስከሬን ተነስቶ መቀበር የጀመረው ከቀናት በኋላ ነበር።

በከተማዋ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ሪፖርቶች መውጣት ጀመሩ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት በከተማዋ በጸጥታ ሀይሎች የዘፈቀደ ግድያ 45 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።

አስገራሚው ነገር በከተማዋ ጭፍጨፋው የተፈጸመው የሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ በክልሉ የታወጀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅን ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ድምጽ ከሰጠ ከቀናት በኋላ መሆኑ ነው።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንደ ፍትህ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ ገለጻ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማራዘም ያስፈለገው የክልሉን ህዝብ ሰላም እና ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ የሚል ነበር።

በመራዊ ከተማ የተፈጸመው ጭፍጨፋን ተከትሎ ብዙዎች የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መራዘም በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት ያመጣል መባሉን እንዲጠራጠሩት አድርጓል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስመሬ የፌደራል መንግስቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንዲራዘም ማድረጉን ከሚተቹ ሰዎች አንዱ ናቸው፤ ያልተጠና አሰልቺ አካሄድ ሲሉ ይገልጻሉ። እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ በኢትዮጵያ ታሪክ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ ነገሮችን ሲያባብስ እንጂ ችግር መፍቻ መንገድ ሁኖ አያውቅም።

“ባለፉት ዘመናት በርካታ የአስቸኳይ ግዜ አዋጆች በኢትዮጵያ ታውጀዋል፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል፤ ነገር ግን ዋነኛ ችግሮቹን ፈትተው አያውቁም። በተቃራኒው ችግሮችን ሲያባብሱ ነው ያስተዋልነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ።

ሲሳይ በተጨማሪም መንግስት ለህዝቡ ምሬት ትክክለኛ ምላሽ አለመስጠቱ፣ እና በጉልበት እፈታዋለሁ የሚለው አካሄዱ በክልሉ ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጉልበት እና ከለላ እንዲያገኙ አስችሏል ሲሉ ያብራራሉ፣ መንግስተ የታክቲክ ድል ያገኘ ቢመስለው እንኳ በህዝቡ ዘንድ ግን ቅቡልነት እና ድጋፍ በስፋ እያሳጣው ነው ብለዋል።

መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት እንደሚያራዝመው ተጠባቂ ነበር ሲሉ የገለጹልን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብት መምህሩ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በታወጀባቸው ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣት አለመቻሉን፣ በታችኛው የክልሉ አስተዳደር እርከን መቆጣጠር አለመቻሉ እና የክልሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተገደበ መሆኑን በምክንያትነት አቅርበዋል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ባይራዘም ኑሮ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ካምፕ ይገባል፤ ይህንንም ተከትሎ ታጣቂ ሀይሎቹ የክልሉን ከተሞች በመቆጣጠር እንደገና መጠናከር ያስችላቸው ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

በበርካታ የክልሉ ከተሞች የድሮን ጥቃቶች እና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካሄዳቸው የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ባለፉት ወራቶች በስፋት ወጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽንን (OHCHR) ጨምሮ በርካታ ተቋማት በክልሉ በድሮን፣ የጸጥታ ሀይሎች የሚፈጽሙት የዘፈቀደ ግድያ እና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል።

የሰብአዊ መብት ህጎች መምህሩ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የኢትዮጵያ ህገመንግስት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ክፍተት እንዳለበት ይገልጻሉ፤ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን በመጠቀም ለሚፈጽማቸው ጥሰቶች ከለላ ይሰጠዋል ብለዋል።

በአብነትም በህገመንግስቱ አንቀጽ 93 ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚደነግገው ክፍል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል የሚለውን ጠቅሰዋል።

የመርአዊ ከተማ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሁኔታውን እንደሚያጣራው ማስታወቁ ይታወሳል፤ መቼ እንደሚያከናውነው ጊዜውን ባያስቀምጥም በቦታው በመገኘት እመረምራለሁ ብሏል።

በመርአዊ የተፈጸመው ግድያ ከሀገር ውስጥ ተቋማት ይልቅ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሀገራት እና ተቋማት የሰላ ትችት አዘል መግለጫዎች ተሰንዝሮበታል፤ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት በአምባሳደሩ በኩል ያወጡት መግለጫዎች ተጠቃሽ ናቸው። ገለልተኛ ምርመራ ይደረግበት ሲሉ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብት ህጎች መምህሩ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የመመርመር ስልጣን ያለው በመንግስት በአዋጅ የተቋቋመው የመርማሪ ቦርድ ብቻ መሆኑን ገልጸው ቦርዱ ምርመራ ቢያከናውንም ዋነኛው ሃላፊነት እና ስራ ያለው መንግስት ላይ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

አለም አቀፍ እውነት አፈላላጊ እና የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት አጋዥ የሚሆን ምርመራዎችን ማቅረብ እንደሚችሉ ግን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ መርማሪ ቦርዱ ተከታታይ ሪፖርቶችን ይፋ አለማድረጉ እንደ ችግር የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል፤ ያለ ግልጽነት መርማሪ ቦርዱ ሃላፊነቱን እየተወጣነው ወይንም አይደለም ለማለት አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲው ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ በበኩላቸው አብዘሃኛዎቹ የሀገር ውስጥ እውነት አፈላላጊ እና የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት ከአለም አቀፍ ተቋማት በተቃራኒ በሆነ መልኩ ወይ ለገዢው ፓርቲ ያደሉ ናቸው አልያም ገለልተኝነት የማይታይባቸው ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ። በሀገሪቱ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ቢኖሩ ኖሮ ከመጀመሪያውም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ባልታወጀ ነበር ሲሉ ረዳት ፕሮፈሰሩ አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መራዘሙን በተመለከተ በርካታ ባለድርሻ አካላት ስጋታቸውን አስተጋብተዋል፣ ከነዚህም መካከል በኢትዮጵያ የአሜሪካን መንግስት አምባሳደር የሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ እና የሰብአዊ መብት ኪሞሽነሩ ዳንኤል በቀለ ይገኙበታል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየታቸውን የሰጡን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ሲሳይ መንግስቲም ስጋቱን እንደሚጋሩ ገልጸዋል። የጦር መሳሪያ ድምጽን ዝም በማስባል ወደ ውይይት መምጣቱ ብቻ ነው አዋጪው ብለዋል። ለተግባራዊነቱ ሁለቱም ተፋላሚዎች ሃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም የአንበሳውን ደርሻ ግን መንግስት ሊይዝ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

መንግስት ችግሩን በሃይል እፈታዋለሁ የሚለውን አካሄድ የሚቀጥልበት ከሆነ ግን በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያጣል፣ ታጣቂዎቹ በርካታ ሰዎችን የመመልመል እድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ሲሳይ አስመሬ አስጠንቅቀዋል። “በህዝቡ ላይ የተፈጠረውን ምሬት ከማባባስ ባለፈ ታጣቂዎቹን እና ህዝቡ ጽንፍ እንዲይዙ ያደርጋል” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተውናል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲው ሲሳይ አሰምሬ በበኩላቸው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የአከባቢው ነዋሪዎችን እና ታጣቂዎችን ጽንፈኛ ከማድረግ ያለፈ የፈየደው ነገር የለም ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።

“በመሳሪያ የተደገፈ ግጭት የሀዝብን ጠያቄ ከማጋጋለ እና የህዝቡን ፍላጎት ከማባባስ ያለፈ የሚፈይደው የለም” ብለዋል።

በተጨማሪም ይላሉ የጎንደር ዩኒቨርስቲው ሲሳይ አሰመሬ የክልሉ ህዝብ የፌደራል መንግስቱን አጥብቆ እየተጠራጠረው መጥቷል፣ የመከዳት እና ያለማመን ስሜቱ እየጎለበተ ነው ሲሉ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል።

የመገለጫ ጋጋታ በማውጣት ብቻ የፌደራል መንግስቱ ችግሮቹን ሊፈታ አይችልም፤ ይልቁንስ ችግሮቹን ለመፍታት የሚታይ ተግባር መፈጸም ይጠበቅበታል ብለዋል። በአብነትም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማንሳት መጀመር ይችላል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውነ አስቀምጠዋል።  ይህን በማድረግም መንግስት ችግሮቹን በሀይል ሳይሆን በመተማመን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳይበታል ሲሉ ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button