አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26/ 2016 ዓ/ም፦ ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ፤ ነሃሴ 8 በጄኒቫ ሊደረግ ስለታሰበው የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ውይይትን በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ ለጋዜጣዊ መግለጫ ሰጭተዋል።
በመግለጫው “በሱዳን እየተካሄደ ላለው አውዳሚ ጦርነት ብቸኛ መፍትሔው ሁሉን አካታች ውይይት እና ድርድር ነው::” ያሉት ልዩ መልዕክተኛው አክለውም ሁለቱም ተፋላሚ አካላት በራቸውን ለውይይት ክፍት እንዲያደርጉ እና ጦርነቱን እንዲያረግቡ ጥረት ላይ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።
ባሳለፍነው ረቡዕ ዕለት የሱዳን ጦር መሪ የሆኑት ጄኔራል አል ቡርሃን ላይ ተቃጥቶ የከሸፈውን የድሮን ጥቃት “አሳዛኝ” ሲሉ የገለጹት ልዩ መልዕክተኛው አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ ጉዳዩን በአንክሮ እየተመለከተችው እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ግጭት የሚፈጠሩ ሰብአዊ ቀውሶች ዩናይትድ ስቴትስን በእጅጉ ያሳስባታል ያሉት ፔሪሎ፤ በተጨማሪም አሜሪካ በሲቪል ሰዎች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እና በደል የፈጸሙ አካላት እንዲሁም የጦር ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎችን ልትጥል እንደምትችል ጠቁመዋል።
ነሃሴ 14፣ 2024 በጄኒቫ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ውይይት ሶስት ነገሮችን እንደሚጠብቁ የገለጹት ልዩ መልዕክተኛው እነዚህም እየተካሄደ ያለውን ግጭት ማስቆም፣ በሁሉም ግዛቶች የሰብአዊ ድጋፎችን ማጠናከር እና ለተፈፃሚነታቸው የሚረዱ አካሄዶችን መፍጠር እንደሆኑ ገልጸዋል::
በኢትዮጵያ እና በጎረቤት ሃገራት የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ከየሃገሩት መንግስታት ጋር ውጤታማ ውይይቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ቶም ፔሪሎ አክለውም ስደተኞችን ለመቀበል በኢትዮጵያ በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል::
ዩናይትድ ስቴትስ በሲውዘርላንድ መዲና ጄኔቫ ለሚካሄደው ውይይት ከሳውዲ አረቢያ እና ግብጽ ጋራ በቅርበት እየሰራች እንደምትገኝ ልዩ መልዕክተኛው አክለው ገልጸዋል:: ከነዚህ አገራት በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የአፍሪካ ህበረት እና የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ተወካዮች በታዛቢነት እንዲገኙ ጠይቀናል ብለዋል::
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ.ር) በቅርቡ ወደ ፖርት ሱዳን አቅንተው ከጀነራል አል ቡርሃን ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል::
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ ኢትዮጵያ በሱዳን እየተደረገ ያለውን ውጊያ ለማቆም እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደሚያደንቁ የገለጹ ሲሆን ጦርነቱ ይዘቱን አስፍቶ ወደ ከባቢው ሃገራት እንዳይስፋፋ እና ቀጠናዊ መልክ እንዳይዝ የቀጠናው ሃገራት ትብብር በእጅጉ እንደሚያስፈልግ አበክረው ገልጸዋል::
በቅርቡ የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ሊቀመንበር እና የሱዳን ጦር አዛዥ የሆኑት ጄነራል አል ቡርሃን በምስራቅ ሱዳን ገቢት በድሮን ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ማምለጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል:: በተፈጸመውም የድሮን ጥቃት ከጄነራል አል ቡርሃን ጋር የነበሩ አምስት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል:: ጥቃቱን ተከትሎ ከጄነራል አል ቡርሃን አሜሪካ ባመቻቸው ውይይት እንደማይሳተፉ ገልጸዋል።
በጀኔራል አልቡርሃን በሚመሩት የሱዳን ጦር እና ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር መካከል ባለፈው 2015 ሚያዝያ ወር በሱዳን የተጀመረው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል። ጦርነቱን ተከትሎ በርካቶች ህይወታቸውን ሲያጡ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል::አስ