አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30/ 2016 ዓ/ም፦ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ ለአራት ዓመት በእስር ላይ የቆዩት ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ነሀሴ 30/ 2016 ዓ/ም ከእስር መፈታታቸውን ፓርቲው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቀ።
ከእስር የተፈቱት የፓርቲው አመራሮች አብዲ ረጋሳ፣ ለሚ ቤኛ፣ ዳዊት አብደታ፣ ሚካኤል በረን፣ ኬነሳ አያና፣ ገዳ ኦልጂራ እና ገዳ ገቢሳ ናቸው።
እስረኞቹ መፈታታቸውን ያረጋገጡት የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለሚ ገመቹ እያንዳንዳቸው ዋስ እንዲያዘጋጁ ነበር ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል። ከዚያም ታስረውበት ከነበረው ቡራዩ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ተወስደው እንዲፈቱ በመወሰኑ ለመጨረሻ ሂደቶች ወደ ቡራዩ ተመልሰዋል ብሏል።
የአመራሮቹ ጠበቆች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት ፍርድ ቤት ቀድሞውኑ በተደጋጋሚ እንዲፈቱ ውሳኔ ያሳለፈ በመሆኑ አመራሮቹ ዛሬ የተለቀቁት በፖሊስ ውሳኔ ነው። “ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ እንዲፈቱ ውሳኔ የሰጠ በመሆኑ አዲስ የሰጠው ውሳኔ የለም” ብለዋል።
አመራሮቹ ፍርድ ቤት እንዲፈቱ የሰጠው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሳይሆን ለአራት አመታት በዕስር ላይ ቆይተዋል።
የፓርቲው አመራሮች ከ2012 እና 2013 ዓ/ም ጀምሮ በኦሮሚያ ፖሊስ ተይዘው በዕስር ላይ የቆዩ ሲሆን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች እንዲለቀቁ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
2012 ላይ የጀመረው የአመራሮቹ እስር በየካቲት ወር የኦነግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አብዲ ረጋሳ በቡራዩ ከተማ ውስጥ የፖሊስ መኮንን በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል። ከሁለት ወራት በላይ አመራሩ የት እንዳሉ ቤተሰቦቹ እና ጠበቆች እንደማያውቁ ፓርቲው በወቅቱ አስታውቋል።
በኋላ ላይ ለስምንት ወራት ከቤተሰብ ሳይገናኙ እንዲቆዩ ወደተደረጉበት ገላን የሚገኝ ልዩ ኃይል ካምፕን ተወሰደዋል። በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ ስምንት የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረዋል።
በሰኔ ወር 2012 የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ለሚ ገመቹ፣ ዳዊት አብደታ፣ ኬነሳ አያና፣ ሚካዔል በረንና በርካታ የኦሮሞ ተቃዋሚ ሰዎች እና ጋዜጠኞች በኦሮሚያ ፖሊስ ለዕስር ተዳርገዋል።
ሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ እና ገዳ ገቢሳን ጨምሮ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል ሞጆ፣ አዋሽ መልካሳ፣ ገላን፣ ሰበታ እና ቡራዩን ጨምሮ በርካታ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል።
“የተወሰኑ አባሎቻችን ገላን ከተማ በሚገኘው ሶሎሊያ በተባለ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ካምፕ ውስጥ ለብቻቸው ተለይተው ታስረው ነበር።
እስረኞቹ በተደጋጋሚ የዕስር ቦታቸው ሲቀያየር የነበረ ሲሆን ሂዩማን ራይት ዎች ዝውውሮቹ የሚደረጉት ለዕስረኞቹ ቤተሰብና ጠበቆች ሳይነገር በመሆኑ ደህንነታቸው እንዳይታወቅ አድርጓል ሲል ገልጿል።
ፓርቲው አመራሮቹ በቀድሞው ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን በአሁኑ ስያሜው ሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በተለያዩ የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ያጋጠሟቸውን አስከፊ ሁኔታዎች በየካቲት 2014 በዝርዝር በመግለጫ አስታውቋል። አመራሮቹ ከህግ አግባብ ውጭ ለረጅም ጊዜ መታሰራቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ በማድረግ ለጤና እክል ተዳርገዋል ብሏል።
በዚያኑ አመት ግንቦት ወር መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት፤ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት “ከሕግ አግባብ ውጪ መታሰራችውን” ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አስታውቋል። ኢሰመኮ ሁሉም እስረኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በእስረኞች ላይ ድብደባ የፈጸሙ የጸጥታ አባሎችና ኃላፊዎች ላይ ምርመራ እንዲያደርግና ተጠያቂ እንዲደረጉ ጠይቋል። ተገቢ ባልሆነ አያያዝ በእስረኞች ላይ ለደረሰው ጉዳትም ካሳ እንዲከፈላቸው ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡አስ