ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ኮሚሽኑ በበቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ ሲያካሂደው የነበረውን ምርመራ ለማቋረጥ መገደዱን አስታወቀ፣ በግድያው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እጅ እንዳለት የሚያመላክት ምስክርነት መሰብሰቡንም አመላክቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር በሆኑት በበቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተሳትፎ መኖሩን የሚያመላክት ምስክሮችን ማሰባሰብ ከጀመረ ከሶስት ቀናት በኋላ የምርመራው ቡድን “ምርመራውን እንዲያቋርጥ መገደዱን” ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጭምሮ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በላከው ደብዳቤ አስታወቀ። 

ኮሚሽኑ ሚያዚያ 9 ቀን ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጽ/ቤት፣ ለክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ለክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ የጻፈውን ደብዳቤ አዲስ ስታንዳርድ ተመልክቶታል።

ባለ ሁለት ገጹ ደብዳቤ፤ በቴ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሾዋ ዞን መቂ ከተማ መገደሉን ያረጋገጠ ሲሆን ኮሚሽኑ “መረጃው እንደደረሰው” ሚያዝያ 2 ቀን “በአቅራቢያው ይሰሩ የነበሩ የምርመራ ባለሙያዎችን” መረጃ እና ማስረጃ እንዲያሰባስቡ ማሰማራቱን ጠቁሟል። 

መርማሪ ቡድኑ ባሰባሰበው መረጃ አና ማስረጃ በቴ ኡርጌሳ በመቂ ከተማ ባረፈበት አብሔም ፔንሲዮን ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም 11 ሰዓት አከባቢ እራት ከበላ በኋላ እንደሚመለስ በመግለጻ የምኝታ ክፍሉን ቁልፍ በማስቀመጥ ለቆ መወጣቱን አስታውቋል።

በዕለቱ በቴ ፔኒሲዮኑን ለቆ ከወጣ ከ30 ደቂቃ በኋላ የደንብ ልብስ የለበሱ እና መሳሪያ የታጠቁ የጸጥታ ሀይሎች በፔኒሲዮኑ በመገኘት ማረፊያ (አልጋ) መከራየታቸውን አትቷል። ቀይ ኮፊያ ያጠለቁ እና መለዮ የለበሱ አራት የጸጥታ ሀይሎች ከሁለት ባለስልጣናት ጋር፣ በጠቅላላው ስድስት ሰዎች ነበሩ ብሏል።

ከሌሎች ግዜያት በተለየ በዕለቱ 11 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ የከተማዋ የጸጥታ ሀይሎች ባለ ሶሰት እግር (ባጃጅ) እና የእግረኛ እንቅስቃሴን መከልከላቸውን አትቷል።

በዕለቱ ሌሊት ላይ ስድስት ሰዓት አከባቢ ከከተማዋ ወጣ ብሎ የበቴ አስከሬን በተገኘበት መንገድ ላይ አንድ ባለሁለት ጋቢና ፒክአፕ በፍጥነት በመጓዝ ከዋናው መንገድ ወጣ ብሎ መበራት ሳያጠፋ መቆሙን የኮሚሽኑ ከአይን ምስክሮቸን ዋቢ በማድረግ ያስቀመጠው ዝርዝር መረጃ ያሳያል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቀይ መለዮ ኮፊያ እና ዥጉርጉር ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ እና መሳሪያ የታጠቁ አራት ሰዎች ከመኪናዋ በመውረድ ከመኪናዋ ኋላ አንድ ሰው ጎትተው በማውረድ በተደጋጋሚ በመተኮስ ጥለውት ሂደዋል ሲል የኮሚሽኑ ደብዳቤ በዝርዝር አስታውቋል።

በነገታው ሚያዚያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም የበቴ ኡርጌሳ አስከሬን ሁለት እጁ አንደታሰረ ጭንቅላቱ ላይ፣ ደረቱ ላይ እና ሆዱ አከባቢ በጥይት ተመትቶ ተገኝቷል።

በነገታው መርማሪ ቡድኑ ምስክርነት ከሰጡት ሰዎቸ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ ቢሄድም ሊያገኛቸው እንዳልቻለ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው መታሰራቸውን እንደተረዳ አመላክቷል። ፖሊስ ያሰርኳቸው ለደህንነታቸው ስል ነው የሚል ምላሽ አንደሰጠው የጠቆመቅው ደብዳቤው ነገረ ግን ኮሚሽኑ እንዳያነጋግራቸው መከልከሉን አሰታውቋል።

ኮሚሽኑ በተጨማሪም የመሰካሪዎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጿል። ፖሊስ የመረማሪ ቡድኑ ያነጋገራቸውን ምስክሮች ከማሰር ባለፈ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አከባቢዎች ሁሉ በመኪና እና በሰዎች እየተከታተሉ እንቅስቃሴያቸውን እንዳወኩባቸው ጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ ከኮሚሽኑ ጋር ሲተባበሩ የነበሩ የበቴ ኡርጌሳን ቤተሰቦች ፖሊስ እነዳሰራቸው አስታውቋል።

በመሆኑም የመርማሪ ቡድኑ አባላትን፣ የምስክሮቹን፣ እና ከምርመራው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል በከተማዋ የሚያካሂደውን ማስረጃ የማሰባሰብ እንቅስቃሴውን ለማቆም መገደዱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በደብዳቤው የክልሉ መንግስት በህጉ ላይ እንደተቀመጠው ለስራው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግለት፣ በሚያካሂደው ምርመራ ምንም አይነት እንቅፋት እንዳይፈጠርበት ጠይቋል።

በእስር ላይ የሚገኙትን ምስክሮቹን ለመጎብኘት በአፋጣኝ እንዲፈቀድለት እንዲሁም የሟች ቤተሰቦቸ እና ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያሉትም የሰብአዊ መብት ጥሰት አንዳየፈጸምባቸው ክትትል እንዲደረገላቸው አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ደብዳቤው ከጻፈበት ቀን ጀምሮ ባሉ አስር የስራ ቀናት ባካሄደው ምርመራ ዙሪያ እና ግኝቱን ይፋ ከማድረጉ በፊት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከክልሉ ባለስለጣናት ጋር ለመመካከር ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል።

አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ኮሚሽኑም በሰጠን ምላሽ ምርመራ እየተካሄደበት ባለ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት አስተያየት እንደማይሰጥ የሚገልጽ ነው። በተጨማሪም ኮሚሽኑ ምንም እንኳ እንቅፋቶቸ ቢፈጠሩም በበቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ የምርመራውን የመጀመሪያ ግኝት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button