ዜናቢዝነስ

ዜና፡መንግስት በሩብ ዓመቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ጉድለት መታየቱን አመነ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9/2016 ዓ.ም፡- በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ እና በሥራ እድል ፈጠራ የተያዘው ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ጉድለት መታየቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ አስታወቁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም መገምገሙን ሚኒስትሩ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።

በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ እና በሥራ እድል ፈጠራ የታየው ጉድለት ምን እንደሆነ እና መጠኑን በተመለከተ መረጃው የጠቀሰው ነገር የለም።

ሚኒስትሯ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በበበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ እና በሥራ እድል ፈጠራ የተያዘው ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ጉድለት የታየው በዋናነት አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል ብሏል።

በቀጣይም ጉድለቶቹን ለማካካስ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ መናገራቸውንም አካቷል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ገልጸዋል ያለው ዘገባው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ስርዓቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመምራት አገራዊ እድገትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውንም አመላክቷል።

ለዚህም የተቋማትን የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት የአሰራር ስርዓት በተገቢው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ማሳሰባቸውንም ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሚኒስቴሩን ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሃብት አጠቃቀም፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የፖሊሲ ዝግጅት፣ የክትትል እና ግምገማ ስርዓት ውጤታማነትን ለማጎልበት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ሚኒስትር ዴዔታው ዶ/ር ነመራ ገበየሁ ባቀረቡት ሪፖርት ማብራራታቸውን መረጃው ያሳያል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃጸም ደረጃ እና ለክልሎች የልማት ዕቅድ የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ መጠየቃቸውን የጠቆመው የሚኒስቴሩ መረጃ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱን ለማሳካት ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ መግለጻቸውን አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button