ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባሉ የነበሩትን ኬርያ ኢብራሂምን አባረረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2016 ዓ.ም፡- የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው ስብሰባ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ባካሄደው ጦርነት ወቅት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘው በቁጥጥሩ ስር ውለው በነበሩ አመራሮቹ ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው አመራሮቹ በመንግስት ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት የነበሩበትን ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ውሳኔዎቹን ማሳለፉን ጠቁሟል።

ባሳለፈው ውሳኔም የስራ አስፈጻሚው የነበሩት የቀድሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬርያ ኢብራሂም እና የቀድሞ የትራንሰፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ከፓርቲው እንዲባረሩ ማድረጉን አስታውቋል።

ፓርቲው ለመባረራቸው ያስቀመጠው ምክንያትም በጦርነቱ ወቅት እጃቸውን ለመንግስት ሰጥተዋል፣ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት የፓርቲውን ሚስጥር አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል መሆኑን ጠቁሟል። በፓርቲው ህገደንብ መሰረት የተላለፈ ውሳኔ ነው ብሏል።

ከእነ ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ጋር በፌደራል መንግስቱ በእስር ላይ የነበሩት እና የክስ ሂደታቸው ተቋርጦ በምህረት የተለቀቁት አመራሮቹ በፓርቲው እንዲቀጥሉ መወሰኑን አመላክቷል።

ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እና ዶ/ር አብርሃም ተከስተ በስራ አስፈጻሚነታቸው እንዲቀጥሉ እንደተወሰነላቸው ያስታወቀው የህወሓት መግለጫ ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳኔ፣ አጽበሃ አረጋዊ፣ ኪሮስ ሀጎስ እና ዶ/ር ረዳኢ በርሄ በማዕከላዊ ኮሚቴነታቸው እንዲቀጥሉ መደረጉን ገልጿል።

በቀጣይ ፓርቲው ለሚያካሂደው 14ኛው ጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴነት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር፣ ኢሳያስ ታደሰ እና አልማዝ ገብረፃድቅ መሰየማቸውን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከስራ አስፈጻሚነት የተባረሩት ኬርያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገ/እግዚአብሔር በድርጊታቸው መጸጸታቸውን በመግለጽ ግለሂስ አድርገዋል ያለው መግለጫው በቀጣይ በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ህዝባቸውን ለመካስ ቃል ገብተዋል ብሏል።

በዛሬው ዕለት የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ጋር በመሆን በቀጣዩ ጉባኤ አጀንዳ ዙሪያ እየተወያዩ መሆኑን ጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button