ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ለጠ/ሚኒስትር አብይ የተበረከተው የፋኦ ሽልማት ድጋፍ እና ነቀፋን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፣ ተቋሙን የተቹም አልጠፉም

አዲስ አበባ፣ ጥር 20/2016 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ላበረከተቱት አስተዋጽኦ እና አመራር በሚል ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሸልሟል።

እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ ከሆነ ሽልማቱ የሚሰጠው የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ልዩ አበርክቶ ላበረከቱ ታዋቂ እና የተከበረ ስብዕና ላላቸው ሰዎች ነው።

ሽልማቱ በጣሊያን ሮም ከተቀበሉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሽልማቱን ያበረከተላቸውን የመንግስታቱ ድርጅትን በማመስገን “ከፍ ያለ ጠቀሜታ ባላቸው እና የኢንዱስትሪ ግብዓት በሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት መደረጉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስገኘ” እንደሚገኝም ገልጸዋል፤ “የምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን” ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ይገባቸዋል ከሚል አስተያየት ጀምሮ ሽልማቱ በጠ/ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ዘንድ ውዳሴ ተችሮታል። የጠ/ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት እና በመንግስታቱ ድርጅት የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታየ አቅጸስላሴ የአለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ለጠ/ሚኒስትር አብይ ሽልማት ማበርከቱን አወድሰው “እርግጥ ነው የገበሬዎች ህይዎት ሲሻሻል የሀገሪቱም እንዲሁ ይሻሻላል” የሚል አስተያየት በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

ሽልማቱ በደጋፊዎቻቸው የተቸረውን ውዳሴ ያክል በርካቶች ደግሞ የመንግስታቱ ድርጅትን የሚተች አስተያየትን ሰጥተውበታል። የከፋ ድርቅን በማስተናገድ ላይ ያለች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በረሃብ ምክንያት የሚሞቱባትን ሀገር መሪ እንዴት ይሸልማል የሚሉ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።

“የመንግስታቱ ድርጅት አካል የሆነው እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ግብርናን ለማሻሻል በሚል የተቋቋመው ፋኦ በሺዎች የሚቆጠሩ በተለይም የትግራይ እና የአማራ ገበሬዎች በረሃብ ምክንያት የሚሞቱባትን ሀገር መሪ በመሸለም የአለምአቀፉ አሰላለፍ ምጸት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አሳይቷል” ሲሉ የአውሮፓ ዩኒቨርስቲ ተቋም ፕሮፌሰሩ መሃሪ ተድላ ማሩ ሸላሚውን ተቋም በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ይገኝበታል።

አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የአለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገሪቱ የምግብ እጥረት እንዳጋለጣት በመግለጽ ጠ/ሚኒስትሩን የጉዳዩ ተጠያቂ ላለማድረግ የሚጥሩ እንዳሉ ሁሉ በሀገሪቱ ለተፈጠረው የምግብ እጥረት የጠ/ሚኒስትሩ የፖሊሲ ውድቀት ነው በሚል የሚተቿቸውም አሉ። ሽልማቱ በሚሊየን ለሚቆጠሩ እና ረሃብ ላጠቃቸው ዜጎች ላይ እንደ ማሾፍ ነው ሲሉ የገለጹም አልጠፉም። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button