ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ሲኖዶሱ ምእመናን እና ተቋማት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወንጀል ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1/2016 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ንፁሐን፣ ምእመናን እና ተቋማት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ መንግሥትና የሚመለከታችሁ ሁሉ ዋስትና እንድትሰጡ፣ ወንጀል ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ፡፡ ድርጊቱንም መላው ዓለም እንዲያወግዘው ጥሪ አቀርቧል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሰጠው መግለጫ መተኪያ የሌለው ሕይወት የሚያጠፋና ሥጋት ላይ የሚጥሉ ተፈጥሮአዊ፣ ሰብዓዊ ክብሩን የሚያራክስ ተግባራት እንዳይደገሙ ለማድረግ በሚጥርበት ዓለም ችግሩ በተለይም በሀገራችን እየተባባሰ መቀጠሉ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ቋሚ ሲኖዶሱ በመግለጫወው በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት፣ በሶሌዲገሉና ጢጆለቡ እና በሌሎች አካባቢዎች በረካታ ሰዎች መገደላቸውን አስታውሷል።

ሲኖዶሱ አክሎም በማዕከላዊ ጐንደር ሀገረ ስብከት የጐንደር ዓቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት መምህር ፍሥሐ አለምነው ባልታወቀ ግለሰብ በድንጋይ ተወግረው መገደላቸው እና ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. የማዕከላዊ ጐንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በኲረትጉሃን ዘርዓዳዊት ኃይሉ ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተመተው መገደላቸው አሰታወቆ በዚህም በእጅጉ ከማዘናችንም በላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያረጋግጥ አድራጐት ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡ 

ተመሳሳይ ግድያና፣ ስደት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የየዕለት ዜናችን ከሆነ ሰንብቷል ያለው መግለጫው ለአብነትም ያህል በወለጋ፣ በጐንደር፣ በጐጃም፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመሳሰሉት አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለው ድርጊት መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት ሀገር፣ እኛንም ሆነ በመላው ዓለም መፍቀሬ ሰብእ የሆኑ የሰብዓዊ ክብር አስጠባቂ ተቋማትን ሳይቀር ማሳዘኑን ቀጥሏል ብሏል፡፡ 

እየተፈጠረ ባለው አስከፊ መከራ፣ በጭካኔ የተሞላ ድርጊት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማጣት የዜጎችን ሕይወት፣ አካልና ንብረት፣ የእምነት ተቋማትን፣ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችና መስሕቦችን ሲያወድም፣ በሀገር ሁለንተናዊ ደኅንነትና በሕዝቦች ትሥሥር ላይ የፈጠረው አለመተማመን በቀላሉ የማይመለስ አደጋ ነው ተብሏል፡፡ 

“ከተከሰተው ረሀብ፣ ድርቅ፣ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በተጨማሪ በየቦታው በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ቀያቸውን ለቀው፣ መነኰሳት ገዳማትን ትተው ተሰደዋል” ያለው ቋሚ ሲኖዶሱ  “ወላድ እናቶች፣ ሕሙማንና አረጋውያን በሕክምና እጦት እያለቁ ነው፣ ሕፃናትና ወጣቶች ከጤናማ እድገትና ከትምህርት ገበታ ተደናቅፈዋል” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ከግጭትና ከጦርነት፣ ከርስ በርስ መገዳደል ወጥተው በውይይትና በምክክር፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት የታላቋን ሀገር መልካም ስምና ክብር እንዲሁም የዜጎቿን ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባር ቅድሚያ እንዲሰጡ በጥብቅ አሳስባልች፡፡  

እንደ ዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም፣ አሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤል ገዳም እና አካባቢው፣ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምና አካባቢው የመሳሰሉ ሁሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት አደጋ የተጋረጠባቸው በመሆኑ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸውም አሳስቧል።

በመጨረሻም በየቦታው የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለማስቀረት ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲኖዶሱ አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button