ዜናቢዝነስ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በቀጣይ ጥቂት አመታት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኬንያውን ሳፋሪኮም መሪነት እንደሚረከብ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት አመታት ያላስቆጠረው የኬንያው ቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጥቂት አመታት ውስጥ ዋና ጽ/ቤቱ መቀመጫ በመሆነችው ኬንያ ካለው ክንውን እንደሚበልጥ ተገለጸ።

በዚህም ምክንያት ትኩረቱን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያዞር ተጠቁሟል።

በቅርቡ ይፋ የሆነው የኩባንያው የፋይናንስ ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ ስታንዳርድ ጋዜጣ እንዳስነበበው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እድገት ከኬንያው የሳፋሪኮም እድገት ጋር የሚወዳደር አይደለም ብሏል፤ በስልክ መስመር ተጣቃሚዎች ቁጥር፣ በኔትወርክ መሰረተ ልማት፣ በስራ ዕድል እና በገቢ በቅርብ አመታት ውስጥ የኢትዮጵያው ሳፋሪኮም የበላይነቱን ይቆጣጠራል ሲል ገልጿል።

ተቋሙ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት መሰረተ ልማት መገንባቱ ለስኬቱ ዋነኛ ምክንያቱን የጠቆመው ዘገባው ከሁለት አመት ባነሰ ግዜ የኬንያን ሲሶ የሚሆን ስፋት ያለውን የኢትዮጵያ ክፍል ሽፋን መስጠት መቻሉን አመላክቷል።

በ33 ከተሞች 2ሺ 200 ሳይቶች እንዳሉት እና ከአራት ሚሊየን በላይ የተመዘገቡ የስልክ መስመር ተጠቃሚ ደንበኞች ማፍራቱን እና ባለፉት 15 ወራት 33 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ሽፋን መስጠቱን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሊቀመንበር ሚካኤል ጆሴፍ መግለጻቸውን አስነብቧል።

ባለፉት 20 አመታት በኬንያ የሳፋሪኮም የተገነቡ የኔትዎርክ ሳይቶች 6ሺ 300 መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የኔትዎርክ ሳይቶቹ ከሁለት ሺ ሁለት መቶ በላይ መገንባታቸውን አስታውቋል።

ሳፋሪኮም በመጋቢት ወር 2023 ፈሰስ ባደረገው የአንድ አመት ካፒታል ኢንቨስትመንት ከግማሽ በላዩ በኢትዮጵያ ማፍሰሱን አስታውቋል፤ ባሳለፍነው አመት 96ነጥብ አንድ ቢሊየን የኬንያ ሽልንግ የካፒታል ፈሰስ ማድረጉን፣ ከዚህ ውስጥ 55 ነጥብ 7 ቢሊየን ሽልንግ በኢትዮጵያ ፈሰስ አድርጊያለሁ ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 አመት የኤምፒሳ ተመዝጋቢዎች ኢትዮጵያውያን ቁጥር 3 ነጥብ አንድ ሚሊየን መድረሱን ማሳወቁ ይታወሳል።

በነሃሴ 2014 ዓ.ም የመጀመሪያውን ጥሪ ስናስተናግድ በኢትዮጵያ የነበረን የኔትዎርክ ሳይት 100 ነበር ሲሉ ያወሱት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ቪም ቫንሄልፑቴ በ2023 የፈረንጆቹ አመት መገባደጃ ላይ የገነባነው የኔትወርክ ሳይቶች 2ሺ 242 ደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት 18 ወራት በኢትዮጵያ በየወሩ 125 የኔትዎርክ ሳይቶች ስንገነባ ነበር ማለት ነው ሲሉ የገለጹት ዋና ስራስፈጻሚው በአዲስ አበባ የአምስተኛው ትውልድ 5ጂ ከ25 እስከ 30 በሚሆኑ ሳይቶቹ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን እስኬር በሚሆን የመሬት ስፋት ባላት ኢትዮጵያ 120 ሚሊየን ዜጎቿ ይኖራሉ፣ የኬንያን ሁለት እጥፍ በምትበልጠው ኢትዮጵያ ገቢ የማስፋት እድሉ እጥፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል፤ በኢትዮጵያ ሶስት ሚሊየን የሚሆኑ ታዳጊዎች በየአመቱ 18 አመት ይሞላቸዋል ሲሉ በመግለጽ የገበያውን እድል አመላክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button