አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29/2016 ዓ/ም፦ በትውልደ ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ የልብ ሐኪም ጥንዶች ዶ/ር ተስፋዬ ተሊላ እና ዶ/ር ኦብሲኔት መርድ የተቋቋመው ሄርት አታክ ኢትዮጵያ (HAE) የተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት፤ በጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች በማስተባበር ለሁለተኛ ጊዜ የልብና ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀና ተገለጸ።
ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ በአትላንታ ጆርጂያ በፒየድሞንት ኒውናን ሆስፒታል ኢንተርቬንሽናል ካርዲዎሎጂስት ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ዶክተር ኦብሲኔት መርድ ደግሞ በሞርሃውስ የህክምና ትምህርት ቤት የህክምና ትምህርት ባልደረባ ናቸው።
ጥንዶቹ ያቋቋሙት ሄርት አታክ ኢትዮጵያ (HAE) የተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከአሜሪካ በጎ ፍቃደኛ ዶክተሮች ቡድን እና በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ (CHFE) ጋር በመሆን ባለፈው የካቲት ወር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለ32 ህሙማን የልብ ቀዶ ህክምና የሰጠ ሲሆን በነሃሴ ወር ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር ህክምና ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አሳውቋል።
ዶ/ር ተስፋዬ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ ከነሃሴ 13 እስከ 24 የሚደረገው ሁለተኛው ዙር ህክምና ከአሜሪካ በሚመጡ 16 የበጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች ትብብር የሚከናወን ሲሆን በህክምናው 80 እስከ 100 የሚደርሱ ታካሚዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የሚሰጠው ህምና የልብ ቀዶ ጥገና፣ ፐርኩታኒየስ ኮረነሪ እንተርቬንሽን (PCI)፣ የልብ ምት መቆጣጠሪያ መግጠም እና የማስወገጃ ዘዴዎችን ጭምሮ አጠቃላይ የልብና የደም ሥር ህክምናን ያካትታል ተብሏል።
“መተንፈስ ለጤናማ ሰዎች ልፋት የማይጠይቅ ተግባር ነው፤ ነገር ግን ለህሙማን እጅግ ውድ ስጦታ ነው። አብዛኛዎቹ የልብ ታካሚዎቻችን በነፃነት መተንፈስ አይችሉም፣ እናም የህይወት እስትንፋስን፣ በአለም ላይ ነፃና እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን አየር እንሰጣቸዋለን” ሲሉ ዶክተር ተስፋዬ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
በጎ ፍቃደኛ የአሜሪካ ህክምና ባለሙያዎቹ ብድን ሄርት አታክ ኢትዮጵያ የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ የሆነውን በከፍተኛ የሕክምና ጣልቃ ገብነትና ቀጣይነት ባለው የጤና አጠባበቅ ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ በልብና የደም ሥር በሚፈጠሩ ችግሮች የሚከሰትን ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ያስችላል ተብሏል።
በተጨማሪም ድርጅቱ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ (CHFE) ከቀዶ ጥገና በኋላ ህሙማን ላይ ሊያጋጥም የሚችልን የደም መርጋት አደጋን ለመከላከል የሚያገለግል ክሊኒክን በማቋቋም ለጤና ባለሙያዎች እራሳቸውን ችለው የልብና የደም ሥር ህክምናን እንዲሰጡ የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
ሄርት አታክ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ከሚገኙ ለጋሽና ተባባሪዎች የተሰበሰበ ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁሶችን መለገስ የሁለተኛው ዙር የህክምና ተልዕኮ አካል መሆኑንም ገልጿል።
በኢትዮጵያ ለሞት በመዳረግ ቀዳሚ በሆነው በልብና የደም ሥር ህመም የተያዙ ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህሙማን የህክምና ባለሙያዎቹን ህክምና ለማግኘት እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ሪፖርቶች አመላክተዋል። አስ