ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በትግራይ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የሶስት ቀን ብሔራዊ ሀዘን እንደሚታወጅ እና መርዶ እንደሚነገር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2016 .ም፡ በትግራይ ሀይሎች እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ተካሂዶ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ህይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር በቀጣይ ወር መጀመሪያ ለሶስት ቀናት ክልላዊ ሀዘን በትግራይ ክልል እንደሚታወጅ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ጀኔራል ታደሠ ወረደ ትናንት መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መርዶ የሚነገረው እና ክልላዊ የሀዘን ቀን የሚታወጀው በጦርነቱ ሳቢያ በክልሉ ተቋርጦ የነበረው እና በተያዘው አመት መስከረም ወር መጨረሻ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን ጀነራል ታደሰ ወረደ ገልጸዋል።

በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ሰማዕታቱን ለመዘከር የህሊና ጸሎት ስነስርአት እንደሚከናወን ጀነራሉ ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ቀን የሰማዕታቱ ቤተሰቦች መርዶ እንደሚነገር እና ከዚያም ቀጥሎ ያሉት ቀናት ክልላዊ የሀዘን ቀናት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

አንዳንድ ቤተሰቦች ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ የልጆቻቸው መሰዋት እየተረዱ መሆኑን የጠቆሙት ጀነራሉ የመንግስትን ይፋዊ መርዶ እንዲጠብቁ አሳስበዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ ስታንዳርድ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ልጆቻቸው በትግሉ የሙቱባቸው ቤተሰቦች መርዶ እንደተደረገላቸው መታዘብ ችሏል። በበርካታ የከተማዋ አብያተ ክርስትያናት የሰማዕታቱ የክብር የቀብር ስነስርአት ሲከናወን ለመመልከት ተችሏል። በመቀሌ ከተማ ቀበሌ 17 በሚገኘው እንዳስላሴ ቤተክርስቲያን የሁለት እድሜያቸው ሃያዎቹ የሆኑ ሴት እና ወንድ ወጣት ሰማዕታት ቀብር ላይ አዲስ ስታንዳርድ ለመታደም ችላለች።

በቤተክርስቲያኑ የሰማዕታቱ አስከሬን ባይገኝም በአከባቢው አጎበል በሚል በሚጠራው ባህል መሰረት ቤተሰቦቻቸው ጓደኞቻቸው እና አብሮአደጎቻቸው በተገኙበት ወታደራዊ ክብር የታጀበ የህይወት ታሪካቸው ተነቦ ፍታት ተፈጽሟል። መርዶ የተደረገላቸውን ቤተሰቦች አዲስ ስታንዳርድ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የመቀለ ነዋሪ የሆኑት እና ባለፉት ሁለት ሳምንታት በበርካታ መርዶዎች መሳተፋቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹ ግርማይ ሃጎስ፣ በየመርዶዎቹ የሚነገሩ ታሪኮች እጅግ አሳዛኝ እና ልብን የሚነኩ ናቸው ብለዋል፤ ለአብነትም ሶስት እና ከዚያ በላይ የአንድ ቤተሰብ ወጣቶች ሞት መርዶ የተነገራቸውን ቤተሰቦች ጠቅሰዋል። በከተማዋ የሚነገሩ መርዶዎችን ለመታደም እና ቤተሰቦቻቸውን ለማጽናናት የግል ስራቸውን ለጊዜው ማቆማቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል። የራሳቸውን የቅርብ ቤተሰቦች መርዶ እየተጠባበቀ መሆኑን ግርማይ ሀጎስ ገልጸዋል።

የግዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በትላንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰማዕታቱ ሙሉ ታሪክ ስነዳ መጠናቀቁን አመላክተዋል። ወላጆች ልጆቻችን የት አሉ ብለው እንዲጨነቁ እና እንዲጠይቁ አይገባም ያሉት ጀነራሉ የግዜያዊ አስተዳደሩ በራሱ ሁሉንም ነገር ግልጽ ያደርጋል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቅርቡ የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳን አቶ ጌታቸው ረዳ ከመርዶ ጋር በተያያዘ የሰማዕታቱን ክብር በሚመጥን መልኩ እንደሚከናወን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አቶ ጌታቸው በርካታ ቁጥር ያለው ሰማዕታት አሉን፣ እያንዳንዱን ሰማዕት የየት አከባቢ ተወላጅ መሆኑን እና የት እንደተሰዋ የማጣራት እና የመመዝገብ ስራ ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ነው የተጠናቀቀው ብለዋል። የሰማዕታቱ የትውልድ ቦታ እና የተሰዉበት አከባቢ ልየታ ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ተጠናቆ ወደ መርዶ ያልተገባው የክረምት ስራዎችን እንዳያስተጓጉል በሚል መሆኑን አስታውቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button