አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2016 ዓ.ም፡– በትግራይ ክልል 32 ወረዳዎች ላይ የከፋ ድርቅና የምግብ እጥረት ማጋጠሙን የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በትግራይ ክልል ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች የከፋ የድርቅ አደጋ ያጋጠማቸው መሆኑን የክልሉ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ አስተባባሪ አቶ ልጅዓለም ካሕሣይ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
በክልሉ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በዋነኝነት በጦርነቱ እና ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ የድርቅ አደጋ በመከሰቱ ያጋጠመ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል ብሏል።
አጠቃላይ ክልሉ በጦርነቱ ምክንያት እና በዝናብ እጥረት እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የድርቅ አደጋ በማጋጠሙ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ እርዳታ ፈላጊ እንዲሆን ማድረጉን ዘገባው አመላክቷል።
ያጋጠመው የምግብ እጥረት የከፋ አደጋ እንዳያስከትል አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አስተባባሪው አሳስበዋል ያለው ዘገባው መንግሥት በቅርቡ ርዳታ እንደሚልክ ቃል በገባው መሠረት በፍጥነት ወደ ተረጂው እንዲዳረስ ይደረጋል ማለታቸውን አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል ሁለት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅና በግጭት ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አታለለ አቡሐይ ገልጸዋል ያለው ዘገባው ክልሉ ያጋጠመው አደጋ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ባሳወቀው መሠረት ርዳታው ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል ብሏል፡፡
በመጪዎቹ ሦስት ቀናት ለሦስተኛ ዙር የሚሰራጭ ርዳታ መኖሩን መናገራቸውን ጠቁሟል። አስ