አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህርዳር ከተማ ትላንት ሃሙስ የካቲት 21/ 2016 ዓ/ም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ተካሄደ ።
የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ ትላንት ምሽት መጀመሪያው የመሳሪያ ድምጽ የተሰማው “አባይ ማዶ” እና “ቀበሌ 14” አካባቢ ነው።
ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የከተማው ነዋሪ፤ “በዳያስፖራ” በሚባል ሰፈር የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ይሰማ እንደነበር ገልጿል።
ነዋሪው አክሎም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና የባንክ አገልግሎት አለመኖሩን በመግለጽ ነዋሪዎች በቤታቸው መቀመጣቸውን ተናግሯል።
ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር የሚደረገው በረራ ከጠዋት ጀምሮ መስተጓጎሉን አዲስ ስታንዳርድ ከተጓዦች መረዳት ችሏል።
አንድ የባርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ትላንት ምሽት የተኩስ ድምጽ የሰማ እንደነበር ገልጾ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ወደ ግቢው አለመምጣታቸውን እና ትምህርት እና ካፌ ዝግ መሆኑን ተናግሯል።
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በባህርዳር ዙሪያ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ በመሆን “ሰርጎ የገባዉን ጽንፈኛ ቡድን” በየቤቱ የማሠስና የማፅዳት ስራ ሲሰራ እየሰራ ይገኛል ሲል ገልጿል።
ቢሮው “በአሁኑ ሠዓት ሙሉ በሙሉ ባህርዳር ከተማና አካባቢዉ ከጽንፈኛ ቡድኑ ጸድተዋል” ብሏል።
መግለጫው አክሎም፤ “ጽንፈኛ” ያላቸው ቡድኖች “የጸጥታ ሀይሉን ጥምረት መቋቋም አቅቷቸዉ ሙትና ቁስለኛ ሆነዉ” የያዙትን መሳሪያ ሳይቀር እያንጠባጠቡ መሸሻቸውን ገልጿል።
እንደ ቢሮው ገለጻ፤ “የጸጥታ ሀይሉን እርምጃ መቋቋም ያቃታቸዉ ጽንፈኞች ራሳቸዉን ለመከላከል የሚያደርጉትን የነፍስ አድን ተኩስ ማጥቃት እያደረጉ እንደሆነ አድርገዉ በሚታወቀዉ የዉጭና የዉስጥ ጽንፈኛ ሚዲያዎች እያስነገሩ ይገኛሉ።”
ባለፉት ቀናት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በመንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት ዳግም ተቀስቅሷል።
ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ በምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በተቀሰቀሰው ግጭት መንገዶች ተዘግተዋል። በጎንደር፣ መራዊ፣ ደጋ ዳሞት፣ ሸዋ ሮቢት፣ አንጾኪያና ገምዛ እና ላሊበላ በመሳሰሉት ከተሞች አካባቢ ከባድ ውጊያዎች ተካሄደዋል። አስ