ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በተፈጸመ ጥቃት 27 ሰዎች ተገደሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ “በፋኖ ታጣቂዎች እና የክልሉን ፖሊስ ደምብ ልብስ በለበሱ ኃይሎች” ከየካቲት 30፣ 2016 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጸመ “የተቀናጀ ጥቃት” 27 ነዋሪዎች መገደላቸውን እና ከ40 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ። 

ከ11 ቀናት በፊት “የፋኖ ታጣቂዎች እና የክልሉን ፖሊስ ደምብ ልብስ የለበሱ ኃይሎች” በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ግጭት መከሰቱን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹት የስፍራው ነዋሪዎች፤ ራሳቸውን ለመከላከት ወደ ግጭቱ ከገቡ የወረዳው ነዋሪዎች መካክለ የተገደሉ መኖራቸውን ገልጸዋል። 

በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በሚገኙ ከ20 በላይ ቀበሌዎች ላለፉት 11 ቀናት ግጭት መቀጠሉን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። 

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የኮላሺ ቀበሌ ነዋሪ፤ የካቲት 30 በቀበሌው ጥቃት መፈጸሙን ገልጾ፤ “በዕለቱ በተፈጸመው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ቆስለዋል፤ የፋኖ ታጣቂዎች ላሞችን ወስደው ሄደዋል” ብሏል። 

ከዚያ በኋላ ጥቃቱ ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች መስፋፋቱን የገለጸው ነዋሪው፤ ራሳቸውን ለመከላከል ወደ ውጊያ ከገቡ ነዋሪዎች መካከል ተጨማሪ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን አክሎ ገልጿል። 

“የፋኖ ኃይሎች እና የአማራ ክልል ፖሊስ ደምብ ልብስ የለበሱ ኃይሎች፤ ከኮላሺ ቀበሌ ጀምሮ እስከ ስንበቴ ከተማን የሚያዋስን ቀበሌ ድረስ እየፈጸሙ ባሉት የተቀናጀ ጥቃት ህጻናት፣ እረጋውያን እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች ወድመዋል” ብሏል ነዋሪው። 

እስከ ዛሬ ቀጥሏል በተባለው ጥቃት 27 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸው ነዋሪው፤ ጉዳት ከደረሰባቸው 40 ሰዎች ውስጥ 20 የሚሆኑት በአፋር ክልል አቋርጠው በአዳማ ከተማ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ከአዲስ አበባ እስከ ደሴ ያለው መንገድ በመዘጋቱ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ተቸግረናል። ተጨማሪ ገንዘብ በመዋጣት አፋር ክልልን አቋርጠው በአዳማ እየታከሙ ነው ያሉት። ሌሎቹ ተጎጂዎቹ ደግሞ በሰምበቴ እና ባቲ ከተማ ነው እየታከሙ ያሉት” ሲል ገልጿል። 

ሌላኛው የከራ አባ ቀርጮ ቀበሌ ነዋሪ፤ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ግጭት አሁንም መቀጠሉን ጠቅሶ፤ “ የግጭቱ አላማ ነዋሪዎቹን ከአካባቢው ማፈናቀል ነው” ሲል ገልጿል። 

“መሬታችንን ለቃችሁ ሂዱ፤ መሬቱ የኛ ነው፤  የኦሮሞ አስተዳደር ዞን የሚባለ ነገር የለም” በማለት ሲያፈራሩን ነበር ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸው ነዋሪው፤ ከዚህ ቀደምም “የረመዳን ወር ላይ ጥቃት መፈጸሙን” ገልጿል። 

አዲስ ስታንዳርድ በዚህ ጉዳይ ላይ የዞኑን እና የወረዳውን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ አስታየታቸውን በዘገባው ላይ ማካተት አልተቻለም።

በአማራ ክልል በሚገኘው በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸማሉ። ለአብነትም ባሳለፍነው አመት ጥር 13፣ 2015 ዓ/ም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ድሙጋ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በተፈጽመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን ቢቢሲ አማርኛ መዘገቡ ዘግቧል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button