አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26/ 2016 ዓ/ም፡_ በአማራ ክልል በ9 ዞኖች በተከስተው ድርቅ ምክንያት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ የክልሉ የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል፣ ይህን ችግር ለመቀልበስ እና በቀጣይም የችግሩን ስፋት የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ከሁሉም አካላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የተከሰተው ድርቅ ያስከተለው ጉዳትና የተሰጠውን ምላሽ የሚገመግም መድረክ ዛሬ በባህር ዳር የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የክልሉ መንግስት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ከ4 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ድርቁ ያደረሰውን ጉዳት በተጨባጭ አጥንቶ መለየት እና መደገፍ ሲገባ “ለፖለቲካ ፍላጎት” ሲባል ኀላፊነት የጎደለው እና የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት ትክክል አለመኾኑን አስገንዝበዋል። “በወገኖቻችን ላይ የተከሰተውን ጉዳት ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል ከሰብአዊነት የራቀ ተግባር ነው” ሲሉም ገልጸውታል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፣ በድርቁ ለተጠቁ አካባቢዎች በፍጥነት ድጋፍ ማድረስ ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ ሲሉ ገልጸዋል። ዶ/ር ድረስ ከድርቁ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን ርሃብ፣ የጤና ችግር፣ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየተሠራ ሰለመኾኑም ተናግረዋል።
በዋግኽምራ ወደ ቦታው የደረሱ እርዳታዎችን በፍጥነት ወደ ተጠቃሚዎች በማድረስ በኩል ክፍተቶች ስለመኖራቸው በምልከታ ተረጋግጧል ብለዋል።
ይህን ክፍተት በማረም ቅንጅታዊ አሠራር ተፈጥሮ የተሠበሠበውን ሃብት ፈጥኖ ለተጎጅዎች የማድረስ ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ከእርዳታ ፈጥነው እንዲወጡ እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በአካባቢዎቹ ላይ የመስኖ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለዚህም የክልሉ ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመስኖ ሥራን የሚደግፉ የውኃ ፓንፖችን ያሰራጫል ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመደገፍ ሥራውን ማገዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።አስ