ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በፋኖ ሀይሎች እና በታጠቁ ነዋሪዎች መካከል በተካሄደ ግጭት 18 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አርጡማ ወረዳ በፋኖ ሀይሎች እና በታጠቁ ነዋሪዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ18 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁ።

ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም በአከባቢው ቀኑን ሙሉ በተካሄድ ውጊያ ከ30 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 10 የሚሆኑን ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ለተጨማሪ የህክምና እርዳታ ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን አመላክተዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ታጣቂዎቹ የመጡት ከአጎራባቹ የሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ማጀቴ ከተማ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ በሚገኙ ሶስት መንደሮች ላይ እሁድ ዕለት ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ ውጊያ ነበር፣ ይህ ውጊያ ከመደረጉ ከሶስት ቀን በፊት ጥቅምት 22 የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ወረዳችን በመግባት አንድ ሽማግሌ ገድለው ሄዱ፤ ከዚያም እሁድ ዕለት በድጋሚ መጥተው ጥቃት አደረሱ፤ ከዚያም ነዋሪው አጸፋዊ እርምጃ በመውሰድ ውጊያው ተጀመረ፤ 18 ሰዎች ሞተዋል፤ ሲሉ ነዋሪው ሁኔታውን ገልጸዋል። ከተገደሉት ነዋሪዎች መካከል ያልታጠቁ እና ሽማግሌ መሞታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ወታደሮች ጨምሮ ጣልቃ በመግባት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ወደ ምሽት ላይ ተሳክቶላቸው አከባቢውን እንዳረጋጉት ነዋሪው አስታውቀዋል።

በወረዳው ከሚገኙ መንደሮች መካከል በሆነችው ቾኮርሶ መንደር ነዋሪ መሆናቸውን የገለጹልን እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው በእሁዱ ግጭት 18 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠው ቁጥራቸው ያልታወቀ የሚሊሻ አባላት መገደላቸውን ገልጸዋል።   

የፋኖ ታጣቂዎቹ ትግላቸው ከመንግስት ጋር ቢሆንም የኦሮሞ መንግስት ነው በሚል የአከባቢው ነዋሪዎችን ለመበቀል በሚል ጥቃት ያደርሱብናል ሲሉ ነዋሪው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፤ ባለፉት ግዜያት ከአስር ግዜ በላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን በማስታወስ።

ነዋሪዎቹ እንደነገሩን ከሆነ ሁኔታው ለግዜው የተረጋጋ ቢመስልም ግጭቱ ተመልሶ መምጣቱ አይቀሬ ነው ብለዋል። ከኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አርቱማ ፈርሲ ወረዳ በሚዋሰነው በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በማጀቴ ከተማ ዙሪያ ባለፉት ግዜያት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ መክረሙ ተገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ግጭቱን አስመልክቶ አዲስ ስታንዳርድ ከአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናት አስተያየት ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button