ዜናፖለቲካቢዝነስ

ዜና፡ በክልሉ ያለው ግጭት፤ የማዕድን ምርት ዘረፉን ፈተና ላይ ጥሎታል – ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2016 ዓ.ም፦ በአማራ ክልል ከሀምሌ ወር ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት የወርቅ ምርትን ጨምሮ በርካታ የማዕድን ሥራዎችን ማስተጓጎሉን እና ዘርፉን ፈተና ላይ መጣሉን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኃይሌ አበበ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ ያለው ግጭት ጥናቶች በአግባቡ እና በጊዜው እንዳይከናወኑ፣ ፈቃድ ጠያቂዎች በአግባቡ ፈቃድ ወስደው እንዳያለሙ ማድረጉን እና  የተሰጠው ፈቃድ በአግባቡ እንዲከናወን ለማስቻል እንቅፋት መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ የማዕድን  ምርቶችን ወደውጭ በመላክ 7 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 400 ሺህ ዶላር ብቻ መገኘቱንም ገልጸዋል። ይህ ሁሉ የአፈፃፀም ችግር ያመጣው በክልሉ ባለው ግጭት ነው ብለዋል። እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት “ውድመት እና ዘረፋ” መፈፀሙንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም 200 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት እቅድ ተይዞ በስድስት ወራት የተፈፀመው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መኾኑንም ኃላፊው ተናግረዋል። ለ45 ሺህ ዜጎች በማዕድን ዘርፍ የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ የተፈፀመው ከ9 ሺህ የበለጠ አለመኾኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ በ36 ፕሮጀክቶች 25 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ለማጥናት አቅደው በተፈጠው ችግር ምክንያት ባሰቡት ልክ አለመፈፀማቸውንም ገልጸዋል። ማሽኖችን ይዘው ወደ ጥናት ቦታዎች ለመሄድ የተደረገው እቅድ አለመሳካቱንም አስታውቀዋል። የማዕድን ሃብት ሥራ ሸለቆዎችን እና ተራራዎችን እንደሚያዳርስ የተናገሩት ኀላፊው “የጸጥታ ችግሩ” በታሰበው ቦታ እንዳይኬድ አድርጓል ብለዋል።

ለዘርፉ ያለው የአመለካከት ችግር፣  በቂ ገንዘብ አለመኖር፣ የቴክኖሎጂ እና የሰው ሃብት ልማት ችግር፣ የባንክ  ብድር አገልግሎት አለመኖር እና  የመንገድ ተደራሽነት አለመኖር ለዘርፉ ፈተናዎች መኾናቸውን ነው ያነሱት።

የአማራ ክልል ወርቅ የለውም የሚለው አስተሳሰብ ቀርቶ ባለፈው ዓመት ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ አቅርበው እንደበር ያስታወሱት ኀላፊው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ወርቅ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ወርቅ እንዳይመረትባቸው ማድረጉን እና የተመረቱትም ቢኾን ለገበያ ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የግራናይት ምርት በማቅረብ እንደ ሀገር አንድ ሦስተኛው ድርሻ ያለው የአማራ ክልል በዚህ ዓመት የነበረውን ድርሻ አጥቷል ነው የተባለው። የጸጥታ ችግሩ በክልሉ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘንድሮ 10 ፋብሪካዎችን ለማስመረቅ አቅደው እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የሚመረቁ ፕሮጀክቶች ከሦስት አያልፉም ነው ያሉት። ይሄም ለክልሉ “ታላቅ ውድቀት እና ፈተና” መኾኑን ነው ያመላከቱት። የጸጥታ ችግሩ መልማት በሚቻልበት አግባብ እንዳይለማ የሚያደርግ እና ወደ ኋላ የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተባብሮ በመሥራት ክልሉን አስተማማኝ ሰላም ላይ ማድረስ ይጠበቃልም ብለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አማራ ክልል መንግስት ባውጣው መግለጫ፤ ባለፉት ወራት እየተካሄደ ባለው የትጥቅ ግጭት፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ በታጣቂ ቡድን በደረሰ ውድመት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል

በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል እያተካሄደ ባለው ግጭት፤ 967 የጤና ተቋማት መዘረፋቸው እና በ298 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መደረሱም ተገልጿል። 

ከዚህ በተጨማሪም ግጭቱ  ከ1 ሺህ 500 በላይ  የውኃ ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መደረሱን የክልሉ ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ገልጿል። በዚህም የተነሳ  817 ሺህ የሚኾኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ ናቸው ተብሏል።  አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button