ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ባለፉት ስድስት ወራት በዲጂታል ፋይናንሲንግ ስርዓት ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ተዘዋውሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2016 .ም፡ በዲጂታል ፋይናንሲንግ ሥርዓት ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ሊዘዋወር መቻሉን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን መረጃ ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

በሚኒስቴሩ የኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አቢዮት ሲናሞ (ዶ/ር) የዲጂታል ፋይናንሲንግ ሥርዓት ከተጀመረ አምስት ዓመታትን ማስቆጠሩን በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ክፍያን ጨምሮ የመንግሥት ድርጅቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እየተጠቀሙ መምጣታቸው የገንዘብ ዝውውር መጠኑ እንዲያድግ አድርጓል ሲሉ መናገራቸውን አስታውቋል።

የኢንተርኔት ባንኪንግን ጨምሮ የዋሌት የክፍያ ሥርዓት እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጹት ሃላፊው አጠቃላይ የክፍያ ሥርዓቱን የተቀናጀ ለማድረግ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም ከመመሪያዎች አንጻር በብሄራዊ ባንክ የተዘጋጀው የዲጂታል ፋይናንሲንግ እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተዘጋጀው ለተጠቃሚዎች ከለላ የሚሰጡ አዋጆች በዲጅታል ፋይናንሲንግ ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተገልጋዩ ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት በኤሌክትሮኒክስ አማራጭ ካመለከተ በኋላ ክፍያ ለመፈጸም በአካል እንዲቀርብ እንደሚደረግ ያስታወቁት ዶክተር ኢንጂነር አብዮት በመሆኑም አሠራሩን በማስፋፋት የተሳለጠ ለማድረግ እና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዲጂታል ፋይናሲንግ መጠቀሙ ከባንክ ውጭ የሚዘዋወር ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ማድረጉን ያመላከቱት ሃላፊው በዚህም የገንዘብ ዝውውርን መንግሥት እንዲቆጣጠር እና ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ተገልጋዩ ጊዜውን እንዲቆጥብ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የኢንተርኔት ተደራሽነት ችግር፣ ያሉት የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ውስንነት እና ማህበረሰቡ በዲጅታል ፋይናንሲንግ ላይ የግንዛቤ እጥረት ያለው መሆኑ ዋነኛ ከተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ላይ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል ያሉት ዶክተር አብዮት በዚህም የኔትወርክ ተደራሽነት ላይ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button