ዜናጤናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ባለፉት አምስት ወራት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2016 .ም፡ ባለፉት አምስት ወራት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን በጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር የወባና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ጉዲሳ አሰፋ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

በጀት ዓመቱ አምስት ወራት ለ4 ሚሊዮን 587 ሺህ 495 የወባ ተጠርጣሪ ህሙማን ምርመራ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል ያለው ዘገባው ከነዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን 575 ሺህ 442 የወባ ህሙማን ሆነው በመገኘታቸው አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ማለታቸውንም አካቷል።

እየጨመረ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በሁለት ዓመት ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ አጎበሮች ማሠራጨት ተችሏል ያለው ዘገባው በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ባለው ጊዜ ከ330 ሺህ በላይ አጎበሮችን ለክልሎች ከማሠራጨት በተጨማሪ፤ 1 ሚሊዮን 504 ሺህ 739 ቤቶች የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል እንዲረጩ ተደርጓል ብሏል።

ከስድስት ሺህ በላይ ባለ 5 ሊትር ፀረ-እጭ ኬሚካል ወደ ሁሉም ክልሎች ተሠራጭቶ ቋሚ የወባ መራቢያ ቦታዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ርጭት መካሄዱንም አስረድተዋል፡፡

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት በሽታው ባልተጠበቀ መልኩ እየጨመረ መሄዱን የገለጹት አቶ ጉዲሳ፤ 75 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ አካባቢዎች ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ በመሆኑ 69 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ተጋላጭ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ቢሆንም በደቡብ ምዕራብ ክልል፣ በደቡብ ክልል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስፋት የሚስተዋል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥና የዝናብ መቆራረጥ ምክንያት የወንዞች መቆራረጥ፣ የድርቅና ጎርፍ መከሰት፣ በየአካባቢው ያቆረ ውሃ መኖር፣ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ አገልግሎቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ መሆን ለበሽታው መጨመር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button