አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 3/ 2016 ዓ/ም፦ አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ዕርዳታ የሚውል 97 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ አሳውቃለች። በተጨማሪም ግሎባል ፈንድ በግጭት ለተጎዱ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ለጤና አገልግሎት የሚውል የ2.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
የአሜሪካ የሲቪሎች ደኅንነት፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚንስትር ኡዝራ ዘያ በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት እንዳስታወቁት ከዕርዳታው ውስጥ 87 ሚሊዮን ዶላሩ ለስደተኞች ድጋፍ የሚውል መሆኑ ገልጸዋል።
የሰብዓዊ እርዳታው ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚውል የ536 ሚሊዮን ዶላር ጥቅል ድጋፍ አካል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ እና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሰፊ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ያለመ ነው ተብሏል።
ሚንስትሯ ኡዝራ ዘያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስን (ዶ.ር) ጨምሮ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በሰብአዊ መብት ትብብር ጉዳዮች ዙርያ ውይይት ማድረጋቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ያዘጋጀችው ይህ ሰፊ የእርዳታ ጥቅል በአፍሪካ ቀንድ፣ በሳህል እና በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች የሚደረጉ ሰብዓዊ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ኤምባሲው ገልጿል።
ይህም በያዝነው ዓመት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ የአሜሪካንን ሰብአዊ እርዳታ መጠን ወደ 3.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ተገልጿል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከ38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል::
ከዚህ በተጨማሪም ግሎባል ፈንድ በግጭት ለተጎዱ ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ለጤና አገልግሎት የሚውል የ2.5 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ ማጽደቁን አስታውቋል።
ድጋፉ ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳን እና ወባን ለመዋጋት የሚውል ሲሆን ተግባራዊ የሚደረገውም ከመስከረም ወር 2017 እስከ ነሃሴ ወር መሆኑ ተናግሯል።
እ.ኤ.አ.ከ2003 ጀምሮ ግሎባል ፈንድ ኢትዮጵያ በኤችአይቪ፣ ቲቢ እና ወባ ላይ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ ለመደገፍ፣ ብሎም ዘላቂነት ያለው የጤና ሥርዓት ለመገንባት 3 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ማድረጉ ተገልጿል።አስ