ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያ ከ164 የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ሀገራት በአራት ዙር ድርድሮች ለቀረቡላት 900 ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቷን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/2016 .ም፡ ኢትዮጵያ ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር ባደረገቻቸው የአራት ዙር ድርድሮች ከድርጅቱ 164 አባል ሀገራት ለቀረቡላት 900 ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።

የአለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድር እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጠና ሥምምነትን አስመልክቶ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሀገራቱ በዕቃዎችና የአገልግሎት ንግድ፣ የገቢ ንግድ ፈቃድ አሰራር መረጃዎች፣ የመንግሥትና የንግድ ድርጅቶች መረጃና ሌሎች ጥያቄዎች ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

በአምስተኛው ዙር ድርድር ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁንና ለዚህ ተልዕኮ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የጥናት ሰነዱን እየገመገመ መሆኑን ተናግረዋል ያለው የኢዜአ ዘገባ ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ውስጥ የድርጅቱ አባል ለመሆን እየሰራች ነው ማለታቸውን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ባለኃብቶች የተለያዩ ኢኮኖሚ መስኮችን ክፍት ለማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጓ ድርድሩ እንዲሳለጥ እድል ፈጥሯልም ማለታቸውንም ዘገባው አካቷል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ እንደሀገር ከምታመርታቸው 6ሺህ 800 የምርት አይነቶች ውስጥ 5ሺህ 700ዎቹ በ10 ዓመት ነፃ እንዲኾኑ አቅርባ ይሁንታን ማግኘቷን አብራርተዋል ያለው አሚኮ ይህም ከምርቶቹ ውስጥ 90 በመቶ ይሁንታን ማግኘት እንደተቻለ አስገንዝበዋል ብሏል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አሁን የሚቀረው የሙከራ ሥራ መጀመር ነው ብለዋል ያለው ዘገባው “ይህን እምንገልጸው የግሉ የንግድ ማኅበረሰብ እና የሚመለከታቸው አምራቾች እንዲሁም ሌሎች እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነው” ማለታቸውን አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button