ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢጋድ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት አሳስቦኛል አለ፣ ማንኛውም ስምምነት በሶማሊያ መንግስት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል ብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 10/2016 ዓ.ም፡- በኢጋንዳ ኢንተቤ ልዩ ስብሰባቸውን ያካሄዱት የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እጅግ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ሲል አሳስቧል።

ማንኛው ስምምነት በሶማሊያ መንግስት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል ሲል ገልጿል። ሁለቱ ሀገራት ግጭት ከሚያባብሱ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ የጠየቀው ኢጋድ ገንቢ በሆኑ ንግግሮች ላይ እንዲያተኩሩም አሳስቧል።

በኢንተቤ በተካሄደው 42ኛው የኢጋድ መሪዎች ልዩ ስብሰባ ሌላኛው የመከረው አብይ ጉዳይ የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሲሆን ተፋላሚ ሀይሎች ግጭቶችን በማስቆም ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ ጠይቋል።

በሱዳን ጉዳይ ሁሉን ያሳተፈ ሰላማዊ ውይይት እንዲካሄድ ለማስቻል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ፈቃደኛ መሆኑን ጠቁሟል።

ሱዳን የተፋላሚ ሀይሎች ብቻ ሳትሆን የህዝቦቿ ናት ያለው ኢጋድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲያቆሙ ጠይቋል።

የሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ተቀዳሚ ሀላፊነት የሱዳን ህዝብ ፍላጎትን እውን ማድረግ ላይ መሆን ይገባዋል ሲል አጽንኦት ሰጥቶ አመላክቷል።

በኡጋንዳው የኢጋድ መሪዎች ልዩ ስብሰባ ላይ ከአባል ሀገራቱ መሪዎች መካከል የኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ ፕሬዝዳንቶች የተገኙ ሲሆን፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር፣ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔቲ ዌበር ታድመዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button