ፖለቲካ

ዜና፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ጋር በኢትዮጵያና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2016 .ም፡ ከተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጡ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ጋር በኢትዮጵያና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገለጸ።

በአውሮፓ ህብርት ፓርላማ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት ኢዛቤል ቪስለር የተመራ ቡድን ከኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ምክር ቤቱ በማህበራዊ የፌስቡክ የትስስር ገጹ ያጋራው መረጃ ያሳያል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የጸጥታ ችግር፣ የፌዴራል ስርዓት፣ የባህር በር ጥያቄ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲሁም የሴቶች መብት አጠባበቅን በሚመለከት የህብረቱ የፓርላማ አባላት እንዲብራራላቸው መጠየቃቸውን ጠቁሟል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ስለመግባቱም አስረድተዋል ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ እያነሳች ያለችው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአለም አቀፍ ህጎች መሰረት በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ የተከበሩ ዶ/ር ዲማ ገልጸዋል ያለው የምክር ቤቱ መረጃ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጥ የሚያስችላት በርካታ አማራጮች እንዳሉም ማብራራታቸውን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ኬይረዲን ተዘራ መግለጻቸውንም መረጃው አካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button