አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24/2016 ዓ.ም፡- የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ማህሙድ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር በስልክ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዙሪያ ማውራታቸው ተገለጸ።
ሁለቱም መሪዎች የጋራ የልማት ትብብራቸውን ማሳደግ በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል ሲል የአል ሲሲ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል። ሶማሊያ ደህንነቷን እና መረጋጋቷን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ግብጽ ከጎኗ እንደምትቆም አጽንኦት ሰጥተው አልሲሲ በስልክ ውይይታቸው ወቅት መግለጻቸውን ጽ/ቤታቸው ጠቁሟል።
በተመሳሳይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ማህሙድ ከኳታሩ ኢሚር ታሚም አል ታኒ ጋር በስልክ ማውራታቸውን የሶማሊያ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አስታውቋል። ሁለቱም መሪዎች በጋር ጉዳዮች እና በቀጠናዊ የጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ መምከራቸውን ያስታወቀው የቪላ ሶማሊያ ጽ/ቤት መረጃ በተጨማሪም የጠበቀ ትብብራቸውን ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ጠቁሟል።
በሌላ ዜና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ሞሃመድ ኦመርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው መወያየታቸውን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ሁለቱም ባለስልጣናት በመከሩበት ወቅት በኬንያ የደቡብ ሱዳን ልዩ ልዑክ አኮል ኩር ኩክ መታደማቸውንም ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
የውይይታቸው ዋነኛ አጀንዳ የቀጠናውን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልበት መንገድ እና አልሸባብን መዋጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደነበር ተጠቁሟል።
ኬንያ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ከሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነች ሲሉ ሩቶ መናገራቸውን አስታውቀዋል። መገናኛ ብዙሃኑ የዊልያም ሩቶ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የደቡብ ሱዳን ልዩ ልዑክ በጋራ የመከሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰንድ መፈራረማቸውን ተከትሎ መሆኑን በስፋት አትተዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባዎቻቸው የሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ ስምምነት ከዚህ በፊት በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በጋራ ለመጠቀም በሚያለሙት የላሙ ወደብ (ላፕሴት ፕሮጀክት) ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።