ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ማራዘሙን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9/2016 .ም፡ የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ማራዘሙን አስታወቀ። የሰላም ጥሪዉን ለተጨማሪ 7 ቀናት የተራዘመው ከህዝቡ በቀረበ ጥያቄ መሆኑን ገልጿል።

በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማሰብ መንግሥት ከታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ7 ቀናት የሚቆይ የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂ ኃይሎች ለሰላም ጥሪው አወንታዊ ምላሽ ሰጥተው ገብተዋል ሲሉ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) መናገራቸውን ዘገባዎቹ አመላክተዋል። ለእነዚህ አካላት አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደኾነም ተናግረዋል።

ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ምሁራን ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደኾነ ጠቅሰው ለዚህም የክልሉ መንግሥት ላቅ ያለ ምሥጋና እንዳለው ገልጸዋል።

ዶክተር መንገሻ በሰላም ጥሪዉ እየተደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ ቢኾንም ታጣቂ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም ለማምጣት ግን ጊዜው አጭር ስለመኾኑ ሕዝቡ በየመድረኮቹ አስተያየት ሰጥቷል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የወጣቶችን ጥያቄ መሰረት በማድረግ እና ለሰላምም ተጨማሪ እጆችን ለመዘርጋት በማሰብ የቀን ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት የክልሉ መንግሥት አምኖበት የ7 ቀናት ጭማሪ መደረጉን ተናግረዋል። በሕገ ወጥ መንገድ ትጥቅ አንስተው የነበሩ አካላት በተሰጣቸው ተጨማሪ እድል ተጠቅመው በየአካባቢዉ በሚገኙ የኮማንድ ፖስት ማዕከላት በመሄድ የሰላም ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁም ጥሪ ቀርቧል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button