ዜናፖለቲካ

ዜና: “ከህወሓት፣ ከሻዕብያ እንዲሁም ከብልፅግና ወገን የጦርነቱ ተጠያቂዎች ለፍርድ ባለመቅረባቸው አሁንም የጦርነት ፍላጎት አለ” - አረና ትግራይ ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ አሁንም ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች እየታዩ ያሉት እና የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰመው ባለፈው ሁለት ዓመት ለነበረው ጦርነት ከሁሉም ወገን ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ ነው ሲሉ የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ አስታወቁ።

ከህወሓት ይሁን ከሻዕብያ እንዲሁም ብልፅግና ወገን የጦርነቱ ተጠያቂዎች ስላልቀረቡ አሁንም የጦርነት ፍላጎት አለ ብለዋል።

ለዚህም ዋነኛ መፍትሔ የሚሆነው “የጦር ወንጀል ይሁን ዘር የማጥፋት ወንጀል የፈፀሙ አካላት፥ ለዓለምአቀፍ ፍርድ ቀርበው ሲዳኙ ብቻ ነው፤ ጦርነት የችግሮች መፍትሄ አድርጎ መመልከት የሚቆመው ብለን እናስባለን” ብለዋል።

በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር በወቅታዊ የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ትላንት ነሃሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል።

ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ለትግራይ አደጋ ይዞ የሚመጣ እና ሐላፊነት የጎደለው አካሄድ እየተከተለ ያለ ሲል የገለጹት ሊቀመንበሩ የህወሓት አመራሮች ልዩነታቸው የግል እና የቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ፍጥጫ የወለደው ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልጸዋል።

ይህ የህወሓት የውስጥ ጉዳይ ሊሆን እየተገባው ሆን ተብሎ ክፍፍሉ ወደ ህዝብ ለማውረድ ብሎም የከፋ ግጭት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሁለቱ ህወሓት ውስጥ ያሉ ቡድኖች አንዱ ሌላውን ከአስመራ እና አዲስ አበባ ጋር ካሉ ሐይሎች በመመሳጠር እርስ በርስ ይካሰሳሉ ያሉት የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ከሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል አንዱ ከኤርትራ ሐይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ፓርቲያቸው እንደሚገነዘብ ጨምረው ገልፀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አቶ ዓምዶም “ከሁለቱ ቡድኖች አንዱ ከሻዕብያ ጋር እየተገናኘ በሚል የሚሰሙ ውንጀላዎችም ሓቅነት ያላቸው ናቸው” ሲሉ ገልጸው “ይህ ሊቆም ይገባል፣ የሁለቱ ህዝቦች ወይም መንግስታት ግንኙነት ሊደረግ ከሆነ ደግሞ ይፋዊ በሆነ መንገድ ህዝብ አውቆት ነው ሊደረግ የሚገባው” ሲሉ አሳስበዋል፤ “ውስጥ ለውስጥ የሚደረግ ግንኘነት ጦርነት የሚያባብስ፣ ሌላው ሐይል ደግሞ ሌላ ደጋፊ እንዲፈልግ የሚያደርግ እንዲሁም ውጥረቱ ወደሌላ አካባቢ እንዲሻገር የሚገፋ አደገኛ አካሄድ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እና ድርድር መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል የሚል ጥሪ በተደጋጋሚ ለዓመታት ማቅረቡ የገለፀው ዓረና ትግራይ ይሁንና አሁንም ሁሉም አካላት ካለፈው ጥፋት ሳይማሩ ጭምር አደገኛ መንገድ ይዘው ቀጥለዋል ሲል ወቀሳ መሰንዘራቸውን ከጀርመን ድምጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button