ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “በትግራይ የሚካሄዱ ሁሉም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሊፈቱ ይገባቸዋል” - የትግራይ ጸጥታ አካላት ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ የሚካሄዱ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሊፈቱ እንደሚገቡና የህዝቡን ሰላም እና ደህንነትን ለማደፍረስ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች አጥብቀው እንደሚታገሉ የትግራይ ክልል ጸጥታ አካላት ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።

የክልሉ ጸጥታ አካላት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ ላይ በመምከር ባወጡት የአቋም መግለጫ “የክልሉ ፖለቲካ በትግራይ ልጆች እንጂ ከውጭ አካላት የሚጫን አይሆንም፣ አንቀበልም፤ ከዚህ ውጭ ለሚኖሩ ጉድለቶች አጥብቀን እንታገላለን” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ከየትኛውም የፖለቲካ አሰላለፍ ውጭ እና ነጻ ነን” ሲሉ ገለጹት ከፍተኛ አመራሮቹ  “የህዝቡን ተጠቃሚነት እና ደህንነት ለገበያ የማናቀርበ መሆኑን ቃል እንገባለን” ማለታቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

“በትግራይ የሚካሄዱ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሰለጠነና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈጸሙ፣ ሁሉም አስተሳሰቦች እድል አግኝተው በህጋዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል እንደሚገባ ሙሉ ዕምነት አለን” ብለዋል።

የክልሉን ህዝብ ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም አንድነቱን የሚጎዳ ነገር አንቀበልም ያለው መግለጫው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ፣ የትግራይ ግዛታዊ አንድነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

“በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የትግራይ ህዝብ ለህልውናው ሲል የከፈለውን መስዋዕትነት ይሁን ተጋድሎውን የሚያራክስ ማንኛውንም ተግባር ይሁን ሀሳብ ምንም አይነት ተቀባይነት እንደሌለው እና እንደምንታገለው መግለጽ እንወዳለን” ሲሉም አስታውቀዋል።

ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል ተሸጋግረናል ያሉት የጸጥታ አካላቱ በመግለጫቸው ያልተተገበሩ የፕሪቶርያው ስምምነት ውሎች በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመታገል እንዲተገበሩ እንሰራለን ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት አማካኝነት የተጀመሩ የክልሉን ሉዐላዊነት የማስከበር ተግባራት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ እና ነጻ ያልወጣ የክልሉን ህዝብ ነጻ የማውጣት አወንታዊ ተግባራትን እናደንቃለን ያለው የአመራሮቹ መግለጫ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ያልተፈጸሙ ጉዳዮች በአጭር ግዜ እንዲፈጸሙ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እናደርጋለን ብለዋል።

የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት እንዲተገበር ለማድረግ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመሆን በመከናወን ላይ ላሉ እንቅስቃሴዎች ያለንን አድናቆት እንገልጻለን ያሉት አመራሮቹ በመግለጫቸው የቀሩ እና ያልተተገበሩ የስምምነቱ ውሎች በአጠረ ግዜ እንዲፈጸሙና የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች እንዲወገዱ እና በስምምነቱ መሰረት እንዲከናወኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የተጀመረው የጸረ ሙስና ዘመቻ እንዲሳካ ለማድረግ፣ የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅሰቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ህዝቡን ያሳተፈ ርብርብ ለማድረግ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚጠበቅብንን እንፈጽማለን ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button