አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲያቸው በሚያካሂደው ጉባኤ እንደማይሳተፉ ትላንት ነሃሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለፓርቲው ሊቀመንበር በጻፉት ደብዳቤ አስታወቁ።
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ያላስተላለፈበት እና የማያውቀው የምዝገባ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ሲሉ በመግለጽ በጉባኤው የዲሞክራሲያዊ አካሄድ እና ህጋዊነት ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ባልተደረሰበት ሁኔታ አልሳተፍም ማለታቸውን በትግራይ ቴሌቪዥን ይፋ በተደረገው ደብዳቤያቸው ተመላክቷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ለፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በጻፉት ደብዳቤ ሊያካሄድ የታሰበው ጉባኤ ፓርቲውን እና የክልሉን ህዝብ አደጋ ላይ የሚከት ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
የፓርቲው የበላይ አመራሮች ውሳኔ ሰጭነትን በጣሰ አካሄድ በመከናወን ላይ ባለው የህወሓት ምዝገባ ሂደት እንደማይሳተፉ ያስታወቁት አቶ ጌታቸው ፓርቲው ሊድን የሚችለው አመራሩ እና አባላቱ በሚያደርጉት የተስተካከለ እንቅስቃሴ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፓርቲው ጉባኤውን ማካሄድ የነበረበት ከሶስት አመታት በፊት እንደነበር በደብዳቤያቸው ያወሱት አቶ ጌታቸው በአመራሩ ድክመት ሳይካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ጉባኤው መቼ እና እንዴት መካሄድ እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ አልደረሰበትም ሲሉ ገልጸዋል።
“መሬት ላይ ያለው ቅጥ ያጣ እንቅስቃሴ በመጨረሻ ፓርቲያችንን እና ህዝባችንን አደጋ ውስጥ የሚከት ለመሆኑ ግልጽ እየሆነ ይገኛል” ብለዋል።
ፓርቲው ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጻፈው ደብዳቤም ይሁን በህወሓት ስም የሚደረጉ የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ፓርቲውን የማይወክሉ እና የአንድ ቡድን ህገወጥ እንቅስቃሴ በመሆናቸው እንደማልቀበለው ላሳውቅ እወዳለሁ ብለዋል።
“አልቀበለውም ብቻ ሳይሆን እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ፓርቲውን የሚያፈርስ በመሆኑ በጽናት እታገለዋለሁ” ሲሉ የገለጹት አቶ ጌታቸው “ፓርቲው ሊድን የሚችለው በህገወጥ መንገድ መመሪያዎቹን እየጣሰ እንቅስቃሴ እያደረገ በሚገኘው ቡድን ሳይሆን በእኛ አመራሮቹ እና በአባላቱ የተደራጀ እንቅስቃሴ መሆኑን ላሰምርበት እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ በፓርቲያቸው አመራር ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩበት ገለጻ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ለጊዜያዊ አስተዳደሩን ዕቅድ መበላሸት እና ለክልሉ ጸጥታ መደፍረስ የህወሓት አመራር ተጠያቂ ነው ሲሉ የገለጹት አቶ ጌታቸው ክልሉ በቀውስ ውስጥ እየታመሰ ይገኛል፣ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የህወሓት አመራር ከህዝቡ ሰላም እና ደህንነት ይልቅ ለግላዊ ፍላጎቱ ቅድሚያ መስጠቱ ነው ሲሉ መተቸታቸው በዘገባው ተካቷል።
ፓርቲው ጉባኤ ማካሄድ እንዳለበት እምነታቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው “አሁን በፓርቲው በአመራር ላይ ያለው አካል ግን ስልጣን ለመቀራመት እንጂ ፓርቲው እንዲሻሻል አይደለም” ሲሉ ተችተዋል፤ ዝግጅቱ ግልጽነት እና ይዘት የለውም ሲሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በዘገባው የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት አካሂደው መመለሳቸውን እና ፓርቲያቸው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባቱን እንዲሁም በሁለት ሳምንት ውስጥ ምላሽ እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ መናገራቸው ተካቷል።
እንደ ደ/ጺዮን አገላለጽ ህወሓት ህጋዊ ፓርቲ ሁኖ መመዝገብ ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው ከጦርነቱ በፊት በነበረበት ህጋዊነት እንዲመለስለት ይፈልጋል፤” የተሻሻለው አዋጅ እንደ ፋኖ ላሉ ቀድመው ፓርቲ ሁነው ላልተመዘገቡ ቡድኖች ሊጠቅም ይችላል፣ እንደ ህወሓት ላሉት ጋን አይሰራም፣ ምክንያቱም እንደ አዲስ ፓርቲ በጭራሽ አንመዘገብም” ብለዋል። አስ