ዜናፖለቲካ

ዜና: “ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ በስፋት ተወያይተናል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም፡-ትላንት ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም መጠናቀቁ በተገለጸው የፕሪቶርያ ስምምነት ተግባራዊነትን በገመገመው የአፍሪካ ህብረት ሁለተኛው መድረክ ላይ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ጉዳይ በስፋት ውይይት እንደተካሄደበት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።

ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ መሻሻል ማሳየቱን የገለጹት አቶ ጌታቸው ነገር ግን ሁለቱም አካላት በተለይ በምዕራብ ትግራይ ክፉኛ የተጎዱ ዜጎችን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመፍታት ሂደቱን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ብለዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ የትግራይ ስደተኞች ጉዳይም መነሳቱን ጠቁመው እነዚህ ስደተኞች “በአሁኑ ግዜ ትርጉም አልባ በሆነው ግጭት ውስጥ አላስፈላጊ ጥቃት እየተጋፈጡ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በሱዳን የሚገኙ ስደተኞችን በተመለከተ ሂዩማን ራይት ዎች ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እየተቃረበ በመምጣቱ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ስደተኞች ላይ ስጋት ፈጥሯል ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የትግራይ ሀይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ሲል መኮነኑን ተከትሎ በገዳሪፍ የሚገኙ ከትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ህይዎች አደጋና ስጋት ከፍተኛ ነው ሲል ገልጿል።

የፌደራል መንግስቱ እና የህወሓት ሃላፊዎች በተሳተፉበት የፕሪቶርያ ስምምነት ተግባራዊነትን የገመገመው የአፍሪካ ኅብረት ሁለተኛው ስብሰባ የተለያዩ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልፀዋል ዋነኛዎቹም በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል ስለተካሄደው የፖለቲካ ውይይት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ስለመመለስ፣ የትግራይ ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ማቋቋም እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ማዋሃድ የሚሉት ናቸው ብለዋል።

የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ተገናኝተው ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ገለጻ ማድረጋቸውንም አቶ ጌታቸው አመላክተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ይህ ስብሰባ መጋቢት 11 ቀን በአዲስ_አበባ የተደረገውን የመጀመሪያ ስትራቴጂክ ግምገማ ተከትሎ የተደረገ ሲሆን ከመጀመሪያው ስብሰባ በኋላ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) “የጦርነት ማቋረጥ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ በማሳየት “በቋሚነት ለመመካከርና በተመሳሳይ መልኩ በቀጣይ ጥቂት ወራትም ለመገናኘት ተስማምተዋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር በሁለተኛው የስትራቴጂክ ግምገማ ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ አስታውቀው ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫውም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ ቁርጠኛ ነች›› ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button