ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ እንዲወጣ አንፈልግም ሲሉ የሶማሊያ ፌደራል መንግስት አካል የሆኑት “ጁባላንድ” እና “ደቡብ ምዕራብ” ግዛቶች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም፡- የሶማሊያ ፌደራል መንግስት አካል የሆኑት “ጁባላንድ” አስተዳደር እና “ደቡብ ምዕራብ” በሚል የሚጠራው የሶማሊያ ግዛት አስተዳደር የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ እንዲወጣ እንደማይፈልጉ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ መውጣት የተወሳሰበው የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታው ያባብሰዋል፣ አልሸባብ እንዲያንሰራራ ያደርገዋል ሲሉ ግዛቶቹ ገልጸዋል።

የጁባላንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሃሙድ ሰይድ አደን እንደገለጹት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሁሴን ሸክ አሊ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቀጣይ ታህሳስ ወር ለቀው እንደሚወጡ ማስታወቃችው በሀገሪቱ በሰፈሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ዘንድ ውጥረት መፍጠሩን ጠቁመዋል። የውጥረቱ መንስኤ መጻኢ ተልዕኳቸው በይፋ አለመታወቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ የሚጠቅመው አልሸባብን ነው ሲሉ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በአጠቃላይ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ሲሉ መናገራቸውን ጋረዌ ኦንላይ በዘገባው አስነብቧል።

ሁኔታው በሀገሪቱ በሚገኙ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ስምምነት ሊፈጠርበትየማይችል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሶማሊያ የሰፈረው ሰላም አስከባሪ ሀይል ከሀገሪቱ ለቆ የሚወጣም ከሆነ ውይይት ሊደረግበት ይገባል፤ ማንም በተናጠል ውሳኔ ሊያሳልፍ አይችልም ሲሉ አስታውቀዋል።

ጋረዌ ኦንላይን በሌላኛው ዘገባው እንዳስነበበው የሶማሊያ ሌላኛው ግዛት ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ ይወጣል መባሉን ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወመው መግለጹን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ጦር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት “በደቡብ ምዕራብ” የሶማሊያ ግዛት ሰላም እና ጸጥታ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል ማለቱንም ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የደቡብ ምዕራብ ግዛት የጸጥታ ጉዳዮች ሚኒስትር በኤክስ (ትዊተር) ገጹ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ስራ በተሰማራው ሀይል ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር አስቸጋሪ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ሲል ገልጾ ለአበርክቶው ምስጋና እናቀርባለን፣ የጦሩ ቆይታ ይቀጥላል፣ የድርሻቸውንም ይወጣል ሲል አወድሷል።

የኢትዮጵያ ጦር ለቆ ይውጣ መባሉ አላስፈላጊ እና የተሳሳተ ምክር ሲል ተችቷል።

ሶማሊያ በሀገሯ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ የሚገኙ ሁሉም የኢትዮጵያ ወታደሮች በቀጣይ አመት 2017 ታህሳስ ወር ላይ ጠቅልለው ይወጣሉ ብላ እንደምትጠብቅ ቪኦኤን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

የቪኦኤ ጋዜጠኛ የሆነው ሃሩን ማዕሩፍ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሼክ አሊን ጠቅሶ ትላንት ባሰራጨው ዘገባው የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (ATMIS) በቀጣይ አመት ታህሳስ ወር ተልዕኮው ካበቃ በኋላ “የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሃይል አባል አይሆኑም” ብሏል።

የቪኦኤው ሃሩን የፕሬዚዳንቱን አማካሪ ጠቅሶ እንደዘገበው ከቀጣይ አመት በኋላ በሶማሊያ በሚሰፍረው ጦር ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደማይኖሩ እና ከሌሎቹ የሰላም አስከባሪ ሀይል ካበረከቱ አራቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት #ጅቡቲ፣ #ኬንያ፣ #ኡጋንዳ እና #ቡሩንዲ የተውጣጡ ብቻ እንደሚሆኑ ጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button