ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የህወሓት ህጋዊ ዕውቅና እንዲመለስ የተደረጃ ትግል እና ከፍተኛ የፖለቲካ ድርድር እናካሂዳለን ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ፣ ፓርቲው ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7/2016 ዓ.ም፡- የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀመንበር እና #የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ነሃሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ባጋሩት መረጃ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እውቅና ውጭ በተጻፈ ደብዳቤ ነው ቦርድ ውሳኔ ያሳለፈው ሲሉ ገልጸዋል።

“ከማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ እና መመሪያ ውጭ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ተማምነናል በሚል ማደናገሪያ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር፣ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ከከፍተኛ የፓርቲው ካድሬ የተውጣጡ ተወካዮች የሄዱበት መንገድ አላስፈላጊ ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለን እንድንገባ አድርጎናል” ሲሉ አመላክተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በደብዳቤያቸው “ከፓርቲው ህጋዊ እውቅና ጋር በተያያዘ አዲስ የተሻሻለው አዋጅ እንደገና እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የሚያስገድድ፣ ወርቃማውን የትግራይ ትግል ታሪክ የሚያጎድፍ፣ በቀጣይ ቅርቃር ውስጥ እንድነገባ የሚያደርግ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው ፖለቲካዊ ድርድር በማካሄድ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ወስኗል” ሲሉ አውስተዋል።

በህወሓት ውስጥ ያለ ህገወጥ ቡድን ጉባኤውን ማካሄድ የፈለገው በፓርቲው ውስጥ የዘረጋውን ኔትዎርክ በመጠቀም የሚቃወሙትን አመራሮችን ከስልጣን ለማንሳት ነው ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በደብዳቤያቸው ኮንነዋል።

“የጋራ መግባባት ባልተደረሰበት፣ በማደናገር እና መርህ አልባ በሆኑ እና በኔትወርክ ባሰባሰቧቸው አመራሮች አማካኝነት ይቃወሙናል የሚሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ ብቻ እና የትግራይ ህዝብን እና ክልሉን አደጋ ላይ በሚጥል አግባብ የሚካሄድ ጉባኤ አበክረን ልንኮንነው የሚገባ እና ምንም አይነት እርባና የሌለው ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

በመጨረሻም “መላውን የትግራይ ህዝብና ሁሉንም አቅማችንን በማስተባበር፣ የተደራጀ ትግል እና ከፍተኛ የፖለቲካ ድርድር በማድረግ ድርጅታችን ህወሓትን ህጋዊ እውቅና እናስመልሳለን” ያሉት አቶ ጌታቸው “አሁን ካንዣበበብን ፈተና በመውጣት የትግራይን ሁለንተናዊ ማገገምና እድገት እናረጋግጣለን” ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤውን ዛሬ ነሃሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፓርቲው በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ በቀጥታ ስርጭት የጉባኤውን መክፈቻ ስነስርአት አስተላልፏል።

ህወሓት ጉባኤውን ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በይፋዊ የግል የፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት “ቀድሞ የገባውን ግዴታ ሲሸራርፍ የመጣው ህወሓት ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ደምስሶታል” ሲሉ ገልጸው “ድርጊቱ የትግራይ ህዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል” ሲሉ ኮንነዋል።

“አንዴ፡ ሁለቴ፡ መሳሳት ያለንና  የነበረ ነው፣ በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ስህተት ሶስቴ መፈጸም  ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ብቻኛው ተጠያቂ እራሱ ይሆናል” ሲሉ አሳስበዋል።

“ህግና ስርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button