አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6/ 2016 ዓ/ም፦ የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ነሐሴ 4 ቀን ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ.ር) ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እና ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን ውዝግብ በሰለማዊ መንገድ ለመፍታት መምከራቸው ተገልጿል።
ኤርዶጋን አክለውም፣ ኢትዮጵያ “የሱማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ስጋቶች የሚቀርፉ እርምጃዎች ብትወስድ፣ ውዝግቡን የመቀልበሱ ሂደት ይሳለጣል” ሲሉ መግለጻቸውን የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታውቋል።
የኢቶጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በበኩሉ ባወጣም አጭር መግለጫ፡ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓመተ ምህረት የስልክ ውይይት ማደረጋቸውን ገልጾ የሁለቱ መሪዎች ውይይት በሁለትዮሽ ጉዳዮች በተለይም የንግድ መጠንን በእጥፍ በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነበር ብሏል። ቀጠናዊ ትብብር ማጠናከርን በተመለከተም ውይይት ማድረጋቸውን አክሎ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ በጋራ ስምምነት መንገድ የባህር በር የማግኘት አስፈላጊነትንም አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል ተብሏል።
በተጨማሪም የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሞሐመድ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውይይታቸውም ቱርክዬ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የምታደርገውን ሁሉንአቀፍ ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አበክረዋል።
በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ያለመ ሁለተኛ ዙር ንግግር በቱርክዬ አንካራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ሁለተኛው ዙር ንግግር እንደሚካሄድ በኢስታንቡል በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት የቱርክዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን፤ በቅርቡ ወደ አዲስአበባ አምርተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የተወያዩ ሲሆን “በጉዳዩ ላይ በዝርዝር መምከራቸውን” መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸውም፤ “ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት ዕውቅና እስከሰጠች ድረስ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ውጥረት ይቋጫል” ማለታቸውን ሮይተርስን ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን ይጣረሳል በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ሲሆን የሁለቱም ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከዚህ በፊት በአንካራ በነበራቸው ውይይት ሌላ ዙር ድርድር ለማድረግ መስማማታቸውም ይታወሳል።አስ