ፖለቲካ

ዜና: “የጋምቤላ ክልልን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የፌዴራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተቀናጅተው እየሰሩ ቢሆንም የሚታይ ለውጥ አልመጣም” - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2016 ዓ.ም፡-የጋምቤላ ክልልን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ “የፌዴራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተቀናጅተው እየሰሩ ቢሆንም፤ ውጤት ላይ የሚታይ ለውጥ አለመኖሩን” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከፌዴራል ፖሊሲ፣ ከፌዴራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ የፀጥታ ሃይል ጋር በመሆን የማህበረሰቡ ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ውጤትን መለኪያ ያደረገ ስራ በመስራት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋምቤላ ክልል የነበረውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ ለክልሉ የስራ ኃላፊዎች በሰጠው ግብረ መልስ ወንጀለኞች በህግ እንዲቀጡ በክልሉ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ሚና አለው ብሏል።

የመስክ ምልከታ ቡድኑ አስተባባሪ ወ/ሮ ከድጃ ያሲን የማህበረሰቡን እና የክልሉን ሰላም የሚያደፈርሱት ወንጀለኞች ተለይተው በህግ እንዲቀጡ እና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የአመራሩ ቁርጠኝነት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከዚህ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመስራትም ወንጀለኞችን አጋልጦ የሚሰጥ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር ፓል ጆክ በክልሉ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማርገብ የአመራሩ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ በማንሳት ወንጀለኛን የማጋለጥ ችግር ስለመኖሩ እያንዳንዳቸው በተሰጣቸው ኃላፊነት የገመገሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወንጀለኞች የግድ ወደ ህግ መቅረብ አለባቸው በሚል ክልሉ በሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት የመለየት ስራ መስራታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸው በዚህም የፌዴራል የምርመራ ቡድን እገዛ እያደረገልን ነው ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button