አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29/2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በቀጥታ እንድታስተዳድር አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን ያስታወቁት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ጦር ሰፈር መገንባት እንደማትችል አስታወቁ።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ድንበር በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ታጁራ ወደብ እንድትጠቀምበት ሃሳብ ማቅረቧን አስታውቀው “ሆኖም ይህ አማራጭ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለመገንባት ያላትን ፍላጎት እንደማያካትት” አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ለማሟላት ቢያንስ አስር ወደቦች ያስፈልጋታል ሲሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ከ100 ሚሊየን በላይ ሸማቾች ያላት ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ኢትዮጵያ ከሶስት እና አራት በላይ ወደቦች ያስፈልጓታል” ሲሉ የተደመጡት አሊ ዩሱፍ “ኢትዮጵያ አሁን ያላትን የገበያ ፍላጎት ለማሟላት አስር ወደቦች ያስፈልጓታል፣ ስለዚህ እነዚህን ፍላጎቶች እንረዳለን፣ የሚጠበቀውን ለማድረግም እንሞክራለን” ብለዋል።
ዩሱፍ አክለው ጂቡቲ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እንደምትፈልግም አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያ ከአንድ በላይ መተላለፊያ እንዲኖራት በማገዝ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና ሁሉም እንዲረጋጋ በማድረግ በዋናው ቁምነገር ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል” ሲሉ የተደመጡት ሚኒስትሩ “እንደ ጂቡቲ የሚኖረን ሚና ያ ነው፤ ላለፉት አመታት ስናደርግ የነበረውም ይህንን ነው፤ አሁንም በእነዚህ መርሆች ላይ መስራታችንን እነቀጥላለን” ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፣ የጂቡቲን ጥያቄ ትቀበል ወይንም አትቀበል ግልጽ ባይሆንም የስምምነት አማራጩን ይፋ ያደረጉት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ ከኢትዮጵያ መሪዎች ያገኙት ምላሽ አወንታዊ ነው ማለታቸውን የቪኦኤ ዘገባ ያሳያል።
በአፍሪካ ቀንድ የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በቀጥታ እንድታስተዳድር አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን ጅቡቲ ማስታወቋን መዘገባችን ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻ እንድታገኝ አንደኛውን የጂቡቲ ወደብ “ሙሉ በሙሉ እንድታስዳድር” አገራቸው አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ መናገራቸውን ዘገባው አካቷል።
አማራጭ ሃሳቡን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌህ ለኢትዮጵያ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን እና በተፈፃሚነቱ ዙርያ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውም ተካቷል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በቀረበላት ሃሳብ እስከአሁን ያለችው ነገር የለም ያለው ዘገባው ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ በአማራጭ ሃሳቡ ዙሪያ በያዝነው ሳምንት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሁለቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት ዕድል ሊኖር ይችላል ሲሉ መናገራቸውም ተመላክቷል። አስ